ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ – ውብአለም ታደሰ (ዶ/ር)

 ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም.

ጉዳዩ፡ የ2012 ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ስራን ይመለከታል፡፡

በቅድሚያ የአለማችን እና የሀገራችን ከፍተኛ የህልውና ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ (Covid-19) በሀገራችን ከፍተኛ ጉዳት እንዳያዳያደርስ በእርስዎ አመራር የሚደረገውን የተቀናጀ ርብርብ ከልብ አደንቃለሁ፡፡ እስካሁን የምናየው ውጤትም በጣም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ መጨረሻውን ያሳምርልን፡፡ እርስዎም ራስዎንና ቤተሰብዎን ይጠብቁ፡፡ የኮሮና ቫይረስ በአንዳንድ ሀገራት ቤተመንግስት ድረስ መግባቱን አይተናል (እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ስፔን….)፡፡

ሚያዚያ 16፣ 2012 ዓ.ም. ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ያሉበትን ደረጃ ሲጎበኙ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ አብዛኛዎቹ ችግኞችም ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ እና ማንጎ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች መሆናቸው፣ ባለፈው አመት 4 ቢሊየን ችግኝ በሀገር አቀፍ ደረጃ መተከሉንና አብዛኛዎቹ መጽደቅ መቻላቸውን፣ የዘንድሮውን ጨምሮ በቀጣይ 4 አመታት እስከ 20 ቢሊየን ችግኞችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል እየተስራ መሆኑን ገልጸውልናል።

እንደ አንድ የደን ባለሙያ ካለፈው አመት ጀምሮ የሀገራችንን የደን ዘርፍ ለማሳደግ እያደረጉ ያለውን ጥረት፣ ለምሳሌ ያክልም፣ የአምናውን ተከላ በቅርብ እየተከታተሉ ማስተባበርዎ፣ በግልዎ በርካታ ችግኞችን መትከልዎ፣ የተከሏቸውን ችግኞች በተደጋጋሚ መንከባከብዎ፣ በአንድ ቀን ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኖች እንዲተከል አቅደው ማስፈፀምዎ፣ የሸገር ወንዞች ልማትና የእንጦጦ መናፈሻ ስራዎችን አስጀምረው በቅርብ መከታተልዎ፣ የዚህን አመት ተከላ የችግኝ ዝግጅት በአካል መገምገምዎ፣ በአጠቃላይ ለሀገራችን የአረንጓዴ ሌጋሲ ያለዎትን ራዕይ በአድናቆትና በአክብሮት የምከታተላቸው ስራዎች ናቸው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

አምና የተከልናቸው ከ4 ቢሊዮን በላይ እና ዘንድሮ የምንተከላቸው 5 ቢሊዮን ችግኞች ለምን አላማ እንደሚተከሉ የተሟላ መረጃ እርስዎም መላው ህብረተሰቡም እንዲኖረው ማድረግ የደን ልማት ስራዎቻችንን ስኬት እና ችግሮች ለመለየት እና ስራዎቹንም ለመከታተል ያመቻል፡፡ ስለዚህ በየአመቱ ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ ምን ያክሉ ችግኞች:

 • የዛፍ ዝርያ ችግኞች (ለጣውላ፣ ማገዶ፣ ተፋሰስ ጥበቃ፣ የከተማ ውበት…..)፣
 • የሳር ዝርያ ችግኞች (ለአፈርና ውሃ ጥበቃ)፣
 • የፍራፍሬ ችግኞች (እንደ አቦካዶ፣ ማነጎ፣ ፓፓያ……..)
ተጨማሪ ያንብቡ:  የትኛው ነው ሊያስጨንቀን የሚገባው?

መሆናቸው ቢገለፅ መረጃው ግልፅ ይሆናል፡፡ ያለበለዚያ በየአመቱ በድፍኑ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች መተከላቸው ብቻ ሲገለፅ ለብዙሀኑ የህብረተሰብ ክፍል ሁሉም የዛፍ ዝርያ ችግኞች ይመስላሉ፡፡

እንዲሁም በየአመቱ ከሚተከሉት የዛፍ ዝርያ ችግኞች ውስጥ ደግሞ የሚከተሉት መረጃዎች አብረው ቢገለፁ፡

 • ከተፈሉት ችግኞች ምን ያክል ሄክታር በደን ለመሸፈን ታቅዷል፣
 • ችግኝ የሚፈላው አላማን መሰረት አድጎ ነው እና፣ የተፈሉ ችግኞች ዋና አላማ (ምን ያክሉ ለጣውላ ምርት፣ ለኮንስትራክሽን/ለማገዶ፣ ለተፋሰስ ጥበቃ/የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ከተማ ለማስዋብ (Urban greening)፣ ለህብረተሰብ ለማሰራጨት፣ ለሽያጭ፣ ወዘተ..)
 • ምን ያክል ችግኝ በፕላስቲክ ከረጢት (Plastic pot)፣ እና በብተና (Bare root) የተዘጋጀ መሆኑ ቢገለፅ፡፡ ይህ መሰረታዊ መረጃ ነው፡፡ በሀገራችን በአብዛኛው የዛፍ ችግኝ የሚፈላው በብተና (Bare root) ነው (በበጀት እጥረት) እነዚህ ችግኞች አብዛኞቹም አይፀድቁም፡፡
 • የተፈሉት ችግኞች የባለቤትነት ሁኔታ (በመንግስት፣ በግል፣ በማህበራት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ ወዘተ..)፡፡ ይህም በየአመቱ የሚፈላው እና የሚተከለው ችግኝ የባለቤትነት ድርሻን ያሳየናል፡፡
 • ባለፈው አመት ከተተከሉት ችግኞች ምን ያክሉ ፀደቀ?

 

የዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት በርካታ አመታት የሚገለፀው የተፈላውና የሚተከለው የችግኝ መጠን ብቻ መሆኑ የዘመቻዎቹን ውጤታማነት ለመረዳትና ለመከታተል አዳጋች ያደረገዋል፡፡

ለመረጃ ያክል እንዲሆንዎት ከኢትዮጵያ ሚሌንየም ጀምሮ በቢሊዮን ቁጥር ያላቸው ችግኞችን በየአመቱ “ተክለናል”፡፡ ለምሳሌ ያክል አምና (2011 ዓ.ም.) 4 ቢሊዮን፣ በ2010 ዓ.ም. 4.3 ቢሊዮን፣ በ2009 ዓ.ም. 3.5 ቢሊዮን፣ በ2008 ዓ.ም 4 ቢሊዮን፣ በ2007 ዓ.ም. 3 ቢሊዮን፣ በ 2006 ዓ.ም. 5.3 ቢሊዮን ችግኞች መትከላችንን በየአመቱ ሪፖርት አድርገናል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በየአመቱ በተከታታይ አመታት በቢሊዮን ቁጥር የዛፍ ችግኝ የሚተክል ሀገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ መረጃው ያለው ቢያካፍለኝ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

የእርስዎን የአረንጓዴ ሌጋሲ ራዕይ በተገቢው መንገድ ለማስተግበር እንዲረዱ የሚከተሉትን አንዳንድ በሀገራችን የደን ዘርፍና የተፈጥሮ ሀብት በአጠቃላይ ያሉ አሳሳቢ ችግሮችን ትኩረት እንዲሰጣቸው ለመዘርዘር እወዳለሁ፡፡ ችግሮን በትክክል መረዳት ወደ መፍትሄዎች ለመሄድ ይረዳናል ብዬ አምናለሁ፡፡

 • በሀገራችን በየአመቱ ከምናለማው ደን የምናጠፋው የደን መጠን በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በየአመቱ በአማካኝ ከ92,000 ሄ/ር በላይ በደን ሀብት ይወድማል/ይመነጠራል፡፡ በየአመቱ የምናለማው ወደ 20,000 ሄ/ር ነው፡፡ ስለዚህ በአመት ከ 70, 000 ሄ/ር መሬት የደን መሬት ይመነጠራል ወይም የደን ሽፋን ይቀንሳል፡፡ ይህም ሀገራዊ የደን ሽፋን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ እንቅፋት ይሆናል፡፡
 • በደን ሀብት መመናመን ሳቢያ የሀገራችንን የደን ውጤቶች ፍላጎት ማሟላት ስላልቻልን በየአመቱ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የእንጨት ውጤቶችን (ጣውላ፣ ቪንየር፣ ወዘተ.) እናስገባለን፡፡ በአብዛኛው እዚሁ ማምረት እና እንዲያውም ወደ ዉጪ ኤክስፖርት ማድረግ ሲገባን፡፡
 • በርካታ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያክል፡ ሀገራችን ከሺህ አመታት በፊት ጀምሮ ለውጪው አለም ኤክስፖርት በማድረግ የምንታወቅበት የዕጣን ዛፍ (Boswellia papyrifera)፡፡ የኮሶ ዛፍ፣ ሶማሌ ክልል የሚገኘው የኸብ (Cordeauxia edulis)፣ ጋምቤላ የሚገኘው የቅቤ ዛፍ (Vitellaria paradoxa)፣ ጥቁር እንጨት፣ ወዘተ..
 • በተፋሰሶች መራቆት፣ የአፈር መሸርሸር ምክንያት በቢሊዮን ቶን አፈር ተጠርጎ ይወጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ የእርሻ ምርታማነት መቀነስ፤ የወንዞች፣ ሀይቆች፣ ግድቦች በደለል መሞላት ይስተዋላል፡፡ በርካታ ሀይቆቻቻችን የድረሱልን ጥሪ ማሰማት ከጀመሩ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አለማያ ሀይቅ ደርቋል፡፡ ጣና፣ ዝዋይ፣ አባያ፣ ጫሞ፣ አባያታ፣ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ ጣናን ለመታደግ ዘመቻ የተጀመረ ቢሆንም ዘላቂነት ያለው ስራ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
 • በርካታ ብሄራዊ ፓርኮቻችን ስማቸው ብቻ ቀርቷል፡፡ አንዳንድ ፓርኮች (ለምሳሌ አዋሽ ፓርክ) የቤት እንስሳት የግጦሽ ቦታ ሆነዋል፡፡ አንዳንድ ሀገራት ያሏቸውን የዱር እንስሳት ሀብት እና የተፈጥሮ ደን ዘመናዊ በሆነ መልኩ በማልማት የሳፋሪ/ የቱሪስት መዳረሻዎች ያደርጋሉ (ለምሳሌ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ)፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ…” -  ነፃነት ዘለቀ

 

ለተጨማሪ መረጃ ቢሆንዎት፣ ሀገራችን በ 1970- 1980 በነበሩት አመታት ውጤታማ የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ያካሄድንባቸው አመታት እንደነበሩ በርካታ የደን ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ ያን ወቅትም “ወርቃማው” የደን ዘመን ይሉታል፡፡ ወቅቱ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት የሰጠበት፣ ጠንካራ መዋቅር የነበረው፣ ተገቢ የሰው ሀይል እና የበጀት ድጋፍ የነበረበት፣ ወዘተ.. እንደነበር መረጃዎች እና የወቅቱ የዘርፉ ምሁራን ያስታውሳሉ፡፡ ዛሬ የመንግስት የደን ኢንተርፕራይዞች የሚያመርቷቸው የእንጨት ውጤቶች በአብዛኛው በዚያን ወቅት የለሙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ ይህንን ጥሩ ተሞክሮ በተለያየ ምክንያት ማስቀጠል አልቻልንም፡፡ መዋቅሩ ፈርሶ፣ ልምድ ያላቸው የደን ባለሙያዎች ተበታትነው፣ የተገነቡ አቅሞች ፈርሰው (ለምሳሌ የደን ክለላና ቅየሳ ፕሮጀክት ፈርሶ እንደገና ለማደራጀት ተገደናል፡፡)፣ የደን ልማት፣ ስልጠና፣ ምርምርና ኤክስቴክሽን ስርአት መልሰን ሳንገነባ እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህም ውድ ዋጋ እያስከፈለን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ የጀመሩት አረንጓዴ ሌጋሲ ራዕይዎ እንዲሳካ ሀገራዊ የደን ልማት፣ ስልጠና እና ምርምር ተቋማትን በተገቢው መንገድ ማጠናከር ይገባል ብየ አምናለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

በመጨረሻም፣ ሀገራችን ካላት ስነምህዳራዊ ተለያይነት (Diversity) እና ተስማሚነት፣ አመቺ መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን (ደን፣ አፈር፣ ውሃ…) በዘላቂነት በማልማት፣ በመጠበቅና በመጠቀም የበለፀገች ሀብታም ሀገር ማድረግ ይቻላል፡፡ ልናስፋፋቸው የምንችላቸው በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጥሩ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል ሁለገብ ጠቀሜታ እና ፈጣን ዕድገት ያላቸው በርካታ ዛፍ ዝርያዎች፣ በመንግስት እና በለጋሽ ድርጅቶች የሚካሄዱ ውጤታማ የደን ልማትና ጥበቃ ስራዎች እና ፕሮጀክቶች፣ በግል የሚለሙ ሞዴል የደንና ጥምር እርሻ ደን ልማት ስራዎች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ሀገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚካሄዱ ውጤታማ ስራዎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቁማር ወጣ!ገባ! ቦልቼ-ቦልቼ!!! - አገሬ አዲስ

ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅልን፣

አክባሪዎ

ውብአለም ታደሰ (ዶ/ር)

የደን ተመራማሪ

Let’s work towards a greener future and clean Ethiopia !

Wubalem

==============================================
Wubalem Tadesse (Ph.D.)
Senior researcher
Central Ethiopia Environment and Forest Research Center
Ethiopian Environment and Forest Research Institute (EEFRI)
E-mail: [email protected] or [email protected]
Tel: (+251)-912-132303 (Mobile)
P.O.Box: 30804 (Private)
Addis Ababa, Ethiopia
Skype: wubalem.tadesse
===================================================

3 Comments

 1. Another important point to consider is to classify land based on their suitability and capacity. Land for afforestation, reforestation, agroforestry and crop production should be mapped and delineated. Planting all sorts of trees on all available open land may not be appropriate. At the later stage the tree-planted land may be needed for crops to satisfy food security needs.

 2. የኢትዮጵያ ምሁራን እባካችሁ ምን አለበት ሞራልና ስብዕና ቢኑራችሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የደን ችግር የምፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ የግድ ለርዕሰ ብሄሩ ደብዳቤ መጻፍና በጭሆት ሰውን ማደንቆር አስፈላጊ አይምስለኝም፡፡ ብዙ የመረጃ ልውውጥ ዘዴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒክስና የህትመት የምርምር መድረኮች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አጉል የብልጽግና ካድሬነት ወይም ጉጀሌነት ደስ አይልም፡፡ ሃገሪቱ ብዙ ማህበራዊ ችግሮች አሉባት፡፡ የሚያወሩና ጥሩንባ የሚነፉ ብዙ ካድሬዎች ስላሉ ባለሙያው ስራው ላይ ትኩረት ቢያድርግ ለህሊናውም ለፍጣሪውም መልካም ነው፡፡

  • You do not understand how this matter is completed and it easy to blame and criticize those who have extensive knowledge on their fields. The article from Dr. webalem Tadesse is so profound and crucial do not derail it like the delegates who only think about filling the dam. There is no half negotiation and this is the future of the country. The Prime minister has two priorities COVID19 and GRED and Ethiopia has the upper hand now it is Ethiopian way or the high way.
   God bless Ethiopia and those who stood for truth, justice and peace.
   Yegomoraw LIJ.
   Canada.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.