/

የልውጥ ሕያዋን (GMO) አደጋ በኢትዮጵያና ደሀ አገራት ጆሮ ያለው ይስማ – ሰርፀ ደስታ

GMO

ሰሞኑን ብዙ ከሚነገርላቸው ጉዳዮች አንዱ የልውጥ ሕያዋን (ጂኤምኦ) ጉዳይ በኢትዮጵያ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ በዚህ ወቅት ለምን እንዲህ እንደ ተዛመተ እስካሁንም ለእኔ ግልጽ አደለም፡፡ የጥጥ ልውጥ ዘር ኢትዮጵያ ከውጭ ልታመጣ ነው ወይም አመጣች የሚል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ባለፈው እንደገለጽኩላችሁ የጥጥ ልውጥ ዘር ኢትዮጵያ እንዲገባ ተወስኖ እንደውም ገብቶ የተሞከረ መስሎኝ የነበረው ወደ አስር ዓመት እድሜ ያስቆጠረ መሰለኝ፡፡ ያ በፊት የታሰበ ወይም የተሞከረ የልውጥ ጥጥ ዘር ማስገባት ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንደሚገባኝ ግን ልውጥ ዘሩ ገብቶ የተሳካ አይመስልም፡፡ ምን አልባትም በእኛ አገር በተተከለበት ቦታ አካባቢውን ባለመልመድ ጠፍቶ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ሰሞኑን ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በርካታ ምሁራንም የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ አያለሁ፡፡ አንዳንዶች ያወግዛሉ ሌሎች ደግሞ ያበረታታሉ፡፡ እኔ እንደባለሙያነቴ ከሁለቱም ወገን ነኝ፡፡ በተለይ ከዘረመል (ጄኔቲክስ) ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች በብዛት በማበረታታቱ ያመዝናሉ፡፡ ያላቸውን ሥጋትም መግለጻቸው አልቀረም፡፡  ከሙያው ጋር ብዙም ትስስር የሌላቸው ባለሙያዎች ደግሞ ይሄን የልውጥ ሕያውን ነገር ከፍተኛ አደጋ እንደሆነ እየገለጹ ነው፡፡ እኔ ከሙያው ጋር ግንኙነት ከአላቸው ባለሙያዎች ስሆን ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ባለሙያዎች ሥጋት ቢያንስ ግማሹን  የምጋራ ነኝ፡፡ ሆኖም የእኔ ሥጋት መነሻ ከሌላ ምንጭ ነው፡፡

እኔ ከሁሉ በፊት ስለጥቅሙም ስለጉዳቱም በቂ የሆነ እውቀቱ ይኑረን ባይ ነኝ፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉም አፍሪካ አገራት በሚባልበት መልኩ ትልቅና ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ እየታሰበ አይመስልም፡፡ ዛሬ ስለ ልውጥ ዘሮች መጠቀምና አለመጠቀም ጉዳቶችና ጥቅሞች ላይ ያተኮረው እይታችን በእውቀትና ተጨባጭ በሆነ መረጃ ካልተደገፈ የሚያመጣው አደጋ ከፍተኛ ነው የሚል ጽኖ እምነት አለኝ፡፡ ልውጥ መለዘርም ሆነ ሌላው የሳይንስ ውጤት እውቀትና መረጃው ከአገራቱ ከራሳቸው መመንጨት እስካልቻለ ድረስ የተባለውም ጥቅም አይመጣም፣ የተፈራው ሥጋት አይቀርም፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በዚህ ዘርፍ ምርምር ብዙም ትኩረት እየሰጡ ያልሆኑ አገራት የነበራቸውን ሀብትም ለመጠበቅ ይሁን ሳይንሱ የሚያስገኘውን ትሩፋት ለመጠቀም እድሉ አይኖራቸውም፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ እውቀት ያላቸውና ምርምሩን የሚያካሂዱ ወደፊት በብዝሀ ሕወት ከፍተኛ ሀብት ያላቸውን አገራት ዘረመል በመጠቀም የሚያገኟቸውን በልውጥ ዝርያ መልክ እያዘጋጁ መልሰው ለእነዚሁ አገራት በውድ ዋጋ ከመሸጥ በላይ አገራቱ ያላቸውን የብዝሀሕወት ሀብት ሁሉ ሙልጭ አድርገው በመውሰድ አገራቱ ለራሳቸው ሀብት ጥገኛ የሚሆኑበት አደጋም አለው፡፡ ምክነያቱም እነዚህን አገራት በተወሰኑ ልውጥ ዝርያዎች ከአጥለቀለቁና አገራቱ የራሳቸውን ዝርያዎች ሁሉ ከተዎ በኋላ ከልውጥ ዘር አምራቾቹ መመጽወትን ያመጣል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ለዚህም ነው ከመንም በፊት በዚህ ዘርፍ የሚደረገው ምርምርና መረጃ ይቅደም የምለው፡፡

በቡርኪና ፋሶ ከዚህ በፊት የጥጥ ልውጥ ዘር ገብቶ በብዛት ከተመረተ በኋላ ጥራቱ ከአገር በቀሉ ሲነጻጸር ዝቅተኛ በመሆኑ ጉዳት እንዳስከተለ በሰፊው ተሰምቷል፡፡ ብዙዎች ልውጥ ዘር ሲባል በሁሉ ነገር የተሻለ አድርገው ይስሉታል፡፡ ልውጥ ዘሩ ግን የተለወጠው ለአንዲት ባሕሪ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዓለማችን በብዛት የሚነገርለት ልውጥ የጥጥ ዘር ተውሳክን እንዲቋቋም ተደርጎ የተሰራ እንጂ ከምረታማነቱና ከምርጥ ጥራቱ ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ እንደገባኝ በቡርኪና ፋሶ የገጠመው ይሄው ነው፡፡ ቡርኪና ፋሱ እውቀትና አቅሙ ቢኖራት የራሷን ጥራት ያለውን ጥጥ የተውሳክ መክላከያውን ጂን (ወሳኝ ዘረመል) ብቻ በማስገባት የራሷ ልውጥ ዝርያ በአዘጋጀት ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ባለሙያዎችም መንግስታትም ትኩረት እየሰጡት አይመስልም፡፡ ባለሙያዎችም ከአገራቱ ዝርያዎች የተሻለውን  ወሳኝ ዘረመሎችን ከሌላ ሕያው በማስገባት ወይም የራሱን በማስተካከል የበለጠ ለአካባቢው የተስማማ ውጤታማ የሆነን ዝርያን ከማውጣት ይልቅ ሌሎች የሰሩትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት የሰጡ ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው በተለመደው የዝርያ መረጣም ከውጭ አስገብቶ በማላመድ ለአገር እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በከፍተኛ ምርታማነቱ ይታወቅ የነበረው ቁብሳ በመባል በአገራችን የሚታወቀው ዝርያ በ60ዎቹ ገአረንጓዴ ለውት (ግሪን ሪቮሉሽን) ጊዜ በተለይም በሕንድና ደቡብ አሜሪካ ስኬታማ የሆነው ዝርያ በአገራችንም ስኬታማ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ይሄ ዝርያ በአሁኑ ወቅት በበሽታ ምክነያት ስኬታማነቱ እየቀነሰ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ የዘረመል ልውውጥ በብዙ አገራትም አለ፡፡ ይሄ ሲሆን ግን በአገራችን የነበረው የተለመደው የዝርያዎች ምርምር ሥራ ከብዙ አገራት በአልተናነሰ ይሰራ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከላይ የጠቀስኩት ቁብሳ በበሽታ ምክነያት አደጋ ላይ ሲሆን ተመራማሪዎች እሱን የሚተካ አዘጋጅተው ስለነበር ለገበሬው ለመድረስ ብዙም አልቸገረም፡፡ እንደማውቀው በአሁኑ ጊዜ በርከት ያሉ ሌሎች ዝርያዎች ቁብሳን እየተኩት ነው፡፡ በልውጥ ዝርያውም መሆን ካለበት እንዲሁ ነው፡፡ ከውጭ ማምጣት ወሳኝ ካልሆነ በቀር ማምጣቱ ትክክል አደለም፡፡ የራስን ማዘጋጀት ነው እንጂ፡፡ እንዲህ ሲሆን በዛው ልክ በልውጥ ዝርያዎች ባሕሪም የሚኖረን እውቀት ስለሚጨምር ሊያስከትሉ የሚችሉትንም ጎዳቶች በቀላሉ ማስቀረትና በአግባቡ መጠቀምንም ጭምር ያስችላል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ያህል በጥራት ወይም በሌላ በሚወደድ ባህሪ የታወቀ ጥጥ እንዳላት አላውቅም፡፡ ምን አልባት በአገር ውስጥ በአንዳንድ ባሕሪያቸው ልዩ የሆኑ የጥጥ ዝርያዎች ከአሉና ችግራቸው የተውሳክ ብቻ ከሆነ እነሱኑ የሚፈለገውን ወሳኝ ዘረመል (ጅን) በማስገባት ማሻሻል መልካም ነው፡፡ ይሄ ነው የሚባል ጥሩ የሆነ ባሕሪ ያላቸው ዝርያዎች ከሌሉን ግን ከውጭ ማስገባቱ ጥሩ ነው፡፡ እግረመንገዱም ሌላ ጥሩ የሆነ ባሕሪ ያለውን ዝርያ ወደአገራችን ለማስገባት ስለሚያስችል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ልውጥ ዝርያ በሚል ብቻ ለተውሳክ መከላከል ብቻ ስለተቀየረ ማስገባቱ ውጤቱ እንደቡርኪና ፋሶው ነው፡፡

ወደፊት የዘረመል ለውጡ በከፍተኛ ሁኔታ በዓለም ላይ መስፋፋቱ ስለማይቀር ሳንወድ በግድ ሌሎች በሚያመጡት ልውጥ ዝርያ ጥገኛ ከመሆናችን በፊት የራሳችን የሆነ ልውጥ ዝርያም ይሁን ሌሎች ከዚህ ጥበብ ጋር የተያያዙ እውቀትና አቅሙን ከአዳበርን አስፈላጊያችን ካልሆነ በቀር የራሳችንን ብዝሀ ሕይወት በምንፈልገው መልኩ ዘረመላቸውን እያስተካከልን ለራሳችን መጠቀም ብቻም ሳይሆን በከፍተኛ ዋጋ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡ ይሄን ሀሳብ ከዓመታት በፊት እንደዛሬው የዘረመሉ ሳይንስ ሳያድግ እኔም አሁን ያለኝን ያህል እውቀት ሳይኖረኝ በቁም ነገር ሳሰበው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ይሁን የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ መልኩ እንዲያስቡና ለዘርፉ ምርምር በአገራችን ትልቅ ትኩረት እንዲሰጡ አበክሬ አሳሰባለሁ፡፡ በእንሰት ላይ የእንሰት አጠውልግን በሽታ ለመቋቋም የሚያስችልን ወሳኝ ዘረመል ለማስገባት በኢትዮጵያ እየተሞከረ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ መበረታታት ከሚገባቸው ጀምር አንዱ ነው፡፡ በእንሰት ከተሳካ ምን አልባት ለምርምሩ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይችላል፡፡ በአንዴ ላይሳካ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ግን ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ እውቀቱ ከራሳችን መመንጨት አለበትና፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሀ ሕይወት ክምችቷ በዓለም ላይ ከሚጠሩት አንዱ እንደሆነች ግልጽ ነው፡፡ ወደፊት ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች በብዝሀ ሀብት የሚታወቁ አገራት ያላቸውን ሀብት በራሳቸው አዘጋጅተው ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከቻሉ እንደተባለው ትንሳዔያቸው ሩቅ አይሆንም፡፡ ይህ ዘርፍ ከየትኛው ሳንሳዊ ዘርፍ አነዚህ አገራት በዓለም ላይ ተፎካካሪም ብቻ ሳይሆን ብልጫ እንዲኖራቸው የሚያስችል ዘርፍ ነው፡፡ በዓለም ላይ የሥነ-ሕይወት ምርምር አሁንም ጨቅላ ነው፡፡ በዓለም ረጅም ታሪክና ባሕል ያላቸው አገራት ለዘመናት የኖሩበትን እውቀትም ለዚህ ዘርፍ ሊየወጡት ይችላሉ፡፡ አሁን ላይ በተነሳው ቫይረስ ብዙ መማር እንችላለን፡፡ በሳይንስ መጠቅን ያሉት ሳይሆኑ ለዘመናት ባሕላዊና ማሕበረሰባዊ እውቀት ያላቸው የተሻለ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን እውቀት እያሳዩን ነው፡፡ በቅርቡ በማዳጋስካር የዚሁኑ በሽታ ለመከላከል የፈጠሩት መድሀኒነት በዓለም ሳይቀር ትልቅ ትኩረት አግኝቶ አይተናል፡፡ ሆኖም ከደሀዋ ከማዳጋስካር በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ጤና ድርጅትን ጨምሮ ብዙዎች እየነቀፉት እናያለን፡፡ እውነታው ማላጋሲዎቹ ቢያንስ በተሻለ ሁኔታ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል መድሀኒት እንደሆነ እያሳዩ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ላይሆን ይችላል፡፡  እንግዲህ በእኛ አገር ጨምሮ በሌሎች በብዝሀ ሀብታቸው የሚታወቁ አገራት የዘረመሉን ሳይንስ የወደፊት ገበያቸው አደርገው ጭምር ቢያስቡት እላለሁ፡፡ ኢትዮጵያም ብዙ የባሕል መድሀኒት ባለሀብት ነች፡፡ ሆኖም እውቀቱ ሁሉ ለአገር በቀል ለሆነ ሳይንስ ያልደረሰ በመሆኑ ወደፊት ሁሉንም አጥተን የራሳችን ከሌሎች በግድ መግዛት እንደይሆን ከወዲሁ አሳስባለሁ፡፡

ይሄ ሳይሆን ቢቀር ግን ሳንወድ በግዳችን የዘረመሉ ሳይንስ ውጤት ተጠቃሚ መሆን ስለማይቀር የራሳችንን ሀብት በሌሎች ተዘጋጅቶ መጥቶ ለመግዛትና የማይረቡ ነገሮችንም ማራገፊያ ገበያ መሆናችን ልንሆን እንችላለን፡፡ የእኔ የልውጥ ሕዋን ስጋት የሚመነጨው ከአለማወቅ ሊመቱ ከሚችሉ አደጋዎች አንጻር እንጂ ከልውጥ ዘረመሉ ከራሱ ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ ለውጥ ዘረመል አደጋ ያመጣል ከተባለው እውቀቱ ከአለ አደጋውን ማስቀረት ይቻላልና፡፡ ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ በብዙ ቦታ በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ከልውጥ ዝርያ ሊመጣ የሚችለውን ስጋትና ጥቅሙን በብዛት ይረዱታል፡፡ ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ላይ ከውጭ የሚገቡ የልውጥ ዝርያዎች አደጋን በብዙ መልኩ አልተገነዘቡት ይሆናል፡፡ ወደፊት የአረቢካ ቡና ሲቢዲን የሚቋቋም ልውጥ ዘር ከወደ ሞንሳንቶ ቢመጣ በእርግጠኝነት አምጥተን እናምርት ማለታችን አይቀርም፡፡ እንግዲህ አስቡት አረቢካ ቡና ቤቱም ዘሩም ኢትዮጵያ ሆኖ ማለት ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ በሳንዲዬጎ የእጽዋትና እንስሳት ዘረመል ተመራማሪዎች ጉባዔ (ከ3000 በላይ ተመራማሪ የሚገናኝበት) ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ ጉባዔው በአብዛኛው ይካሄድ የነበረው በዘርፍ በዘርፍ ተከፍሎ በተለያየ አዳራሽ ስለነበር የቡና ምርምር ሥራዎች ወደሚቀርቡበት ገባሁ፡፡ በዚያ አዳራሽ የቀረቡ የምርምር ሥራዎች በአብዛኛው የሚያወሩት ስለ አንድ ከኢትዮጵያ ስለተገኘ ልዩ የቡና ዝርያ ነው፡፡ አብዛኞቹ ተመራማሪዎች ከላቲን አሜረካ ናቸው፡፡ በዛ አዳራሽ ግን እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ይቅርና አፍሪካዊ ታዳሚ እንኳን የለም፡፡ እኔ ራሴን ያገኘሁት እንደ ልዩ እንግዳ ነው፡፡ የተነሳው ተናጋሪ ሁሉ ግን ስለዚሁ የኢትዮጵያ ቡና ሳያወራ አይወርድም፡፡ በኢትዮጵያ ግን የቡና ምርምር የት ነው ያለው? ይሄ እንደምሳሌ ነው በብዙ ዘርፎች እንዲሁ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ያቺ ጤፍ እንኳን ዛሬ የሚመራመሩባት ሌሎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሌሎች ተቀጣሪ በመሆን ከማገልገል ያለፈ የምርምር ባለቤትነት ቦታ እንኳን ምን ያህል እንዳላቸው አላውቅም፡፡ በነገራችን ላይ የጤፍ ዘረመል አርትኦት (ኤዲቲንግ) እየተሰራ እንደሆነ ሰምቼ ነበር፡፡ እንግዲህ ስለ ልውጥ ዘረመል እያሰብን ጤፍ ልውጥ ዘረመል ሆና ዘር ግዙ ተብሎ ከሌሎች አገራት መግዛታችን መንገድ ላይ እንደሆነ አስተውሉ፡፡ አስከፊነቱ አብዛኞቹ ምርምሮች እየተሰሩ ያሉት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንኳን አደለም፡፡ ስለዚህ የምርምሩ ውጤት ባለቤትነት ለመሆን ምንም እድል የለም፡፡

ጆሮ ያለው ይስማ (መንግስት፣ ተመራማሪዎች የሚመለከታችሁ ሁሉ)

አመሰግናለሁ!

ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! ጥበብን ያድለን! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.