መጽሐፍ ግምገማ – ‘አንፋሮ’ ን አየሁት (በገ/ክርስቶስ ዓባይ)

‘አንፋሮ’ ደራሲ ሀብታሙ አለባቸው

አታሚ አሳብ አሳታሚ ድርጅት

የገጽ ብዛት 608

መጀመሪያ ዕትም ሚያዝያ 2011

Anfaro e1589910485351እንደ እውነቱ ከሆነ ደራሲ ሀብታሙ አለባቸው የተዋጣላቸው ብዕረኛ እንደሆኑ የሥራቸው ውጤት ይመሰክራል። የሥነ ጽሑህ አድናቂዎችም ሆኑ ወደፊት መጽሐፍ ለመጻፍ የሚያስቡ ሰዎች እንደ የክብር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’፤ እንደ አቶ ብርሃኑ ዘሪሁን ‘ማዕበል’፤ ወይም እንደ በዓሉ ግርማ ‘ኦሮማይ’ ሁሉ ይህንንም መጽሐፍ ቢያነቡ ብዙ የአጻጻፍ ስልትና ጥበብ እንደሚገበዩበት በድፍረት መጠቆም ይቻላል።

ደራሲው አቶ ሀብታሙ አለባቸው ዕፁብ ድንቅ የሆነ የመጻፍ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ፀጋም የተቸራቸው ሰው ናቸው ቢባል ሐሰት አይደለም። ይሁን እንጂ ይህንን ችሎታቸውን ለሐቅ ጉዳይ አልያም ሚዛናዊ በሆነ አገላለጽ ማዋል ሲገባቸው፤ ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደ ጡጦ ሲጠቡት ያደጉትን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንደ እርሾ በመጠቀም፤ የልጅ ኢያሱን ስም ኩሸት በሚባል መልኩ መጥፎ ተግባራቸውን ከሚገባው በላይ እያጋነኑ ታሪክ የማጉደፍ ተግባር መፈጸማቸው እጅግ የሚገርምና ይቅርታ ሊደረግለት የማይገባ ከወንጀል የማይተናነስ ድርጊት ፈጽመዋል።

አቶ ሐብታሙ አለባቸው ‘አንፋሮ’ ብለው የሰየሙትን ይህንን መጽሐፍ በጥናታዊ ሥራ ላይ ተመሥርተው ለመጻፋቸው ምንም ማስረጃ ወይንም ዋቤ መጻሕፍትን አላስቀመጡም። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ደራሲው ከልጅ ኢያሱ ጠላቶች ሲነገር፤ ሲጻፍና ሲወሳ የነበረውን የአንድ ወገን አስተሳሰብ ከማስተናገድም በላይ ይበልጡኑ እያጋነኑ ታሪክ የማጠልሸት ተግባር ላይ ተጠምደው ያንኑ ለማረጋገጥ ሞክረዋል። ‘ትንሽ ቆሎ ይዘህ ከአሻሮ ተጠጋ’ እንደሚባለው የልጅ ኢያሱን ትንሽ ድክመት አጉልቶና አባዝቶ እንዲህ ያለ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማድረግ ለኅሊና የሚቀፍ ከመሆኑም ባሻገር ፍጹም የሆነ ስብዕናን የማዋረድ (character assassination) ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለሙሉ-ዓለማችን ስንል ተመልሰናል !!

‘አንፋሮ’ ን  ከተስፋየ ገ/አብ ‘የቡርቃ ዝምታ’ መጽሐፍ ለይቶ ማየት አይቻልም። የወያኔ ተላላኪ የነበረው ተስፋየ ገ/አብ፤ በአፋዊ ተረት ላይ ተመሥርቶ በጻፈው ልብወለድ መጽሐፍ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ግፍ እንደ ተፈጸመ፤ እንዲያውም በአረመኔያዊነት ጡት እንደተቆረጠ አድርጎ በመተረኩ፤ የበታችነት ስሜት የሚያሰቃያቸው አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ያንን የፈጠራ ትርክት እንደ እውነተኛ ታሪክ በመጠቀም፤ በተለይ በአማራ እና በኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል መለያየትና መቃቃር የሚፈጥር ከፍተኛ የሆነ የጎሣ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንዲያራምዱበትና፤ ቆይቶም የሚያረጋግጡበትን የአኖሌን ሐውልት አንዲያቆሙ ረድቷቸዋል።

ከዚህም ሐውልት መቆም ጋር ተያይዞ፤ ወደፊት ብልህ መሪ እስካላፈረሰው ድረስ፤ በኦሮሞና በሌላው ማኅበረሰብ መካከል የተጎለተ እንደ ትልቅ የመለያያ ግድግዳ ሆኖ፤ አሁን ያለውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩም ትውልድ ደንቃራ ሆኖ መዝለቁ የሚያጠራጥር አይደለም።

ደራሲ ሀብታሙ አለባቸውም በወሎና በሸዋ ሕዝብ መካከል ልዩነት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የሕዝብን አንድነት ማጠንከርና ማቀራርብ ሲገባ ለመከፋፈልና ለማቃቃር መታተር ተገቢ ሊሆን አይችልም።እንደሚታወቀው የልጅ ኢያሱ ትክክለኛው ታሪካቸው እንዳይጻፍ ስውር ማዕቀብና ክትትል ሲደረግበት የቆየ መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ፤ እንደ እርሳቸው ያለ መሪ ኢትዮጵያ አግኝታ እንደማታውቅ እና ወደፊትም ልታገኝ እንደማትችል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች የመሰከሩት ጉዳይ ነው። ለዚህም እውነተኛነት ‘ፍትሕን ፍለጋ’ የተባለውን መጽሐፍ ማንበብ ይጠቅማል።

ተጨማሪና ዋና ማረጋገጫ የሚሆነው ደግሞ፤ ታላቁ ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፤ ልጅ ኢያሱ እንደዚያ ያለ ችሎታና ብቃት ባይኖራቸው ኖሮ ዙፋናቸውን አያወርሷቸውም ነበር። ምክንያቱ ይህ ሆኖ እያለ ደራሲ ሀብታሙ አለባቸው የእንግሊዞችን እና የፈረንሳዮችን ረቂቅ ሤራ ከሚገባው በታች አሳንሰው በመጻፍ የልጅ ኢያሱን ኃጢያት ግን እያጎሉ ተርከዋል፤ ‘በወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል’ እንዲሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህወሃት መራሹ አገዛዝ ባለሃብቶችን ከጎኑ ለማሰለፍ እያደረገ ያለው ሙከራ እንዳልተሳካ ሾልከው የወጡ መረጃዎች አመለከቱ

በተለይ የግብጻዊውን ጳጳስ ጉልህ ተግባርና ሚና በማቀጨጭ የእንግሊዞች ሴራ ተባባሪ እንዳልነበሩ አድርገው ያቀረቡት ገለጻ ታሪክን የሚያዛባ እንደሆነ ለማንም ግልጽ መሆን አለበት። ልጅ ኢያሱ ጀርመኖችን በማቅረብ እኛን አገለሉን በማለት እንግሊዞችን የአስቆጣቸውን፤ ማለትም ከጀርመኖች ጋር የነበራቸውን ጥልቅ ወዳጅነትና ጓደኝነት ከአንድ ጊዜ የጉግስ ጨዋታ ግንኙነት በስተቀር በፍጹም አልጠቀሱትም።

በተረፈ ግን የመቼቱ አመራረጣቸው፤ የገጸ ባህርይ አሰላለፋቸውና አመዳደባቸው እጅግ በጣም የሚደነቅና የሚመሰገን ነው። በታሪክነቱ ሳይሆን በሥነ ጽሑፉነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ ታላቅ መጽሐፍ መሆኑን በቅንነት ለመመስከር እወዳለሁ።

-//-

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.