ዘልዛሎች ቀይ ባህርን የሸጡ ባንዳዎች ዓባይን ያድናሉ ብለው የማይጨበጥ ጅራታቸውን አሁንም እየተከተሉ ነው! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ ([email protected]Blue Nile

እጅግ ብዙ የጋሻ መሬት መቅቡጥ ተሰጥቶት ሱዳን በዓባይ ተኢትዮጵያ ጎን መቆሟን በከበሮ እየደለቁ ሲያወድሱት የኖሩት ዘልዛላዎች ዛሬም ግድብና ቦንድ እያሉ የይህ አድግን ባንዳ ወሮበሎች የማይጨበጥ ጪራ እየተከተሉ የግድብን ዘፈን በመዝፈን ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ዘልዛላ ዘፋኞች ይህ አድግ ለሱዳን መሬት ሰጠ ሲባል ምላሳቸው ላንቃቸውን እንደ ውታፍ ጥቅጥቅ አርጎ ወትፎት ጪጪ ይላሉ፡፡ ይህ አድግ ቡራዩ ጋሞን ጨፈጨፈ፣ ሲዳሞ ጊድዮን፣ ተመላ አገሪቱ ደሞ አማራን አፈናቀለ ሲባሉ የውሀ ሺታ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህ አድግ አማራ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው አባረረ፣ ሴቶች ተማሪዎችንም አሳፍኖ ጪጪ አለ ሲባሉ ጆሮው ያልሰማና አንደበቱ የማይናገር ዱዳ ሆነው ያርፋሉ፡፡ ግድብና ቦንድ ሲነሳ ግን የአገር አሳቢና ትልቅ ሰው ለመምሰል ተይህ አድግ ጀርባ ተሰልፈፍው በአድር ባይ ኮቢያቸው ስንክ ሳር የሚያካክል ጥሑፍ ይጥፋሉ፤ በመስሎ አዳሪና በታጣፊ አንደበታቸው ደግሞ የራዲዮኑንና የቴሌቪዥኑን ጣቢያ ያጣብባሉ፡፡

የዓባይ አጠቃቀም ጉዳይ የእየሳሩሌም የባለቤትነት ጥያቄና የምዕራባዊያን መከካለኛው ምስራቅን የመቆጣጠር እቅድ መንትያ ወንድም ነው፡፡ የቀድሞው ግብጥ ፌሮን ጀማል አብዱል ናስር አረብን አስተባብሮ እስራኤልን ሊወጋ ሲዘጋጅና ምዕራባዊያንን አልታዘዝም ሲል በምዕራባውያን የምትረዳዋ እስራኤል “ዓባይን በሰማይ ቧንቧ እየሩሳሌም ወስደን አንተ ውሀ ተእስራኤል ትገዛለህ!” ስትል አስፈራርታው ነበር፡፡ ይኸንን ይጫኑ፡፡ Struggle Over the Nile – Legacy of dispute

እስራኤልን የሚያንገራግርና ለምዕራባውያን የማያጎበድድ የግብጥና የሱዳን ገዥ በተነሳ ቁጥር የግብጥ ጥጋብ ማስታገሻው መዶሻ ዓባይ ነው፡፡ የግብጥ አክራሪዎች “የአረብ ጸደይ” በተባለው አብዮት ወቅት ወደ ስልጣን ሲጠጉ ባንዳው ለገሰ ዜናዊ ዓባይን እንዲገድብ አስቸኳይ ቀጪን ትዕዛዝ ሲሰጠው በጥድፊያ መተከል ድንጋይ መከመር ጀመረ፡፡ ይኸንን የለገሰን መታዘዝ ያልጠረጠሩ ጮርቃዎችና የሚያውቁ አድርባዮች ቦንዳቸውን ይዘው እየተንከረፈፉ ተከተሉት፡፡

ለገሰ ድንጋይ ሲከምርና ቦንድ ሲያውጅ ሆዳምና ዘልዛላ ቦንደኛ በሰለፍ እንደሚሄድ የተጫነ ግመል ተከተለው፡፡ እንደ ግመል የሚከተለው ቦንደኛ “ቀይ ባህርን የሸጠ ባንዳ፣ እርስታችንን ለሱዳን መቅቡጥ የሰጠ ባንዳ፣ መሐሉን ለቻይና፣ ህንድና ፓኪስታን የቸበቸበ ባንዳ፣ አገሪቱን በዘር እሾህ ያጠረ ባንዳ ለምን ተዓባይ አተኮረ?” የሚል ጥያቄ አላነሳም፡፡

ብዙው ግመል ቦንደኛ ለገሰ ዜናዊ ስለታዘዘና ስልጣኑን ለማቆዬት መተከል ድንጋይ እንደካበ አልተረዳም፡፡ ልናስረዳ ብንጥፍም ሊያነብልንና ሊረዳን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ እንዲያውም አያሌ ጭንጋፍ የግመል መንጋዎች ይኸንን የባንዳዎች ቀንድ “ዓባይን የደፈረ..” እያሉ አርበኛ ሊደርጉት ከጅለው እግዜርንም አስቀየሙ፡፡ የግመሉ መንጋ ዶላሩን፣ ዮሮውን፣ ፓውንዱንና ብሩን የአህያ ጆሮ እያስመሰለ መስልጦ ለሙሰኞቹ የንግድ መርከብ ገዛና እርሱ ተባህር እንተወረወረ ኩበት ተንከርፎ ቀረ፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የለገሰ ህወሀት ሎሌነቱ ሲዳከም ለገሰን ተቆጥ የሰቅሉት ኃያላን ለገሰ ጡት አጥብቶ ያሳደገውን ባንዳ አብዮት አመዴን ተወንበር ኮፈሱት፡፡ ይኸንን ግልገል ባንዳ ተወንበር ሲኮፍሱት ቦንደኛው መንጋ አሁንም “ተግዮን ባህር የወጣው ሙሴዋ” ብሎ ተቀበለውና አረፈው፡፡ መንጋው በዚህ ወቅትም “ለገሰ ያሳደገውና ተለገሰ ጋር ሕዝብ የጨፈጨፈ፣ ግብረ ሰዶም ያስፈጠመ፣ እግርና እጅ ያስቆረጠ፣ ዘር ያመከነና አገር የሸጠ ጀሮ ጠቢ እንዴት ለአገረ-ገዥነት ሊበቃ ይችላል?” የሚል ጥያቄ አልጠየቀም፡፡

ጆሮ ጠቢው የጡት አባቱ የለገሰ የመንፈስ ልጅ ስለሆነ እንደ አባቱ እርሱም መንጋውን አንከረፈፈውና አረፈው፡፡ እንደ አሳዳጊው የለገሰ የመንፈስ ልጅ የሚፈራውና የሚሰማው የአገሩን ሕዝብ ሳይሆን ተባርጩማ የኮፈሱትን ኃያላን ነው፡፡ ጀርባው እስቲመለጥና መቃብር እስቲጠራውም የሚያገለግለው እነሱኑ ነው፡፡

ይህ ወቅት እስራኤልና ምዕራባውያን ተግብፅ ተደራድረው የፍልስጤን ገዥዎች አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ላይ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ ግብጥ የታዘዘችውን እንድትፈጥም መውቀሪያው መዶሻ ደግሞ ዓባይ ነው፡፡ ሱዳንን ለማንበርከክም መርቴሎው ዓባይ ነው፡፡ እንደ አለመታደል በዚህ ወቅት በዓባይ ጉዳይ ተደራዳሪዎች ደግም ባንዳው ለገሰ እየመለመለ ያሳደጋቸውና የክህደት በለስ ሲያበላቸውን የኖሩት ይሁዳዎች ናቸው፡፡ ይሁዳው አባታቸው ለገሰ ቀይ ባርን ሸጠው፡፡ ከሀዲ ልጆቹ ደግሞ ዓባይን እየሸጡ ነው፡፡ ቀይ ባህርን የሸጠ ባንዳ ዓባይን ሲሸጥም ዓይኑን አያሸው፡፡ በባንዳው የይህ አድግ ወሮበሎች የጦር መሪነትና ዲፖሎማሲ ዓባይ ይከበራል ብሎ የሚያምን በዘር ሰንሰለቱ ውስጥ የመንዘላዘል ጂን ያለው ብቻ ነው፡፡

የዓባይም ሆነ ሌላው የአገሪቱ ክብር የሚጠበቀው ይህ አድግ የሚባለው ክብር የለሽ ውቃቢ ተኢትዮጵያ አድማስ ተጠርጎ ሲጠፋና ባህርና ድንበርን ተማስደፈር አለመኖርን፤ የአገርን ሕዝብና ክብር ተማስደፈር አለመፈጠርን የሚመርጥ በእውቀት የተገነባ ቆራጥ መንግስት ሲመሰረት ብቻ ነው፡፡

አስር ሺ የመንደራቸውን ልጆች አስጨፍጭፈው ባህር ያስወሰዱት አረመኔ ባንዳዎች በዘልዛሎች ቦንድ የንግድ መርከብ በገዙበት ወቅት ተሰባት ዓመታት በፊት የቀረበ ጦማር ይህ ነበር፡፡

 

ዓባይን ማን መቼ ይገድበው?

በላይነህ አባተ ([email protected])     ሰኔ ሁለት ሺ ስድስት ዓ.ም.

መለኮትን ረስቶ ስለሌለ ልማት የሚሰብክ መነኩሴና ስለግድብ የሚያወራ ካድሬ ያልሰለቻችሁ እስቲ እጃችሁን አውጡ! የዓባይ ግድብ ወሬ በግፍ ዜጎችን እንደ መግደልና ማሰር ላሉ ወንጀሎች መሸፋፈኛ ድሪቶ ሆኖ ማገልገል ከጀመረ ውሎ አደረ፡፡ ዓባይ ጥቅም ላይ አይዋል ወይም ዓባይ አይገደብ የሚል አንድም ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አንዳንድ ምሁራንም ከካድሬዎች ጀርባ ተሰልፈው የግድብ ሰበካውን እንደ እስክስታ ያስነኩታል፡፡ በተለይ ባለፉት ሳምንታት ብዙ የግድብ ሰበካ ክታቦች ተከትበዋል፡፡ እነዚህ ክታቦችም ስለዓባይ ስለሚዘፈኑት ዘፈኖች፣ ስለዓባይ ሲሳይነት፣ ስለዓባይ ጎጅነት፣ ወዘተርፈ አትተዋል፡፡ ዓባይ ሲያስከትልብን ስለኖረውና ወደፊትም ስለሚያመጣብን መዘዝ በሰፊው አውስተዋል፡፡

አንዳንዶቹ እንዲያውም የአምስት አመት ልጆች እንደሚያስተምሩ ሁሉ ዓባይ ሐብታችን ስለመሆኑ፣ ዓባይን የመጠቀም መብት እንዳለንና ዓባይን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ እንደ ዓባይ በረዘመው ጽሑፋቸው መክረዋል፡፡ ዓባይን ለመገደብ የሕዝብ መብት መከበርን (የዜጎችን መረሽንም የሚጨምር ይመስለኛል) መጠበቅ እንደሌለብን ምሁራዊ ምክራቸውን ለግሰውናል፡፡

በእኔ እምነት ይህ ምናምንትስ ዓባይ ግድብ  የሚሉት ሲነሳ  የውይይት ርእስ መሆን ያለበት የዓባይ ባለቤትነታችን ወይም ደግሞ ዓባይን ስለመጠቀም አስፈላጊነት መሆን የለበትም፡፡ ዓባይ የማን ነው? ወይም ዓባይን መጠቀም ያስፈልጋል ወይ? ብለን የጎጃምን ወይም የባሌን የአስር አመት እረኛ ልጅ ብንጠይቀው በቂልነታቸን ይስቅብናል፡፡ እየተቀኘም በዋሽንቱ ይዘፍንብናል፡፡

በኔ አመለካከት ውይይት እሚያስፈልገው ከኢትዮጵያ ማህጸን መንጭቶ፤ እየተጠልመለመ ወደ ላይ አቅንቶ፤ ወንድሙን ጣናን ስሞ፤ ከገደል ላይ የሚፈጠፈጠውና የሚጨሰው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ባርኮ የሰጠን ግዮን ባለቤትነታችን መሆን የለበትም፡፡ ምክክራችን “ዓባይ ማደሪያ የሌለው ግንድ ይዞ ይዞራል” እያልን ስንደሰኩር ጅረቶችን እያስገበረ፤ አፈራችንን እያግበሰበሰ ስለሚኮበልለው ዓባይ ባለንብረትነታችን መሆን የለበትም፡፡

ጉልበት፣ ሐይልና ጥበቡ ካለን ፈረንጅ ለራሱ እንዲጠቅም አድርጎ የጋገረው የአለም ሕግ ባይፈቅድ እንኳን ወንዛችንን የመጠቀም ምርጫ እጃችን ላይ ስለሆነ ስለመብታችን በመደስኮር ብዙ ጊዜ ማጥፋት የለብንም፡፡ መመካከር ያለብን በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ ይመስለኛል፡፡

፩. ዓባይን ማን ይገድበው?

፪. ዓባይን መቼ እንገድበው?

፫. ዓባይን በምን መልክ እንጠቀምበት?

 

፩. ዓባይን ማን ይገድበው?

እርግጥ ነው፤ ዓባይን መገደብ ወይም ለሌላ ጥቅም ማዋል ያለበት መላው ያገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝብ በሙሉ ልብ  ይህንን ብሔራዊ ሐብት ለልማት ለማማዋል ብልህ መሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞና ትከሻ ለተከሻ ተደጋግፎ እንዲሰራ ታማኝና ፍቅር አምራች መሪዎችን ይሻል፡፡ ሕዝብ ጥርጣሬ ውስጥ እንዳይዘፈቅ ፈተና ያለፉ ባለማተብ መሪዎችን ይሻል፡፡

እንደምታውቁት እምነት ከማንነት ጋር ይያያዛል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው “ዓባይን ማን ይገድበው” በሚል መልክ ቀረበ እንጅ ዋናው አላማ የታማኝነትንና  የማተብን አስፈላጊነት ትኩረት ለመስጠት ነው፡፡ እውንን በአሁኑ ወቅት በሕዝብ የሚታመኑና ለአገሪቱ ሉአላዊነት የቆሙ ባለማተብ መሪዎች አሉን? አንዳድ ጸሐፊዎች  በየዋህነትም ሆነ በሌላ ምክንያት “ገዥዎቹ የሕዝብን መብት የሚደፈጥጡ ቢሆኑም ለአገሪቱ ስንል እነሱን ተከትለን አባይን እንገድብ ” እያሉ ለማሳመን ልባቸው ውልቅ እስከሚል ይሰብካሉ፡፡ “ቅድሜያ ፍትህ ይስፈን !” የሚሉትን የሰበአዊ መብት ተከራካሪዎችም “ቅድሚያ ግድብ” እያሉ ይሞግቷቸዋል፡፡

ቅድሚያ ግድብ ባይ ግድብ ሰባኪ ምሁራን ሆይ! መብት ረጋጭም ሆኖ እኮ ከእውነት አለመራቅ አለ! ነፍሰ-ገዳይም ሆኖ እኮ እውነተኛ መሆን አለ! ሕዝብ ጨፍጫፊም ሆኖ እኮ ከሀዲ አለመሆን አለ፡፡ የአገሬ ሽፍታ ሳውቀው እንደዚህ ነው፡፡ ሰው ይገላል፤ ነገር ግን ገደልኩ ብሎ ይፎክራል እንጅ አይዋሽም፡፡ ያገሬ ሽፍታ ከድሃ እየቀማ ወይም በድሃ ስም እየለመነ ገንዘብ ውጪ አገር ባንክ ውስጥ አይቀረቅርም፡፡ ያገሬ ሽፍታ ለድሃ ያዝናል፤ ወንበዴ እንዳይገፈውም ይጠብቀዋል፡፡ ያገሬ ሽፍታ ተደብቆ የአገር ንብረት አይዘርፍም፡፡ ቀምቶ ሲሄድም ለሕዝብ ያሳውቃል እንጅ፤ አይክድም፡፡ ያገሬ ሽፍታ ዳር ድንበሩን ተግቶ ይጠብቃል፡፡ አዎን! ሽፍታ እንኳን ማተብ አለው፡፡ ሽፍታ እንኳን ይታመናል፡፡ ሽፍታ እንኳን የአገሩን ዳር ድንበር አያስነካም፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ አንድ እንኳን ለክብሯ እሚከራከር፣ የማይወሰልትና የማይክድ የገዥ አባል አላት ወይ? ዛሬ  ሁለት ጸጉር አብቅለውስ ሽምጥ ሲክዱና ሲዋሹ የሚገታ ልጓም አላቸው ወይ? “በባእዳን እጅ ከውሽት ድርና ማግ የተሸረቡ ጉዶች” ብሎ ሕዝብ እሚጠራቸው ከመሬት ተነስቶ ነወይ?  ለሩብ ክፍለ ዘመን ሕዝብን አልዋሹትም ወይ?  ሞተው ሳለ አልሞትንም እያሉ ሽምጥጥ አድርገው የሚቀጥፉ የውሸት ከረጢቶች አይደሉም ወይ?

ከቅጥፈትና ክህደት ሸማ የተሰፉ ከንቱዎችን ተክቶሎ ሕዝብ ለመግጓዝ  እንዴት ይደፍራል?  እነሱስ በሕዝቡ ላይ የግዴታ ቀረጥ የጣሉት እነሱን አምኖ በፍላጎቱ  ገንዘብ የሚወረውርላቸው እንደማይኖር ተገንዝበው ሳይሆን ይቀራል?  “ለአገሬና ለሕዝቤ” በሚል ሰበብ ራስዎን ሸንግለው ቢከተሏቸው እንኳን የት ሲደርሱ እንደሚከዱዎት ሊያውቁ ይችላሉ? ሌላው ቀርቶ “እንደነዚህ አይነት የማይታመኑ ገዥዎች በድንገት ተነስትው እንደዚህ አይነቱን ሥራ የጀመሩት የሚያገኙት ጥቅም ቢኖር አለዚያም እንደልማዳቸው የውጪ ሐይሎች ተላላኪ ሆነው”  ብሎ ሕዝብ ቢጠራጠር ተገቢ አይደለምን?

የባልና ሚስት ፍች ሳይቀር ከሽማግሎች ጋር መመካከር ባህል በሆነበት አገር፤ በኤርትራ አላግባብ ፍች እንዳይመክር የተከለከለ ሕዝብ፤ የባህር በሩ ሲዘጋ አያገባህም የተባለ ሕዝብ የአባይን አጠቃቀም አላማ ጥርጣሬ ውስጥ ቢያስገባ ለምን ይፈረድበታል? ለም መሬቱ በሄክታር ዘጠና ዘጠኝ ሳንቲም ሲሸጥ የተመለከተ ሕዝብ፣  ምድሩ ለሱዳን ጉቦ በመሰጠቱ ልቡ የደማ ሕዝብ ለዚህ አላማው ላልታወቀ የአባይ ግድብ ጀርባውን ቢሰጥ መውቀስ ያስፈልጋል ወይ? አገሪቷን ካዋረዷት የመካከለኛው ምስራቅ መንግስታት ጎን የሚቆም ቡድን አይኑን በጨው ታጥቦ ገንዘብ ሲጠይቅ “ውጣ ከዚህ” ቢሉት ፍርድ አለ ወይ? ቅጥፈትን፣ ውሸትን፣ ክህደትን ባህሉ ካደረግ ቡድን ጋር አለመሰልፍ ያስወቅሳል ወይስ ያስመሰግናል?

ግድብ ሰባኪ ካድሬዎችና ምሁራን ሆይ! ውይይታችን እኮ ከስጋ በፊት ነፍስ፣ ከሆድ አስቀድሞ አገርና ሕዝብ ብለው የተሰውትን አቡነ ጴጥሮስን ስለመከትል ወይም አለመከተል አይደለም፡፡ እሰጥ አገባው ጴጥሮስን ዳግም ለሰው የሞሶሎኒ ጉዲፈቻዎች መጋዣ ሆኖ ስለማገልገል ወይም አለማገልገል ነው፡፡

እነዚህን ከንቱዎች በማገልገል ወይም ለማገልገል በማሰፍሰፍ ላይ ያላችሁ ግድብ ሰባኪ ምሁራን ሆይ! ለመሆኑ አንድ ሰው ስንት ጊዜ ቢዋሻችው በውሸታምነት ትፈርጁንና ትለዩታላችሁ? ምን ያህል ጊዜ ቢከዳችሁ በከሐዲነት መድባችሁ ውል መዋዋል ታቆማላችሁ? ስንት ጊዜ ቢቀጥፋችሁ በቀጣፊነት ፈርጃችሁ ትሸሹታላችሁ? ስንት ጊዜ ቢሰርቃችሁ በሌብነት ፈርጃችሁ በተጠንቀቅ ትጠብቁታላችሁ? ሶስት፣ አስር፣ ሺ ወይስ ሚሊዮን ጊዜ?

አንድ ቀን እውነት ሳንሰማ፣ አንድ ረፋድ ታማኝነትን ሳናይ ሩብ ክፍለ-ዘመን ኖርን እኮ! የጆሮ ታንቡራችን በውሽት እየተበሳ፣ ልባችን በክህደት እየደማ፣ ሕሊናችን በቅጥፈት እየቆሰለ ሃያ ሰላሳ አመት ቆጠርን እኮ! ታዲያ የተበሳ ታምቡር፣ የቆሰለ ልብ፣ የተወጋ አንጀትና ህሊና ይዘን ዶሮ ሳይጮህ እንደገና ሺህ ጊዜ የሚክዱንን ጉዶች እንዴት ብለን እንከተል?

፪. ዓባይ መቼ ይገደብ

ዓባይ መገደብ የነበረበትማ ሙሴ ከዓባይ ከወጣበት ማግስት ጀምሮ ነበር፡፡ ክፉና ደጉን መለየት ከጀመርኩብት ጀመሮ እንቅልፍ የለሹ ዓባይ ሲያሳስበኝ ይኖራል፡፡ ካሚዎን ውስጥ ሆኘ ድልድዩን በተሻገርኩ ቁጥር “አይ ግዮን!” እያልኩ ያልተከዝኩበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ወደ ሜዲቲራንያን መንጎዱን  ትቶ በአሶሳ አቋርጦ፣ ጋምቤላን አዳርሶ፣ በቦረና  ዞሮ፣ ኦጋዴንን አርከፍክፎ ፣ የአፋር ግመሎችን አስጎንጭቶ፣ ባህረ-ነጋሽን ሰላም ብሎ፣ ሑመራን ካለማ በኋላ ተመልሶ ጣና ውስጥ እንዲገባ ዓባይን ለምኘው ነበር፡፡  እንደ አቡነ ጴጥሮስ የበቃሁ ስላልሆንኩ አልሰማኝም፡፡

“አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ሁመራም ሆነ ባህረ ነጋሽ ዛሬ የእኛ ስላልሆኑ ልመናህ ከንቱ ነበር ብላችሁ!”ይበልጥ ሆድ አታስብሱኝ፡፡ አዎን! በሐዘን ተውጦ እየተከዘ እንደ ቀበቶ ጥምጥም የሚዞረውን አባይ እያየሁ ስቆዝም ኖሬአለሁ፡፡ ስንኞችም ደርድሬአለሁ ፡፡ እርግጥ ነው፤ ዓባይን መጠቀም አለመቻል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዘወትር ሕመም ስለሆነ ዓባይ ጥቅም ላይ መዋል አለበት፡፡  ግን መቼ? እንደሚታወቀው እንኳን ዓባይን ከስራ ላይ ለማዋል የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈርም በቂ ዝግጅት ይጠይቃል፡፡

እንደምታውቁት ገላችን በተፈጥሮ ብዙ አይነት የጀርም መከላከያ ሐይሎች አሉት፡፡ በትሪሊየን በሚቆጠሩ ጀርሞች ተከበን በጤና የምንኖረው በዚህ የመከላከያ ሐይሎቻችን ምክንያት ነው፡፡  በገላችን የመከላከያ ሐይሎችና በአካባቢያችን ባሉት ጀርሞች የሐይል ሚዛን ሲናጋ በሽታ ይፈጠራል፡፡ የሰውነት መከላከያ ሐይሎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲዳከሙ እንኳ ጠንካራው ጀርም በቆዳችን ላይ በሰላም የሚኖረው ደካማ ጀርምም ይጀግንና በሽታ ያመጣብናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  ጀርሞች ይዳቀሉና ጠንካራ ዘር በመፍጠር ጠንካራውን መከላከያችንን ሳይቀር አጥቅተው በሽታ ያመጡብናል፡፡ አባይን ተከትሎ የሚመጣ ጥቃትና  የእኛ የመመከትና መልሶ የማጥቃት ዝግጁነት በገላችንና በጀርሞች መካከል  ያለውን የሐይል ሚዛን ይመስላል፡፡

የጦቢያ ሕዝብ መከላከያ ሐይሉ እንደ ጣሊያንና ግብጥ ላሉ ለውጪ ጀርሞች መቅሰፍት እንደሆነ ደጋግሞ አሳይቷል፡፡ አለምም በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ዳሩ ግን ጊዜንና ሌሎችንም መስፈርቶች ሁሌ ቀመር ውስጥ ማስገባት ያሻል፡፡  በድሮ ጥቃቶች ወቅት የነበሩት የጦር መሪዎች፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የሚዘምቱ ጎበዝ አለቃዎች፣ ጥራኝ ጫካው እያሉ የሚያንጎራጉሩ ሽፍቶችና ምድሪቱም ሕዝቡም ለጠላት እንዳይገዙ ለመገዘት ብቃት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች ዛሬ አሉ ወይ? የሕዝብ መተማማንና የመንፈስ ጥንካሬ እንደ በፊቱ ጠንካራ ነወይ?

አገር ፍቅርን የሚስተምሩትን የባህል ዘፈኖች፣ ወኔን የሚቀሰቅሱ ሽለላና ቀረርቶዎችን አጥፍተን ወጣቱን ጫቱን እየቃመ በእራባውያን ፊልምና ዳንስ የነፈዘ ሱሰኛ አላደረግነውም ወይ? የገነባነውን የጦር ሓይል በትነን የመከከላከያ ደንደሳችንን አልደረመስነውም ወይ? ጦርነትን በብእራቸው የሚፋለሙ ምሁራንንና ታቦት ተሸክመው ሊዘምቱ የሚችሉ ካህናትን በእስራትና በብስጭት እያማቀቅን አልጨረስናቸውም ወይ?

በሐፍረት ተሸማቀው የተመለሱት ቅኝ ገዥዎች አሁን ወንበር ላይ ቁጢጥ ያሉትን ጉዶች በዘርና በጎጥ አጥምቀው እንደ መተት አልበተኑብንም ወይ? በመቀነስና በክፍልፋይ የሂሳብ ስሌት አሰልጥነው የቋንቋ ካርታ መሬት ላይ እንዲያሰምሩ አላኩብንም ወይ? የተሳስርንበትን ሰንስለት በጥሰው በክልል በረት ውስጥ አላጎሩንም ወይ? በየበረቱ የታጎረው ሕዝብስ ዳግም እንዳይገናኝ የጥላቻ ድንጋይ እየተካበና የውሸት ታሪክ እየተነዛ አይደለም ወይ? ሕዝቡ በሃይማኖት እንዲለያይ የማይፈነቀል ድንጋይ አለ ውይ? ገዳማትና ቤተ ክርሲቲያንን መለኮትን ረስተው እንደ ካድሬ የሌለ ልማት የሚሰብኩ “ካህናት” ምሽግ አላደረጓቸውም ወይ?

በአለም አቀፍ ግንኙት ጥበብ የተካነ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኛ ወይም አምባሳደር አለን ወይ? ይህ መስሪያ ቤት በአሞሌ ጨው እንደ ላም በሚደለሉ እንሰሳዎችና አንገታቸውን አቀርቅረው በሚታዘዙ ሎሌዎች የተሞላ አይደለም ወይ? ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ፍርድ ቤት ቀርበው የተፈርደባቸውን ፍርድ እንደተፈረደላቸው አድርገው በሚረዱ ማፈሪያ ማይማን የተሞላ አይደለም ወይ?

ታዲያ አብሮን ከሚኖረው የባንዳ ጀርም ሳንገላገል ውሃ የጠማው የውጪ ጀርም መርዝ ሲረጭብን የምንቋቋምበት ማርከሻ መድሃኒት አዘጋጅተናል ወይ?  ሕዝብ ካበረ ግብጽን ከጣሊያን የበረታ ቅጣት መስጠት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ዱባና ቅል ለየቅል ናቸው፡፡ ጣሊያን ትርፍ ለማትረፍ መጥቶ የነበረ ጀርም ሲሆን ግብጽ ግን ያለውን ብቸኛ ውሃ ላለማጣት እንኳን ያለውን ተበድሮም መርዝ የሚረጭ ጀርም ነው፡፡ ግብጽ በርና መስኮት እንደተዘጋበት ድመት በጥፍር ለመቧጠጥ፣ በእንክሻም ለመናከስ ጸጉሩን በማቆም ላይ ያለና ተኝቶልን የማያውቅ ጀርም ነው።

ግብጽ ዛሬ ምስር ብቻ አይደለም፡፡ ከእስራኤል በስተቀር መላው የመካከለኛው ምስራቅ ሕዝብ የግብጽ አጋር ነው፡፡  ሱዳንም ቢሆን ከግብጽ ጋር የሚስለለፍ ነው፡፡ አንዳንዶች ሱዳን  የጦቢያን መሬት እንዲወስድ ስለተፈቀደለት በአባይ ጉዳይ ከግብጽ በመለየቱ ፈንድቀዋል፡፡ በዚህ የተሞኙ (ወይም ለማታለል የሚፈልጉ) ግድብ ሰባኪዎች ያልዳሰሱት ግን አባይ ላይ የተፈጸመው የግብጽና የሱዳን የሸሪያ ጋብቻ መሻከር እስከመቼ እንደሚዘልቅ ነው፡፡

የግብጽ ጋጠ ወጥ የሕዝብ ተውካዮች ተስፈንጣሪዎችን እየረዳን ኢትዮጵያን እንበታትናታለን አለዚያም በቦንብ እናጋያታለን እያሉ እየደነፉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ግድብ ሰባኪዎች “ግብጽ አሁን የደከመችበት ጊዜ ስለሆነ ጊዜው ሳያመልጠን ቶሎ ብለን ግድቡን እንስራ” የሚል ውኃ የማይቋጥር ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ግድብ ሰባኪዎች ሆይ ! ግድቡ ጥበቃ እሚያሻው እኮ እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ነው፡፡

የውጪ ጥቃት በጣም ያማል፡፡ አሁን እንኳን ንቀውን በየመድረኩ የሚደነፉት ያሳምማል፡፡ ከውርደት ለመዳን የቁሳዊና መንፈሳዊ ሐይል ብቃታችን መፈተሽ ያሻል፡፡ እንግዲህ ዝግጅታችን የእኛን ክብር ሲጠነቁሉ ለመከላከል የሚያስችል፤ ግንባችን ሲያጋዩ ደግሞ የነሱን ግድብና ፒራሚድ ወደ አሸዋነት ለመቀየር የሚያስችል ነወይ?

፫. ዓባይን በምን መልክ እንጠቀም

ዓባይ የሚገደበው ሲነሽጥ ተንደርድሮ ሄዶ መተከል ላይ ድንጋይ በመቆለል መሆን የለበትም፡፡ በምን መልክ ዓባይን ብንጠቀም እንደሚሻል ሊያስተምሩ የሚችሉ አያሌ ባለሙያዎች አሉን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ እድሉ ከተሰጣቸው ይፈጽሙታል የሚል ግምትም አለኝ፡፡  ባለሙያዎች በምርምር አማራጮችን ሁሉ ፈትሸው የተሻለው መንገድ በሕዝብ ተቀባይንት ሲኖረው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ግድብ ሰባኪዎች ሆይ! ከሁለት-ሶስት አመታት በፊት ግድቡ እንዲሰራ የተወሰነበት የአሰራር ሂደት አጋርፋ ውስጥ ባቄላ እንዲዘራ ከተወሰነበት ቀጭን ወታደራዊ ትእዛዝ በምን ይለያል?

ማጠቃለያ

በሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ወደ ጎን ትተን ዓባይን አሁኑኑ እንገድብ የምትወተውቱን ግድብ ሰባኪ ካድሬዎችና ምሁራን ሆይ! ዓባይ ጥቅም ላይ አይዋል ወይም ደግሞ አይገደብ የሚል ዜጋ በማግኔትም ፈልጋችሁ አታገኙ፡፡ “አይኔን ዳቦ ያድርገው ብላችሁ!” ካልማላችሁ በስተቀር ችግሩ ከሕዝብ እንዳልሆነ የምታውቁ ይመስለኛል፡፡

ከክህደት፣ ከቅጥፈት፣ ከዘወትር ውሸትና  ከሌብነት የጸዱ ባለማተብ መሪዎችን ስታሳዩን “ጎሽ የኛ መሪዎች!” ብለን እንከተላቸዋለን፡፡ በዓባይ አጠቃቀም ጉዳይ የሚመለከታቸው የአገሪቱ ምሁራን ሰፊ ምርመር አድርገው መተከል ላይ ድንጋይ መከመሩ የተሻለ መርጫ መሆኑን ለሕዝብ አስረድተው የጸደቀ ስለመሆኑ ዋቢ ስታቀርቡልን እኛም እንደ እናንተ ቅስቀሳ እንጀምራለን፡፡

በተጨማሪም እቅዱ እንደ እስራኤል ያሉ አገሮች የራሳቸውን ጊዜአዊ ፍላጎት ለማሳካት የወጠኑት ሸር አለመሆኑን  ስታረጋግጡልን መልካም ሐሳብ ልንለው እንችላለን፡፡ በአባይ አጠቃቀም ሰበብ  የሚመጣውን ጥቃት ለመከላከልና የአጸፋ መልስ ለመስጥት የሚችል ጠንካራ የቁሳቁስና የመንፈስ ሐይል ተዘጋጅቶ ከሆነ ቀጥሉ እንላለን፡፡

ጨርሰን እስካልጠፋን ድረስ ዓባይን የሚወስድብን የለም፡፡ ይልቁንስ ከግድብ ካድሬ ጋር ስንሟገት ግዛታችንን ሱዳን እየወሰደብን ነው፡፡ ህንድ አረብና ቻይን ዜጎቻችንን ወደ ዱር ወርውረው መሬታችንን እያረሱት ነው፡፡ ጅቡቲዎች ሳይቀር ውሃችንን ለግመላቸው ሊያጠጡት ነው፡፡ “የጸጥታ ሐይሎች”ና ካድሬዎች ዜጎችን እያፈናቀሉ ነው፡፡ ስንቱ በግፍ ወህኒ እየማቀቀ ነው፡፡ ተማሪው፤ ሴቱና አዛውንቱ የጥይት ራት እየሆነ ነው፡፡

ግድብ ሰባኪ ምሁራን ሆይ! ምነው በግፍና በግዛታችን መደፈር ዙሪያ ለመጻፍ ብእራችሁ ይደርቃል? በግፍ ስለሚሰቃዩት ዜጎቻችንና በሉአላዊንታችን ላይ ሰለሚደርስብን ውርደት ለመስበክ አንደበታችሁ ለምን ጥርቅም ይላል? እንደምታውቁት ስለግድብ ለማስተማር ባለሙያ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ስለግፍ ለመጻፍ ግን ሰው መሆን ብቻ ይበቃል፡፡ ባለሙያ ከመሆንም ሰው መሆን ይቀድማል፡፡

ግድብ ሰባኪዎች ሆይ! እባካችሁ በማተብ የለሾች እንድንጠመቅ ስብከት፤ አብረናቸው እንድንጨፍር የጥሪ ክታብ መክተብ ይብቃችሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ሰኔ ሁለት ሺ ስድስት ዓ.ም.

በላይነህ አባተ ([email protected])   

 

2 Comments

  1. Many write about Abay rather than the other hardships mentioned above because these so called other hardships are very minor compared to the Abay issue. When it comes to Abay all Ethiopians regardless of their sex , age , educational status or political affiliations will entertain the topic , but the other topics you listed above are very elementary with only a small portion power hungry unreformed backward individuals willing to spend their time to read about them . It is high time now for all intellectuals to get in with the Medemer program by stopping to sweat the small stuffs and start writing about the big stuff Abay , if they expect people to care about what they write .

  2. For Girma Birru massacre of people, brutal displacements, tortures, sterilization and s o one are minor things. He does not look like a human being. Even hyenas and pigs are sensitive to their own species.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.