የሀገርና ወገን አድን ጥሪ ክፍል ፭ – የፌዴራሌዎችና ህወሃት ቅንጅት ለጥፋት መመከትንና የአባይ ሙሌት ማዘግየትን በተመለከተ – ከአባዊርቱ

65

ይቺን ሁለት ሶስት ቀናት የኢትዮጵያ ምቀኞችና ሴረኞች ተነስቶባቸዋል። ችግራችን ከኮሮናም በላይ ነው። ኮረናን ተታከው የአገሪቱን በኢኮኖሚ ደከምከም የማለት አዝማሚያን ተገን አድርገው ፣ በላባቸው ሳይሆን የሚሰፈርላቸውን አስቤዛ በመተማመን ፌዴራሌዎች ከዋና አጋፋሪያቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ዘመቻ ከፍተዋል። እኔ በበኩሌ እስትንፋስ ውስጤ እስካለ ዝም አልልም። እንደኔ የተቃጠላችሁም ዝም አትበሉ። ዋይታችን በህብረት ቢሆን ግን መልካም ነበር። መጀመርያ ልደቱና ጁዋር ብቻ መስለውኝ ነበር። እነዚህን ሁለት ኦፖርቹኒስቶች ዝም ሲባሉ ሌሎች ህወሃት መቀሌ ላይ የገጣጠማቸው ፌዴራሌዎች ዘራፍ ፣ እምቢኝ ለምርጫ፣ እምቢኝ ለቅርጫ እያሉን ነው። እንደ አንድ ለአገሩ እንደሚቆረቆር ዜጋ የሚከተሉትን መፍትሄ የምላቸውን በአደባባይ ስጠቁም ምናልባት የአገሩ ጉዳይ የሚገደው አይንና ጆሮ ይደርስና እልባት ይገኝበታል ከሚል ነው – ቢሳካም ባይሳካም።

፩) ዋናው የአባይ ጉዳይና አሜሪካ – ዘንድሮ የታሰበው ሙሌት ለከርሞ ይተላለፍ

መፍረድ እንኳ ይቸግራል አገሪቱ ኮሮናን የሚያክል ቋጥኝ ተሸክማ። ሆኖም የአባይ ጉዳይ አሁን ካለው የበለጠ ትኩረት ቢሰጠው ደስ ይለኛል። ባለፈው በቪኦኤ እንደሰማሁት በአለም አቀፍ ደረጃ ስለ አባይ ጉዳይ የሚመክሩና የሚዘክሩ የኢትዮጵያ ልሂቃን መማክርት ሸንጎ መኖሩን ነው። እጅግ የሚያኮራ ነው በእውነቱ። እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ጀግና ወገኖቻችን ያሉንን ያህል ከሀድያን በብዙ ቢላ የሚበሉም አሉን። እየተሰማ ያለው ባብላጫው የነዚህ ከሃድያን ቢላዎች ፉጨት በመሆኑ ያገር ወዳዶቹን መልካም ስራ እየዋጠው ይገኛል። መፍትሄ የምለው ልክ እንደቪኦኤው ዘገባ የአገር በቀል ሚዲያዎችም እነዚህን መልካም ተጋድሎዎች ከፍ ብታደርጉ ሌላው ቢቀር ለወጣቱ ተስፋና ብርታት ይሆናሉ። እነ ትናንሽ አይምሮ ጁዋልቱ (ጁዋርና ልደቱ) ስለ መስከረም ሰላሳ ሲዶልቱ አገር ወዳዱ ሁሉ በምሁራኑ መልካም አነቃቂ ፕሮፖጋንዳ ያሸማቅቃቸዋል። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን የአባይን ሙሌት ብተመለከተ ይቺን ክረምት ቢያልፈን መልካም ይመስለኛል። ይህን የምልበት በብዙ አገር ውስጥ (ከላይ የጠቃቀስኳቸው በጥቂቱ) ጉዳዮች ቢሆኑም ዋንኛው ትራምፕ ከሚሉት ሰውዬ እንዳንላተም ከሚል ስጋት ነው። ይህ ሰው የሚቀጥለውን የህዳር ምርጫ በዝረራ ስለሚሸነፍ ዴሜክራቶቹ ወደ መንበሩ ብቅ እስኪሉ መጠበቅ ብልህነት ይመስለኛል። ባይደን ሲያሸንፍ የኢትዮጵያ ጉዳይ ግድ የሚሏቸው ጥቁር ሴኔተሮች ፍትሃዊ ጆሮ ይስጡናል ብዬ እጠብቃለሁ። እስካሁንም ቆይተናልና አንድን ክረምት በመረጋጋት ብናልፈው ብልህነት ይመስለኛል። ድንገት በዲፕሎማሲው ግብጽ ልቧ ሊተብት ይችል ይሆናል፣ አስረዘምኩት ሙሌቱን ብላ። ለዚህም ብዙም እንዳታቅራራብን ምርጦቹ ያገሬ የቴክኒክ ሰዎች አንድ አይነት ለአደባባይ ሽያጭ የሚበቃ መፍትሄ አያጡልንም። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በወንዞቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ የማንንም በጎ ፍቃድ መጠየቅ አይጠበቅባትም – አሜሪካ ሆነች ግብጽ። ሆኖም ይህ ትራምፕ የሚሉት ሰውዬ በረኪና ጠጡ ለኮሮና የሚል መሪ የኢትዮጵያን አቋም እንደ ንቀት ወስዶ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ይከተናል ከሚል ስጋት ነው። የኮሮናውም ጉዳይ ገና የሚያመጣብን የኢኬኖሚ ጣጣ አለና እባክዎ ዶር አቢይና የመማክርት ሸንጎ በዚህ ጉዳይ በጥልቅ ተወያዩበት። አቶ ትራምፕ ይሸነፋል፣ አኪሩም ወደተሻለ ሁኔታ ይዞራል። የውስጥ የግብፅ አሽቃባጮችም ከአሜሪካ በቃላት ጦርነት እንድትላተሙ ይፈልጋሉና አደራ አስቡበት። ይተላለፍ ለከርሞ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰሞኑ የግብር ጭማሪ እና የፀረ-ሽብር ሕጉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው

፪) እንደተረዳሁት ጁዋር ሆነ አዲሱ የጥፋት ጓዱ ልደቱ አቢይ እርምጃ እንዲወስዱባቸው ይፈልጋሉ። ቀሪው ሀገር ወዳዱም እኔን ጨምሮ በጁዋር ላይ እርምጃው ምነው ዘገየ፣ ለምንስ ዶር አቢይ ያበላልጣሉ የምንል ብዙሃን ነን። እስቲ አገሩን የሚወድ ሁሉ ሰከን ይበልና ይህን ጉዳይ ያላምጥ። በበኩሌ ከሰሞኑ የጁዋርና ልደቱ ንግግር ፣ እናም የነሱን ንግግር ተከትሎ የሌሎች ጭምብል ፌዴራሌዎችና ህወሃት ፉከራና ቀረርቶን ሳጤነው መንግስት የሆነ እርምጃ እንዲጀምር ሆን ብለው “የሚማጸኑ” ነው የሚመስለው ። ለምን ይሆን? ኮረና በአንድ በኩል፣ ግብጽ በሌላ አቅጣጫ ኢትዮጵያን እንዲህ ቀስፈው ይዘው የነዚህ ክፉዎች በስመ ምርጫ በአገር ላይ ዛቻና ፉከራ መንግስትን ነካክተው መንግስት እንዲላተማቸው ሳይፈልጉ የቀሩ አይመስለኝም። የሁዋላ ሁዋላ በዚህ አምባጓሮ ተጠቃሚው ህውሃትና ጭምብል ፌዴራሌዎች ስለሚሆኑም ይመስለኛል። ስለሆነም መፍትሄ ቁጥር አንዱ መረጋጋትና ጠላትና ወዳጅን መለየት ነው። መንግስትም እንደበፊቱ በትእግስት ይራመድ። አገር ወዳዱ በህብረት ቆሞ ከፓርቲ በፊት የአገርን ልእልና ማስቀደም ይጠበቅበታል። ብዙዎቻችሁ በዚህ ላትደሰቱ ትችላላችሁ። እኔም አንድ ሰሞን የዶር አቢይ ትእግስት ትእቢትን ወለደ ብዬ ብዙ ብዬ ነበር። እርምጃው ከጅምሩ ቢሆን ነበር። አሁን መዘዙ ብዙ ነው። እስቲ ተመልከቱት ፣ የእስክንድር ነጋ የባለአደራ ፓርቲ ጥሪ እንኳ ከልድቱና ጁዋር የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም። በዚህ መከራ ጊዜ ጭራሽ አቢይን በእምባገነንነት ይፈርጃል። ማንን ለመጥቀም ነው? ወያኔዎቹስ ከዚህ የተለየ ምን አሉ? ፈጣሪ ሰከን ብለን ሁሉን ከአገር አኳያ እንድንመረምር ያድርገን እንጂ ያልጠበኩት እየሆነ ነው ያለው። እኔ አንድ ተራ ዜጋ የአገሪቱንና አለምአቀፍ ሁኔታን መገምገም ከቻልኩ እንደምን ስመጥር ፖለቲሻኖች ይህንን ማየት እንዳቃታችሁ አላውቅም ። የማንኛችሁንም ፖለቲካ ተለጣፊ ስላይደለሁ ይበጅ የመሰለኝን አቅርቤአለሁ። ስለሆነም በትህትና የምጠይቀው ሁለት የህብረተስብ ክፍልን ነው። አንደኛው ክፍል የአገሪቱ አካሄድ በጣም የሚያሳስበው ግን እጅግ ስሜታዊ በመሆን ያገኘውን መሳርያ ሁሉ መንግስት ላይ የሚወረውር ክፍል ነው። ሁለተኛውና ብዙሃኑ ዛሬም እንደትላንትናው በዝምታ አገሩን ለባንዳዎችና ከሀድያን በግላጭ ያስረከበውን ትውልድ ነው። የዚህ ሁለተኛው ክፍል ዝምታ ነው የጁዋር ቢጤውን ጥራዝነጠቅ እንደልቡ እንዲፈነጭና በትእቢት እንዲወጣጠር ያበቃው። ባለፈው ጁዋር በጀመረው ጦስ ያ ሁሉ ህዝብ ሲያልቅ አደባባይ ድምጻቸውን ከፍ ካደረጉ ፖለቲከኞች ከነ ታዬ ደንደአ ጥቂቶች በቀር እምብዛም አልነበረም። አብዛኛው የጮህው አገር ወዳዱ ዜጋ ነው። የዚያ የብዙሃኑ ፖለቲሻን ዝምታ ነው ዛሬ ጁዋር እንዲህ ተንደላቆ ለሌላ ሽብር ሊያዘጋጀን የደፈረው። ስለሆነም ማ ወዳጅና ጠላት እንደሆነ በመጀመርያ እንለይ። በኔ ግምገማ ኮረና እንዲህ ተንሰራፍታብን፣ የግብጽና አባይ ጉዳይ ማእድ አስቀምጠን በዛሬው ጊዜ የአቢይ አስተዳደር ወዳጃችን እንኳ ባይሆን ጠላታችን ከቶውንም ሊሆን አይችልም ። ስለሆነም አገሩን የሚወድ ወገን በሙሉ በመንግስት ላይ የአባይ ጉዳይ እስኪቋጭ እንኳ ተኩስ አቁሙ እላለሁ። አለበለዚያ ግብጽና የህውሃት/ፌዴራሌዎች መዳፍ ውስጥ እንደ መግባት ነው የምቆጥረው። በዚህ ክፉ ወረርሺኝ ዘመን ብዙ የሚያቀራርቡና የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች እያሉ ለምን ጊዜአችንን በከንቱ እንደምናባክን አይገባኝም። ፖለቲካን እንደ ሙያ የወሰዳችሁ በተለይም በእድሜአችሁ የገፋችሁ እንደነ ኦቦ ዳውድና መረራ ሌላው ቢቀር ከየድርጅቶቻችሁ በእድሜ ወጣት የሆኑትን ወደፊት አስቀድሙ እስቲ ። መቼስ እናንተ ዞር ብትሉ ኦነግ ሆነ ኦፌኮ አይሞቱም። ስንትና ስንት አስርተአመታት የሙጥኝ አላችሁበት? ዴሞክራሲዋንም እስቲ እንዲህ አቅሉን አስቷችሁ ከምትጮሁለት ምርጫ በፊት በየጣቢያችሁ ተለማመዱት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ትንሹ›› ተስፋዓለም (ከጽዮን ግርማ)

፫) በወገን ጥሪዬ ክፍል ፬ እንደጠቆምኩት ዖሮምያ አዲስ አስተዳደር ትፈልጋለች። ለምን? የነ ዳውድ፣ መረራ፣ ጁዋር፣ በቀለና የነፍስአባታቸው ህወሃት ጉዳይ አሳሳቢ ነው። እነዚህን የጥፋት ቡድኖች ለመቋቋም ጽኑ መሰረት ላይ የቆመ፣ ዖሮሞነቱ ከመሰረተ ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ያልተጋጨበት/ባት ትፈልጋለች ዖሮምያ። በክፍል አራት ላይ በሰፊው ስለገለጽኩት አልደግመውም።

የኢትዮጵያ አምላክ ይህን ወሳኝ አመት በብልሃት እንድንሻገረው ይርዳን ። አሜን።

4 Comments

  1. ሰሚ ቢገኝ ግሩም ሃሣብ ነው ወንድሜ አባዊርቱ። ሙሌቱ ይለግ በሚለው ግን እምብዝም አልሥማማም በበኩሌ። ይህ የኛ ብቸኛ ጉዳይ ነው። ከኔ ጓዳ ፈልቆ፣ በኔ ሣሎን ተንፈላስሶ ወጥቶ፣ በደጄ አግድም ሄዶ የጎረቤቴን አንጀት የሚያርሥና ጎረቤቴ ሲያሻው በራሱ ግድቦች የሚያጉረው፣ ሲፈልግ ለፈለገው የሚሸጠው የተፈጥሮ ውኃ እኔ እንዳልጠቀምበት የሚያሥገድደኝ አንድም ምድራዊ ኃይል የለም። ፍርሀታችን፣ድህነታችንና ዓለም አቀፉ ፀረ-ኢትዮጵያ አሻጥርና የመሠሪዎች ሤራ አግዶን ለሽዎች ዓመታት የገዛ ሀብታችን ባዕድ አካል ሆነን ስንጃጃል ባጅተናል። አሁን ግን በቃ። ለአባይ እኔ ራሴ ከነ… ልጆቼ እዘምታለሁ – እውነቴን ነው። ፊት መስጠት አይገባም። ዜና ማናፈሥም ተገቢ አይደለም። “በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሌት ይጀመራል…” የሚል ዜና መልቀቅ ለኔ ትልቅ ጅልነት ነው። ሙያ በልብ። የዜናን ምንነትም አለመረዳት ነው። “ግድባችን ሞላ…” ነው እንጂ ዜና የሚሆነው ይህ ዓይነቱ “ዜና” ፣ “(ሽንትሽን) ሥትሸኝ ፈሥ ፈሥ ይልሽ የለም?” እንደሚለው የኣባይ ጠንቋይ የውሸት ጥንቆላ መግቢያ ነው – ሴት ሆኜ አውቄው ሣይሆን ሴቶች ሲሸኑ የተፈጥሮ ግዴታ ሆኖ ይመሥለኛል ፈሢትም በሰበቡ ነፃነቷን ሥለምታውጅና ያም “እውነት” ለጠንቋዩ የማታለያ፣ ለሴቷ ደግሞ ጠንቋዩን በቀላሉ የማመኛ ዘዴ ነው። ጥሩ ምሣሌ የሰጠሁ አልመሰለኝምና መካስ አለብኝ፦ “የውኃ ሀብት ሚንስትሩ ውኃ ለሰው ልጅ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በዐውደ ርዕዩ ለተሣተፉ ባለሙያዎች አብራሩ!” ፐ! እንዴት ያለች ጉደኛ “ዜና” ነች!
    ሣልረሣው – ወንድሜ አባዊርቱ – ለቁልምጫ የማይመች ሥም ሆነብኝ – ክፍል ሦስትና አራትን አላገኘኋቸውምና ካላስቸገርኩ በ ma74085@gmail.com ብትልክልኝ። ስለቁልምጫ ካነሣሁ አይቀር – የትግራዩ ደጃች አርኣያ አንዱ ወዳጃቸው ‘አርዬ’ ብሎ አቆላምጦ ቢጠራቸው “ተው፣ተው በስሜ ብቻ ጥራኝ፤ የኔ ሥም ለቁልምጫ አይመችም” አሉት ይባላል – መቼም ጨዋታ ነውና (‘አገርሽ ወዴት ነው’ እንዳላልኩ ይታወስልኝ) ይቺን የኮሮና ወሸባ እንዲ እየተቀላለድን እናሣልፋት – ካለፍን ሊያውም።

  2. ወንድሜ ጉዱካሣ ! ይቺን ኮረና በፌዝ ብንሻገራትማ እንዴት ባማረልን። ወደቁምነገሩ ስመልስህ በበኩሌ የትራምፕ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ሰውዬው በአለምአቀፍ ደረጃ ብዙ ሃፍረትን ስለተላበሰ የዛ ማካካሻ ነው የሚፈልገው። ማንን ተማምነን ነው ከራሱ የተጣላውን ትራምፕ ጋር የምንላተመው? ቻይናን እንዳትለኝ ብቻ። ሌላው ቢቀር በውስጣችን እንኳ ብዙ ሰላም ስለሌለ የራሳችንን ህዝበ ፖለቲሻኖቹን እንኳ መተማመን አልቻልንም ። ወያኔ የጠፈጠፈልንን ምድረ ፌዴራሌ ይዘው ነው አቢይ ከትራምፕ ሆነ ከግብጽ የሚፋለሙት? እነግብጽስ ይህን እያጠኑ አይደለም ልትለኝ ነው? እውነት ነው ሙያ በልብ ነበር። ከዚህ ቀደምም መክሬ ነበር ይቺን ሙያ በልብ ዘዴ ማ ሰማኝ እንጂ ። እናም ወንድሜ የውስጥና የውጭ ከሃድያን እንዲህ አፍጥጠውብን ይህን ሙሌት እንጀምራለን ብሎ ከበሮ መደለቁ ስላልተመቸኝ ነው። እኔ አቢይን ብሆን ይቺን በአሜሪካ ሸንጋይነት ከግብጽ ድርድርን እያስታመምኩ እስከ አሜሪካ ምርጫ እያሻሸሁ አቆያታለሁ። አንዴ በቴክኒክ ሰዎች፣ ሌላም ጊዜ በድህነት/ሚሊታሪ ሰዎች እያስጠናሁ ነው እያሉ እንደምንም አዝለው ለህዳር/ታህሳስ ቢያበቁ ትልቅ ድል ነው። ይቺ የሙሌቷን ነገር ባየነሷት እንዴት ደስ ባለኝ። የሙሌት ውሳኔውም ከተደረሰ ወቅቱ ሲደርስ ይሻል ነበር። ውስጤ በአገር ፍቅር ቁጭት እየነደደ ነው ይህን የምለው ። ሙሌቱን በእንዲህ አይነት የውስጥና ውጭ ፈተና እያለን መጀመሩ በጭራሽ አላምንበትም። ሌላው የአባይ ጉዳይ ከባድ ብሄራዊ ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ ከወያኔ ውጭ ያሉት ተቃዋሚ ተብዬዎች እንዴት ከጠ/ሚሩ ጎን እንደማይሰለፉ ግራ ያጋባል። እንደማየው ፖለቲካው ለአገር ልኡላዊነት መሆን ቀርቶ አስቤዛ መሸመቻ እቅድ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። በተረፈ የጻፍኳቸው ሁሉ በሳተናውና ዘሀበሻ አሉልህ። ሰላም ለሀገራችን ይሁንልን።

  3. አባ ዊርቱ እንደ ወትሮዉ የሀገሮ ጉዳይ አሳስቦት መጻፎ ድንቅ ነዉ ዛሬ በአጠቃላይ ጽሁፎ ሳይሆን ሙሌቱን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት እርሶ ባሰቡት መልኩ ግብጾች አያዩትም ሙሌቱ መተላለፉ ሊመጣ የሚችለዉንም ችግር አይቀንሰዉም ወይም አያብሰዉም። ነገሩን አልተከታተሉት እንደሆን እንጂ እስከ ትላንት ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ከመጀመሪያ አቋሙ ለግብጽ በተመቸ ሁኔታ እየተሸረሸረ መጥቷል ያ ሁሉ ግን ግብጾችን አንድ ኢንች ልባቸዉን አላራራዉም።

    ግበጾቹ የሚፈልጉት በአባይ ላይ ቬቶ እንዲኖራቸዉ ዉሀዉ አስተዳደር ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲሰጣቸዉና ሌላም ግዴታን አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ ልትጠቀምበትን የዉሀ መጠን ወስነዉልን እንደገና በድርቅ ጊዜ ልንለቅ የሚገባንን በቁጥር አስቀምጠዉልናል። ከዚህ በፊት ” ነገር ሳይበላሺ ቶሎ ቢደርስልኝና ሌላም ጽሀፍ” ልከን ነበር ሰሚ አልተገኘም። ግብጾች እያንዳንዱን ሊጠቅም ይችላል ያሉትን ሲሞክሩ ለምሳሌ የአለም ባንክ/የተመድ/ራሺያ/አሜሪካ/የአፍሪካ ሀጉራትን ሲያካልሉ የኢትዮጵያ መንግስት ኒዉክለር በእጁ እንደለ ጉዳዩን በንቀት ሲመለከተዉ ነበር በመጨረሻም ማን እንደቀሰቀሰዉ አይታወቀም በዘመናዊ ፖለቲካ እዉቀትና ሚና የሌላቸዉን ዘገምተኞችወደ አንዳንድ ሀገሮች ልኮ ምንም ዉጤት ሳያመጣ ቀርቷል ይባስ ብሎ ሰሞኑን የሚሰማዉ ደግሞ ሐይለ ማርያም ደሳለኝ ለዚህ ታላቅ ስራ መመረጡን ስንሰማ ከግብጽ ይልቅ አመራሩ ምን እየሰራ ነዉ ብለን መጠርጠር ይዘናል።

    ይህ በዚህ እንዳለ በምእራብ ያለዉ መከላከያ ሀይላችን በማንኛዉም መልኩ ሀገርን ከዉጭ ጥቃት መከላለከል የሚያስችል ቁመና ላይ ነን ብሎ ለሰጠን ተስፋ ባርሜጣዬን አነሳለሁ። ዛሬ የፖለቲካ ልዩነት የለም ከተመቾት 14/05/2020 ኢትዮ 360 ምናለ ዛሬ ያስተላለፈዉ ዜና ለጋዜጠኞች ትልቅ ምስጋና ያስፈልጋቸዋል ጋዜጠኝነት ማለት ይህ ነዉ። ሀገር አደጋ ላይ በመሆኑ ዜጋ ሀይማኖት/ጎሳ ሌላም ነገር ሳይገድበዉ አመራሩና ህዝቡ አንድ ሁኖ ይህንን ጥቃት እንድንመክት ጥሪ አስተላልፏል። የሚመጣልን ምንም ነገር የለም ትራምፕ ቢሄድ ለዉጥ አያመጣም ተከፋዮቹን ሀገር ቤት አመራሩ ወዲያ አድርጎ ዜጋ ከዉጭም ከዉስጥም ይህንን ጥቃት እንዲመክት ማደፋፈር እንጂ ሸብረክ የሚያደርግ ነገር ዛሬ ብዙም ፋይዳ ያለዉ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ በዘመኗ ለዉጭ ወረራ እጅ ሰጥታ አታዉቅም ይህም ትዉልድ ያንን ያስቀጥላል የሚል እምነት አለን። በመጨረሻም የግብጽ ህዝብ ክርስቲያን/እስላም/አይሁዶች ሲሆኑ ግብጽን በተመለከተ በሙሉ በአንድ ድምጽ ሁነዉ ለሀገራቸዉ ተናንቀዉ ይሞታሉ እኛም ሀገራችንን ለመዉረር ሀብታችንን በሀይማኖትና በሌላ ስም ለመዝረፍ የሚመጣዉን ምንም ሳይገድበን መመከት የዜግነት ግዴታችንን መሆኑን የገባዉ ዜጋ ላልገባዉ ማስረዳት ይኖርበታል።

  4. አቶ ሰመረ፣ ሸብረክማ የሚያደርግ ብዙ ጉዳይ አለ። ዋንኛውና ፊታችን ተጋርጦ ያለው ህወሃት ነው “ምናባታቸው ያመጣሉ” ካላልን በቀር። ፌዴራሌዎቹም ይመስገነውና እስከትላንት ድረስ ህውሀት ጉያ ተሸጉጠው የነበረው እያፈተለኩ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ አሁንም ጥቂት የበቀለ አይነት ቀላዋጮች ህወሃት እግር ስር ናቸው። ተቃዋሚ ይሁን ተጻራሪ ተብዬዎችማ ተኩስ አቁመው በአባይ ጉዳይ አገር ነቅንቅ እምቢኝን ቢያቀነቅኑ ግብጽስ እንዲህ ትዳፈረን ነበር በገዛ ውሃችን? ሌላው ያልተረዱኝ ነገር ትራምፕ ሆነ ባይደን የውስጥ ሰላምንና ጥንካሬያችንን ነው ቀድመው የሚገመግሙት በቀላጤዮቻቸው። አሁን ምን የሚያኮራ ውስጠ ሰላም አለንና ነው “ሙሌቱን ዝንፍ ሳንል በሃምሌ እንጀምረዋለን” የሚያስብል? ለዚህም ነው ዶር አቢይ እያስታመሙ እስከ አሜሪካ ምርጫ ያድርሱልን የምለው። ዋናው ጉዳይ የውስጥ ጥንካሬያችን ቢሆንም በግልጽ ለግብጽ ወግኖ በአሜሪካ ገንዘብ ሚር እጃችንን ለመጠምዘዝ የሚሞክረውን ቅሌታሙን ትራምፕ” ወግድ ወዲያ፣ የውሃችንን ሙሌት መጀመሩን የሚያስቆም ምንም ምድራዊ ሃይል የለም” ማለት ዋጋ እንዳያስከፍለን ከመስጋት ነው። ሌላው እርስዎ “ዘገምተኞች” ያሉዋቸው ዲፕሎማቶች ብቻ አይደሉም እየተፋለሙ ያሉት። ምርጥ አለምአቀፍ አንቱ የተባሉ ያገራችን ምሁራን ከጀርባ ዋልታና ማገር ያሉ ይመስለኛል በቪኦኤ እንደሰማሁት። ይህ የአባይ ጉዳይ ከጅምሩ ወያኔዎቹ ያግማሙትን ነው አቢይ ነፍስ እየዘሩበት ያለው። ምን ያረጋል ታድያ ። አሁንም ቢሆን መቀሌ መሽገውም መች ተኙላት ለዚች ምስኪን አገር? እንግዲህ ይህ ሁሉ እየሆነ የዚህን ሙሌት ጉዳይ ገፋ ማድረግ ብልህነት አይመስሎትም? አለበለዚያማ የኔው ቢጤ ወታደር ዛራፍ ማለቱ ተስኖኝ መስሎት? አያዋጣንምና ነው። እኔ ይልቅስ የምመኘው ይህን የአባይ ብሄራዊ ጉዳይ ከፍተኛ ቦታ ተሰቶት ፣ ምድረ ተቃዋሚ ሁሉ እስከከርሞ ምርጫ የሚባለውን ጉዳይ እርግፍ አርጎ ትቶ ስለ አባይ ብቻ ቢመክርና ቢዘክር ምናልባት ግብጽም እንዲህ አትፈንጭብንም፣ ሱዳንም ሸርተት አትልብንም ነበር። እናም እስቲ በመጀመርያ የውስጥ ወገኖቻችን በዚህ አባይ ጉዳይ በሙሉ ልብ ከጠቅላያችን ጋር ይቁሙ እስቲ። ወያኔዎቹን ሁሉ ተማልጄ ነበር ለህሊናዬ። አሁንም አልመሸም። ልክ አብላጫው ፌዴራሌዎች ህውሃትን እንደከዱ ሁሉ የቀሩትም ቢያደርጉት ትልቅ እርምጃ ነው። ሙሌቱ አይቀር እንደሆን። ወቅቱ ግን ለኛ አመቺ አይደለም ለማለት ነው። ያገራችን ተቃዋሚዎች ምናለ ከኤርትራ ተቃዋሚዎች ቢማሩ እላለሁ አንዳንዴ። ኤርትራውያን ድንቅነታቸው የሚገርመኝ ኢሳያስን እየጠሉ እንኳ በአገራቸው ጉዳይ የሚያስደምም ህብረት ይፈጥራሉ። ባለፈው ለህዝባቸው ገንዘብ ሲያሰባስቡ እንኳ በሁለት ሳምንት 3 ሚሊዮን ዶላር ከአሜሪካ ብቻ ያዋጡ ጀግኖች ናቸው። ለህዝባቸው ሲቆረቆሩ ኢሳያስን አይደለም የሚያዩት ወገናቸውን እንጂ። ባለፈው አመት ያንን ሁሉ ህዝብ ይዘን ለዲያስፖራው ፈንድ ያዋጣናት ሁለት ሚሊዮን እንኳ አልደረሰም። ይቅርታ ያድርጉልኝ ኢትዮጵያውያን ባብላጫው ወሬኞች ነን። ክፉዎችም ጭምር ። ወያኔዎቹ ደግሞ ከክፋትም በላይ ናቸው። ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልን ብቻ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.