“የአማራ ህዝብ ትግል በዱላ አይፈታም”   አስቻለው መኮንን

ይድረስ ለዶ/ር አብይ አህመድ እንዲሁም ጀሌዎቻቸው

ሰላምና ፍቅር ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሆን እየተመኘሁ፡፡ ሃገራችን አሁንም ባልጠራ የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ መሆንዋ እና እንደ ሃገር ለማስቀጠል ህልውናዋን የሚያስጥብቅላት ባለመኖሩ ዳግም አሳዛኝ ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን፡፡ በዚች አጭር ፅሁፍ ማስተላለፍ የፈኩትን ያህል ባይሆን ከብዙ በጥቂቱ ይህን መልዕክት ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

abiy ahmedጠቅላያችን እነሆ የመንግስትን ሥልጣን ከተቆናጠጡበት ሰዓት ጀምረው የቀድሞውን ስርዓት በመዝለፍ የግል ተወዳጅነትን እንደተጎናጸፉ ምስክር መቁጠር አያሻንም፡፡ የለውጥ አመራር ነን ብለው ከተሰየሙበት ቀን እና ሰዓት ጀምሮ በግል ድርሳናቸው ስብከት ፣ መርህ አልባ በሆነው የአመራር ሰጭነት ሚናቸው የኦሮሞን ብሔር የበላይነት ለማረጋገጥ አበክረው እየሰሩ እንደሆነም እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን፣ የጋራ ተጠቃሚነታችንን ከማያረጋግጥ ፣ ከምላስ በዘለለ ሃገራዊ አንድነት ከማይመኝ መሪ ጋር በአንድ ጠረጴዛ የመቀመጥ ፍላጎት አይኖረንም፡፡ ለውጥን ሲናፍቅ ለነበረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ይዘው እንደ ሐይማኖት መሪ በቀኝ ምላስዎ ፍቅርና ሰላምን እየሰበኩ በግራ ምላስዎ የኦነግን እንቀስቃሴና አሰላለፍ እየመሩ ፣በጓሮ በር የግል አጀንዳዎ የሆነውን የኦሮሞን የበላይነት ይዘው በማን አለብኝነት እየተንቀሳቀሱ እንዳሉም መረዳት አዳጋች አይሆንብንም፡፡ በተደጋጋሚ ያለፈውን ስርዓት ሲዘልፉት የነበረ ቢሆንም የተሻለ አመራር ለመስጠት ግን የያዙት የኦሮሞ ብሔርተኝነት አጀንዳ በእጅጉ እየተፈታተንዎ እንደተቸገሩም  ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ በመድረክ ትወና የተዋጣልዎት መሪ መሆንዎን ልብ ይሏል፤ ይህንን ለግል ጥቅምና የስልጣን ጥማት የቆመውን እንቅስቃሴዎን ሃገራዊ ራዕይ ያለው ሰው ለመገንዘብ እንደም ይሳነዋል?

እስካሁን ባለው የስልጣን ዘመንዎ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የህዝብን ይሁንታ የሚጠይቁ ፣ ብሄራዊ ማንነትን የሚገዳደሩ ታሪክና ባህልን  የሚያጠለሹ፣ በአጠቃላይ ከብሔራዊ ማንነታችን ነጥቀው የሚያወጡ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ  በስልጣን መቀጠል እንደምን ይቻል ይሆን?  በዚህ ኃፍረተ- ቢስ አድራጎትዎ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በኦሮሞ የበላይነት፣ በገዢና ተገዢነት መንፈስ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በማጨለም ከግል ራዕይዎ ብቻ በመነሳት የኦሮሞን ህዝብ የበላይነት ለማንገስ መሯሯጥዎት ትልቁ ሽንፈት እንደሆነም ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ላላፉት ሃያ ዘጠኝ አመታት አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጨምሮ ከቀድሞው ስርዓት የተሻለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ሰሩለት? ጉልቻ ቢቀያየረ ወጥ አያጣፍጥም – በመሰረታዊነት ትልቁ አጀንዳችን የሆነውን ህገመንግስትን የማሻሻል ጥያቄ ያልመለሰ የለውጥ አመራር ሊባል እንደምን ይቻል ይሆን? አሁንም ከቀድሞው ስርዓት እንዳልተላቀቅን እና በሌላ አቅጣጫ እየተዘወርን እንደሆነ በአለም ሁሉ ቋንቋ ላስረዳዎት ብችል ደስ ባለኝ ነበር፡፡ በየጊዜው የግል ድረሳንዎን በመምዘዝ የኢትዮጵያን ህዝብ እንዳሻዎት እያሽከረከሩት በመሪ ተዋናይነት የቅዠት ልብወለድዎን ይዘው በመሰየም በባዶ ተስፋ ለውጥን ሲናፍቅ የኖረውን ህዝብ መና እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም የከፋው ግን በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ የጀመሩት ዘመቻ ነው፡፡ በዚህ ወቅት “ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ከመሞት በላይ አስፈሪው ጊዜ አሁን ነው”፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደሃ አይደለንም ፣ ደሃ ለመሆንም ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ደሃ ማለት ቢያንስ በድህነት ወለል ላይ የሚኖር ገቢው በቀን ከ ($2) ሁለት ዶላር ያላነሰ ነው ይለናል፡፡ በመረጃ እና በማስረጃ ከተማመንን ከዚህ በታች ያሉትን ፍፁም ደሃ ይላቸዋል (Global Extreme poverty) ድህረ ገፅ ፣ ወደ ሃገራችን መረጃ ስንመለስ   ምን ያህል ኢዮጵያውያን ናቸው በዚህ ሰዓት በቀን 60 ብር ገቢ ያላቸው?

በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በመጀመሪያ ደሃ የሚያደርጋት ከዛም ከድህነት የሚያላቅቃት መሪ እንጂ እንደ ሞዴሊስት ዙሪያውን እየዞረ ከሰው በታች መኖራችንን በስመ ብልፅግና የሚያራግብልን መሪ አይደለም፡፡ ለጋብቻ እንደምትታጭ እንስት ፣ በየግብዣው ቃል እየገቡ በቀን አንዴ መብላት የተሳነውን ህዝብ ከጫማዎ ሶል በታች አይርገጡት፡፡ እርስዎ በሚያራምዱት ድብቅ ተልዕኮ በዚሁ የለውጥ ሂደት ነው ፣ ብዙዎች ታፍነዋል ፣ ተገድለዋል ፣ ከቀዬ ከመንደራቸው ተፈናቅለዋል ፣ ተሰደዋል ፣ መኖርን እየናፈቁ ፣ ማደግን እየተመኙ በወጡበት የቀሩት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አንዳችም ስሜት አይፈጥርበዎትም ምክንያቱም የመንግስትዎ አጀንዳ አይደለምና፡፡ ይልቁንም ቀድሞ የነበረብዎትን የኦሮሞ የበታችነት ስሜት በኢትዮጵያዊነት ጭምብል እያስተነፈሱ ወደ ግል ራዕይዎት ግስጋሴውን ተያይዘውታል፡፡ በብሔራዊ ማንነታችን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ላይ የያዙት የጥፋት ዘመቻ ግን የትም እንደማያደርስዎ ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት – ለዘመናት ታሪካዊ ድልን የተጎናፀፍንበት የአርበኝነት መጠሪያችን፣ ማንነታችን ብሎም የአንዲት ኢትዮጵያ፣ የመላው ህዝብና መንግስት መጠሪያም ጭምር ነው፡፡

ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮም ለኢትዮጵያዊነት አጥብቆ በሚታገለው የአማራው ህዝብ ላይ የያዙት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለነገ የማይባል በቅርቡ መፈንዳት ያለበትም የተሸከርካሪ ጎማ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በጨዋታው ሜዳ ላይ የያዙትን ወንበር እንደ እርሰዎ አጠራር ከ”ቀን ጅቦች” ቀምቶ ያቀባበለልዎት የአማራ ትከሻ እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን አይዘንጉት፡፡ ዳሩ ግን መጨረሻው ባጎረስኩ ተነከስኩ ሆነና ፣ ሽርፍራፊ የለመዱ አድርባዮችን ተገን አድርገው ተቀናቃኝ አይኑረኝ ሲሉም በአማራ ህዝብ ላይ ከጫፍ እስከጫፍ ዘመቱበት ፣ ይሁን ግዴለም – የሚገርመው ግን የአማራ ህዝብ ትግል በዱላ አይፈታም! ፤ ለኦሮሞ ነፃነት የአማራ ህዝብ ደሙን መገበር አለበት ካሉን በመጀመርያ የመደመር የፖለቲካ እሳቤዎን ቢቀይሩት መልካም ይሆናል፡፡ የምንደመረው ለእርስዎ አጀንዳ ወይንስ ለሃገር አንድነት? በስልጣንዎ ማግስት አንፀባራቂ ከነበሩት ንግግሮችዎ መካከል ፤ መግደል መሸነፍ ነው! አሸባሪዎቹ እኛ ነን ብለውንም ነበር፡፡ ኡሁንስ? የአማራን ህዝብ የፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረገው ማነው? ነፍጠኛ እያለ የሚያሳድደውስ ማነው? በልማት ሰበብ የአማራን ስብስብ ከቀየው ፣ ወልዶ ከከበረበት መሬቱ ማፈናቀሉስ የማን ሥራ ይሆን? በአዲስ አበባ እና በዙርያው ያሉስ ነዋሪዎች የንብረታቸው መውደም፣ የመፈናቀላቸው ሚስጥርስ? የመደመሩ ስሌት ተገልሎ ነበር ብለው ለሚያስቡት የኦሮሞን ህዝብ ወደ ኢትዮጰያ ህዝብ መደመርም ይመስላል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የሌሎችን ህልውና ማሳጣቱ ፍልስፍናዎን ፉርሽ ያደርዋል፡፡ እያንዳንዱን የጥፋት ዘመቻ መንግስትዎ እየመራ ባለበት ሁኔታ እያጣራን ነው እምናስረው በሚል መርህ ባላየ ባልሰማ የንፁሃን ደም ሲፈስ መታለፉ የመንግስት እውቅና የተሰጠው ድርጊት እንደሆነ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡ አጣርተን ነው የምናስረው የምትለው ዓረፍተ ነገር ፣ ክሱ የህዝብ ሲሆን ለማለት ይሆን? የመንግስት ከሆነ ግን ባይጣራም እንኳን ማሰር ግድያንም ይጨምራል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ህዝብ ላይ የቱንም ጦር ቢያዘምቱ ፤ የቱንም ያክል አፈናና ጭቆና ቢበረታም ግን አንድነታችንን አጠናከረን በፋኖነት ነፃ የአማራ ክልላዊ መንግስት ፣ በብሔር ጥቅም ላይ ያለተመሰረተች አዲስ አበባን እንዲሁም ታሪክና ባህልዋን የጠበቀች ታላቋን ኢትዮጵያን በመገንባት ኦሮሞም በማንነቱ ተከብሮ የሚኖርባት ኢትዮጵያ እንድትሆን ግን እንሰራለን፡፡

ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለእርስዎ የእግር እሳት የሆነብዎት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ድል የሆነውን ሕገ-መንግስት የማሻሻል ጥያቄ ለምን አመመዎት? እውነት እንዳሉት ወጪውን ፈርተው ነው? ሕገመንግሰቱን የማሻሻል ጥያቄዎችስ ለምን ታፈኑ? ፍራቻዎ ምን ይሆን ስል ራሴን ጠየኩ፣ ነገሩ ወዲህ ነው፣ ባለፈው የኦሮምያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ተመለከትኩት፡፡ በዚህ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ያደረጉት የህገመንግስቱን አንቀፅ 49 (5) ነው፡፡ እውነትም ሕገ-መንግስቱ ለእርስዎ ጉዳይ ማስፈፀሚያነት ጥብቅና የቆመ ስለሆነ በአግባቡ ይጠቀምዎታል ፣ ስለዚህ ሰለመቀየሩ ባይወራም ደስ ይልዎታል፡፡ ይህንኑ አዋጅ ተከትሎ በአዲስ አበባ እምብርት የኦሮምያን ዋና መስሪያቤት ሊያስገነቡም እንደሆነ ሰምተናል ፣ በ700,000,000.00 ብር (በሰባት መቶ ሚሊዮን) ብር፡፡ ግልፅ ነው ሕገ መንግሰቱ ቢሻሻል የኦሮሞን በአዲስ አበባ ያለው ጥቅም ለማስጠበቅ የተደነቀረው አንቀፅ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል እስከዛው ቶሎ ቶሎ ቦታ እንያዝ የሚለው የእርስዎና የጀሌዎችዎ ሴራ እንደሆነ አዲስ ለተወለደ ህፃንም ግልፅ ነው፡፡ በእውነቱ ቤተመንግስት ቀለም ከመቀባትና ህገመንግስትን ከማሻሻል የትኛው የህዝብን ጥያቄ ይመልሳል? በዚህ ሰዓት ጦርነትዎ የአማራን ኮቴ ማጥፋት እንጂ ሃገራዊ ራዕይ እንደሌለዎትም ግልፅ ነው፡፡  የአባቱን ታሪክን የሚያጠፋ እርሱም ይጠፋል፡፡

ድል በመላ ሃገራች ለምትገኙ እንዲሁም በመላው አለም ላላችሁ የአርበኛ ፋኖዎች በሙሉ ይሁን፡፡

ፀሀፊ ፡  አስቻለው መኮንን
ከምድረ አውሮጳ

1 Comment

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.