ሰውዬውና ግለሰቡ – መሳይ መኮነን

Mesay mekonen
መሳይ መኮነን

ሰውዬው እረፍት የለውም። ሀፍረትም አልፈጠረበትም። ፖለቲካዊ ሞቱን ከጨለጠም በኋላ ነፍሱ ላለፉት 15 ዓመታት ስትቃትት ከርማለች። በትንሳዔ ለመነሳት ተንከራታለች። እዚህም እዚያም ረግጣለች። ያልቧጠጠችው ዳገት፡ ያልወጣችው አቀበት፡ ያልወረደቸው ቁልቁለት የለም። ይሁንና በፖለቲካዊ ሞት የጠፋች ነፍስ ትንሳዔ የላትም። በእርግጥ አንዳንድ ሚዲያዎች ሰውዬው ነፍስ እንዲዘራ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ከፖለቲካ ሞት ልሶ እንዲነሳ ያላቀረቡለት አፈር የለም። ብዙ ሞክረዋል። በሀገር ቤት ከሚሰራጩት አንስቶ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት ከሚተላለፉት የግል፡ የፓርቲና የመንግስት ሚዲያዎች ድረስ የዘለቀ፡ የሰውዬው ፖለቲካዊ ሰውነት ሞቶ ከተቀበረበት ጥልቅ ጉድጓድ ፈንቅሎ በማውጣት እስትንፋስ ዘርቶ ዳግም የፖለቲካው ተዋናይ እንዲሆን አያሌ ሙከራዎች፡ ጥረቶች ተደርገዋል። ግን አልተሳኩም።

በምርጫ 2002 ከሌላው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ አቅም፡ ጠንካራ የፖሊሲ ሀሳቦችን በመሰነቅና የህወሀትን አገዛዝ እርቃን ያጋለጡ ክርክሮችን በመያዝ ወደ መድረኩ ቢመጣም ያጣውን ተቀባይነት፡ የተነጠቀውን ክብር መልሶ ሊያገኘው አልቻለም። ህዝብ ከሰቀለህ ሰቀለህ ነው። ፈጥፍጦ ከጣለህ ግን መቼም አትነሳም። ሰውዬው ዘንድሮም ፖለቲካዊ ሞቱን በትንሳዔ ድል ለመንሳት እድሉን እየሞከረ ነው። ውጤቱን እያወቀው ገብቶበታል። መስከረም 30 የትንሳዔው ማብሰሪያ ዕለት ይሆንለት ዘንድም ቀጠሮ አሲዟል። ይሳካለት ይሆን?

ግለሰቡም ከገጠመው ፖለቲካዊ ስብራት ለማገገም በተቆራረጠ ትንፋሽ አለሁ ሲል ከሰሞኑ በሰፊው ተከስቷል። የዘር ፖለቲካን ወደስልጣን መወጣጪያ አቋራጭ መሰላል አድርጎ በመጠቀም ተወዳዳሪና አቻ ያልተገኘለት ነው። ከሰውዬው አንጻር የፖለቲካ ልምዱና እድሜው አነስተኛ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ቆይታው በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ጎልቶ ለመታየት እድሉን አግኝቷል። የዘር ፖለቲካ ማማ ላይ ከሰቀላቸው ሰዎች አንጻር ግለሰቡ የተሻለ ተቀባይነትን አግኝቷል። የማህበራዊ ሚዲያው ክስተት ደግሞ ተሰንፈጥሮ ከላይ ጉብ እንዲል ትልቅ ባለውለታው ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በማደፍረስ፡ ከሀሳብ ፍትጊያነቱ ይልቅ የዘርና አጥንት ቆጠራ ላይ የተቸነከረ እንዲሆን በማድረግ ሚናው ቀላል የሚባል አይደለም። ብዙ ጥሯል። በብዙም ለፍቷል። ከአናት ላይ ለመፈናጠጥ አመጽን መንገዱ፡ ጥላቻን ትጥቅና ስንቁ አድርጎ በሰፊው ተንቀሳቅሷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰሞኑ ህወሃት ሕዝቡን አቅጣጫ የሚያስቀይስበት ዘዴ ከሽፏል ወይስ አልከሸፈም? - ከአንተነህ ገብርየ

ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ ግለሰብ ጥሪ አያሌ ነፍሶች ተቀጥፈዋል። ሰላማዊ መንደሮች የሁከት መናሃሪያ እንዲሆኑ ተደርገዋል። እሱን የሚመስሉ፡ የሱን መንገዱ የሚከተሉ አማተር የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች እንደአሸን እንዲፈሉ አድርጓል። በእርግጥ እንዳሰበው እንደምኞቱ አልሆነለትም። የሞከራቸው እድሎች ብዙዎቹ ጨንግፈዋል። የወረወራቸው ሰይፎች ዶልድመዋል። ክንፉ ተመቶ፡ የማትሞተዋን ምላስ ብቻ ይዞ ቀርቷል። በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማንሰራራት ያደረጋቸው ሙከራዎች ጉልበት ሆነው አላቆሙትም። አሁንም ወደፊትም እያንዳንዷን አጋጣሚ ከመሞከር ወደ ኋላ እንደማይል ጠላት ወዳጆቹ የሚያውቁት ማንነቱ ነው። ሰሞኑንም ቀና ሊያደርገኝ ይችላል በሚል አንድ አጀንዳ ይዞ ተነስቷል። መስከረም 30 እንገናኝ እያለ ነው። ይሳካለት ይሆን?

ሰውዬውና ግለሰቡ በብዙ ነገሮች ይለያያሉ። በብዙ ባህሪዎቻቸው ይመሳሰላሉ። ስለኢትዮጵያ ባላቸው ዕይታ አራምባና ቆቦ ተቀምጠዋል። በፖለቲካ ግባቸው ሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች ላይ ረግጠዋል። የታሪክ መረዳታቸው ፈጽሞ አይገናኝም። በኢትዮጵያ እድል እጣፈንታ ላይ አቋማቸው ለየቅል ነው። ፌርማታቸው የተለያየ ነው። መዳረሻቸው ከአንድ ቦታ አይደለም። በባህሪ ግን የአንድ እናት ልጆች ናቸው። ፖለቲካውን መሳሪያ አድርገው ውስጣቸው የሚንተከተከውን የስልጣን ጥማት ለማርካት በሚሄዱበት ይሉኝታ ያጣ መንገድ ላይ ተገናኝተዋል። ሲበዛ ብልጣ ብልጥ ናቸው። መገለባበጥን የፖለቲካ ታክቲካቸው አድርገውታል። እንደገበያው ሁኔታ ዋጋቸውን የሚለኩ፡ እርምጃቸውን የሚመትሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የአክሮባቲስቶች ትዕይንት ነው ከተባለ ከመሪ ተዋናዮቹ ሰውዬውና ግለሰቡ በመጀመሪያው ረድፍ የሚሰለፉ ይሆናሉ። ስለራሳቸው ያላቸው ግምት አይጣል ነው። ከፊት የሚቀድማቸውን አይፈልጉም። በልጦ የተገኘ ሰው ክፉ ጠላታቸው ነው። ከኋላ የሚከተላቸው እንጂ ከፊት የሚመራቸው እንዲኖር አይፈቅዱም። ሁሌም አንደኛ፡ ምንግዜም መሪ መሆንን አጥብቀው የሚሹት፡ ነፍሳቸው የምትቃትትለት አቋማቸው ነው። በፖለቲካ ግብ ቢለያዩም በፖለቲካዊ አካሄድ መስመራቸው አንድ ነው። የሚፈልጉትን ለማግኘት የትኛውንም መንገድ ለመጠቀም ወደኋላ የማይሉ ናቸው። በእነሱ መስዋዕትነት ሀገር ከምትድን፡ ሀገር መስዋዕት ሆና እነሱ ለስልጣን ቢበቁ የሚመርጡ ለመሆናቸው የሚጠራጠር ካለ የዋህ ነው። እንግዲህ እነዚህ የባህሪ መንታ ወንድማማቾች፡ የአንድ እናት ልጆች ሰሞኑን በአንድ መድረክ ተገናኝተዋል። በአንድ ድምጽ፡ በአንድ አቋም የጊዜ መቁጠሪያ ሰሌዳችን ላይ መስከረም 30ን እንድናከብ ጥሪ አድርገውልናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያጽድቁ ወይም ይሻሩ

መስከረም 30 ምን አለ? የኢትዮጵያ ምጽአት ቀን፡ ወይስ ትንሳዔዋ የሚበሰርበት? ሰውዬውና ግለሰቡ መስከረም 30 ያሲያዙን ቀጠሮ መዓት የሚወርድብን ወይስ ወለምታችንን ታሽተን ጭንቀታችንን የምንሻገርበት? ሰውዬው ከመስከረም 30 በኋላ ዶ/ር አብይ በስልጣን ከቀጠሉ እንተያያታለን ዓይነት ከዛቻ የሚጠጋ መልዕክት አድርሶናል፡፡ ግለሰቡም ከመስከረም 30 በኋላ መከላከያው፡ ፖሊስሱና የጸጥታ ሃይሉ ለዶ/ር አብይ አይታዘዙም እያለ አመጽ በአቋራጭ ጠርቷል። የሁለቱም መነሻ ህገመንግስቱ መሆኑን ይነግሩናል። ሀገመንግስቱን ስንፈትሸው፡ አንቀጽ በአንቀጽ ስንበረብረው፡ በመስመር መሃል የተሰወረ መልዕክት ይኖረው እንድሁ ብለን ስንመራመረው የሚሉትን ነገር ልናገኝ አልቻልንም። ለስልጣን ጥማት ነፍሳቸው ብትራብም በዚህ ደረጃ ተከታዮቻቸውን ያደናግራሉ ብዬ አልጠበኩም። የህወሀት የፕሮግራም ሰነድ ስለሆነው ህገመንግስት ባይተዋር ይሆናሉ ብዬ ባልጠብቅም አዛብተው የአመጽ ጥሪ ማድረጋቸው ግን አልደነቀኝም። ሀገመንግስቱን ወይ አላነበቡትም፡ አልያም በቅጡ አልተረዱትም፡ ወይም ደግሞ ሆን ብለው ለሚፈልጉት የፖለቲካ መስመር መጠምዘዙን መርጠዋል። ለአብነትም ሰውዬው የህገመንግስቱን አንቀጽ 9 ቁጥር 3 ሲጠቅሰው መሰረታዊ መልዕክቱን እንዲፋለስ ማድረጉ የመስከረም 30ዋ ጥሪ አንዳች ቀውስ ፍለጋ እንደሆነች ለመረዳት የሚያስችል ነው። በዚህ አንቀጽ ላይ የፖለቲካ ስልጣንን በሃይል ስለመያዝ የሚከለክለውን ድንጋጌ ሰውዬው ”ስልጣንን አላግባብ ለማራዘም አይቻልም” በሚል ተርጉሞ ማቅረቡ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳውን የሚያጋልጥ ይመስለኛል።

ሰውዬውንና ግለሰቡን ህገመንግስቱን ይዞ በእውቀትና በእውነት የሚሞግታቸው መድረክ ቢኖር እርቃናቸውን መጋለጣቸው አይቀርም። በመንግስት በኩል የቀረቡት አራቱ አማራጮች የየራሳቸው ጥቅምና ጉዳት ቢኖራቸውም አሁን የተፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችሉ አይደሉም፡ ዝግ ናቸው ብሎ መከራከር ግምት ላይ የሚጥል ነው። በግሌ ይህ የሀወህት የፖለቲካ ሰነድ የሆነው ህገመንግስት በራሱ የኢትዮጵያ ችግር እንጂ ችግር መፍቺያ ፍቱን መድሃኒት ነው የሚል እምነት የለኝም። በሂደት፡ በውይይትና በህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በህገመንግስቱ በክፋትና በተንኮል የታጨቁ አንቀጾች ተወግደው ሁላችንም የምንስማማበት የቃልኪዳን ሰነድ እንዲዘጋጅ ፍላጎቴም ተስፋዬም ነው። ይህ ማለት ግን አሁን ለተፈጠረው ክፍተት ህገመንግስቱ ምንም መፍትሄ አይሰጥም ማለት አይደለም። የህገመንግስት ባለሙያዎችና የህግ አዋቂዎች እንደሚሉት አማራጮቹ ከበቂ በላይ መውጪያ መንገድ የሚሰጡ ናቸው። በአማራጮቹ ላይ ተወያይቶ የሚሻለውን ተግባራዊ ማድረጉ ላይ የነቃ ተሳትፎና አስተዋጽኦ ማድረግ እንጂ ህገመንግስቱ ውስጥ የሌለ አንቀጽ እየፈለጉ አመጽ መጥራት ሃላፊነት የጎደለው በህግም የሚያስጠይቅ ወንጀል ይመስለኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  (የላጲሶና የተክሌ ጉዳይ) ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ፤ ወይ ጣፍጠው ወይ መረው ታገኟቸዋላችሁ (ጌታቸው ኃይሌ)

ሰውዬውና ግለሰቡ ለምን ይሄን መንገድ መረጡ ለሚለው መልሱን በሚገባን ልክ ሊገባን ይችላል። በአንድ ነገር ግን ሁላችንም የምንስማማ እንደሆነ አስባለሁ። የሰውዬውንና የግለሰቡን የኋላ ታሪክና በፖለቲካው ረዥም ጉዞአቸው ወጥተው የወረዱባቸውን ጥልፍልፍ መንገዶች በሚገባ ለሚያውቅ ህገመንግስቱን አስታኮ ከተላለፈው ” መስከረም 30 እንገናኝ” ጥሪ ጀርባ ምን እንደተደገሰ የሚሸተው ነገር እንደሚኖር አልጠራጠርም። በመንግስት በኩል የቀረቡትና በህገመንግስቱ በኩል የማርያም መንገድ የሚሰጡት አማራጮች ለሰውዬውና ለግለሰቡ ፈጽሞ ሊዋጥሏቸው ያልቻሉት ወደስልጣን ሊያመጧቸው የማይችሉ የተዘጉ በሮች ስለሆኑ እንጂ የተፈጠረውን ክፍተት የማይደፍኑ ዝግ መንገዶች ሆነው እንዳልሆነ እነሱም ያውቁታል። የሽግግር መንግስት ለእነሱ አቋራጭ የስልጣን መወጥጪያ መሰላል ስለመሆኑ ያልተረዳን ከመሰላቸው ተሳስተዋል። እዚያው መድረክ ላይ በብዙ ጉዳዮች መስማማት ያልቻሉት ሰውዬውና ግለሰቡ በሽግግር ስም አንድ መንስግት ውስጥ ወንበር ቢያገኙ ሀገሪቱን እንዴት እንደሚያምሷት፡ እንዴት እንደሚያፈርሷት ከወዲሁ ያልታየን ከመሰላቸው በእርግጥም የፖለቲካ ቂል እንጂ አዋቂ አያደርጋቸውም።

ሆነም ቀረም መስከረም 30 ምንም የለም። እንደማንኛውም ቀን ሆኖ ያልፋል። ሰውዬውና ግለሰቡ እንደከዚህ ቀደሙ ሙከራቸው የመስከረም 30ውም ከሙከራ ሳይዘል፡ ኢትዮጵያን ከጭንቀት የሚያሻግራት ቀን ይሆናል። በግርግር ስልጣን ለማግኘት ሰውዬው የሄደበት ርቀት መጨረሻው ሌላ ዙር ፖለቲካዊ ሞት እንጂ ትንሳዔ ሊያስገኝለት አይችልም። የተሰበረውንና ዱሽ ሆኖ የቀረውን ክንፍ በመስከረም 30 ለማስቀጠል የሚደረገው የግለሰቡ የሞት ሽረት ትግልም መጨረሻው ከርቸሌ እንደሚሆን አልጠራጠርም።

3 Comments

 1. መሳይ አሁን ምን ዳር ዳር ያሰኛል ሰዎቹ ጁዋር መሀመድና ልደቱ አያሌዉ ማለት ምን ያስፈራል ዲሞክራሲ አለ ተብላችሁ እናንተም አምናችሁ ገብታችሁ የለ? መስከረም አበራ ስዩም… ሌሎችም የህዝብ ጋዜጠኞች በጣም የምናከብረዉ ታምራት ነገራ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀዉ እዉነትን ይናገራሉ እናንተ ለእንጀራዉ ያደረ ጋዜጠኛ ሆናችሁብን እኮ።
  ጁዋር መሀመድ የፖለቲካ ተንታኝ ወጣት ምሁር ሌላም ሌላም እያላችሁ በ ኢሳት ሰቱዲዮዋችሁ ቀይ ምንጣፍ አንጥፋችሁለት ኢትዮጵያን እና አንድነትን ሲሰደብልን ነበር እሱን/ሌንጮን(ለታ/ባቲን)/ዲማ ነገዎ ይቀየማሉ እያላችሁ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሸፍናችሁ ስታስተናግዷቸዉ ነበር አረ ማን ቀረ?
  ልደቱ አያሌዉን በተመለከተ እሱም ጠነኛ ባይሆንም ከናንተ አለቃ ጋር አይንና ናጫ በመሆናቸዉ ቀላቅለህ ስትመታዉ ነዉ እንደዉም ይሻል የነበረዉ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን ከልደቱ አያሌዉ ጋር ለማንም ሳታደላ በፕሮግራምህ ብታስተላልፍ እኛም ተጠቃሚ እነሆን ነበር በተረፈ አትፍራ ስማቸዉን ጥራቸዉ የሚያስፈሩ ሰዎችም አይደሉም ሁሉም ነፍሶባቸዋል። መስከረም አበራን አታያትም ስትለበልባቸዉ። እናንተ እዉነትን በጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ለህዝብ ከማቅረብ ከፖለቲከኞች በላይ ጎራ ለይታችሁ ትጨፋጨፋላችሁ ያልታደለች አገር። ጁዋር መሀመድ/ህዝቅኤል ጋቢሳ/ጸጋዬ አራርሳን ይቅርታ ጠይቁ ሳትል ሐይሌ ላሬቦን ቀስፈህ ይዘህ አስፈራርተህ ይቅርታ ጠይቅ ትላለሀ ይገርማል ሁሉም አለፈ። አይ የኢትዮጵያ አምላክ እባካችሁን እስክንድርን እነኳን ተዉት።

 2. መሳይ ልደቱን ለመተቸት የሞራል ብቃቱ አለህ ።አስመራ የግንቦት ሰባትን ጦር ጉብኝት ሄደህ፣ የ ታጋይ ቱታ ለብሰህ፣10 ሺ የሰለጠነ ጦር አለህ ብለህ ውሸት ስትመዘግብ ፣እኛም በባዶ ተስፋ ሆዳችን ሲነፋ፣ኪሳችን ሲራቆት ፣ዛሬ እውነቱ ያንተን ቀጣፊነት የሚመሰክር ነው። የሚገርመው ሐቀኛ ትግል አለ መስሏቸው ወደ አሥመራ ያቀኑ ጓደኞቻችን ዛሬ ተመልሰው እውነቱን ሲነግሩን፣የተባበሩት መንግስታት ለመቋቋሚያ የላከላቸውን ገንዘብ ሳይደርሳቸው እንደቀረ፣ምናልባት አለቃህ ብርሃኑ ነጋ በልቶት እንደሆን ጠይቅላቸው። “እነ ልደቱ ሕገ መንግስቱን ይዞ በእውቀትና በእውነት የሚሞግታቸው መድረክ ቢኖር እርቃናቸውን መጋለጣቸውን አይቀርም” ብለሃል። ደሞዝ ከፋይ ብርሃኑ ለብዙ ግዜ ከልደቱ ጋር ለውውይት ተጋብዞ ፈቃደኛ ያለመሆኑ በኢትዮጵያው ፖለቲካ እውቀትም እውነትም የሌለው በምሆኑ ብቻ ነው።ዛሬ ለውውይት ልደቱን ቢገጥም እራቁቱን እንደሚሮጥ አረጋግጥልሃለው። ያኔ ደሞ በአለቃህ ትዕዛዝ ልደቱ እራቁቱን ተሸነፈ ብለህ በወረቀት ላይ እንደምታገሳ እርግጠኛ ነኝ።
  የተጀመረው የአሳብ ፍጭት እንዳይጎለምስ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው።ውይይታችን፣ ንትርካችን ሕገ መንግስቱን በሚመለከት እልክ አስጨራች ሙግት ማድረግ ሲገባን፣ተሟጋቹን አንገቱን በነገር ማነቅ በሌላው ተሟጋች ላይ ፍርሃትን ስጋትን ፣መሸማቀቅን ይፈጥራል።
  ዛሬ በልደቱ ላይ የሚደረገው ዘመቻ በሃሳቡ ላይ አይደለም። ይህንን ሃሳብ በተለያየ መገናኛ አንስቶታል።ዘመቻው” እንዴት ሆኖ ነው ከጅዋር ጋር ውይይት የምታደርገው፣ጁዋር የኢትዮጵያ አንድነት በታኝ ነው፥ ጠላት አምባ ምን ወሰደህ “የሚለው የኢትዮጵያ ወገን ቁጣ ነው። በልደቱ በኩል ስህተቱ ለጁዋር የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን ያላመዛዘን ሲሆን ፣የዚን አይነት ውይይት ከብርሃኑ ነጋ ጋር ቢሆን እንዲህ ባለ ውዝግ ውስጥ ባለገባ።

 3. Those who you say do not understand your so called constitution actually understand it very well. I can see from your writings that you think the so called constitution is ok. All evil flows from the constitution and those you mention are just applying it. You should come out and in good Ethiopian fashion blame the constitution. And also tell your boss Berhanu the same. No good will come out of the so called constitution. I urge you not to be a sell out in complete agreement with the comments above.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.