የኢትዮጵያ መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በመጠቀም እየተወሰደ ያለውን ያልተገባ የሃይል እርምጃ ያቁም

Justiceበአሁኑ ግዜ ዓለምን እያስጨነቀ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ የሰው ዘር ለከባድ አደጋና ችግር የተጋለጠበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ከዚህ አንጻር፣ የተለያዩ ሃገራት ዜጎቻቸውን ወረርሽኙ ከሚያስከትለዉ አደጋ ለመጠበቅ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ መንግስትም፣ ልክ እንደሌሎች መንግስታት፣ ወረርሽኙ በሀገሪቱ ከተከሰበት ግዜ ጀምሮ እርዳታ ከማሰባሰብ፣ እስከ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማዉጣት እርምጃዎችን ወስዷል። ሆኖም ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ፣ ከዚህ በተጻራሪ፤ የወረርሽኙን ስርጭትን የሚያባብሱና እንደ ሀገር በዜጎች ላይ ሊፈጸም የማይገባ ድርጊት በመፈጸም ላይ ይገኛል። የወረርሽኙ አደጋ ሁሉንም ስጋት ውስጥ በከተተበት ሁኔታ እንደ ቤት ማፍረስ፤ ሰዎችን ከመጠለያቸው ማፈናቀል፣ ዜጎችን በጅምላ ያለፈቃዳቸው ከአዲስ አበባ ወደክልሎች በአውቶቡስ አጉሮ መላክ እና የመሳሰሉ ሰብዓዊነት የጎደላችውን ከአንድ መንግስት የማይጠበው ድርጊቶችን እየፈጸመ ይገኛል።

በቅርቡ፣ መንግስት ራሱ ያወጣዉን የአስቸኳይ ግዜ ድንጋጌ በመጣስ፣ አፍራሽ ግብረ ሃይል በማሰማራት፤ ቤቶችን በማፍረስ፣ ነዋሪዎችን በሃይል ከአፈናቀሏል። በዚህ የተነሳም ህጻናትና እናቶችን፣ ደካማ አዛዉንቶችን፣ እንዲሁም ሌላ መጠለያ ማግኘት የማይችሉ ዜጎችን፣ ለቫይረሱ እንዲጋለጡ የሚያደረግ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት ሲፈጽም ይታያል። ይህ ሳያንስ፤ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ”፣ ቤት የማፍረሱን ድርጊት በተቃወሙ ወገኖች ላይ እየደረሰ ያለው ወከባና እንግልት ከግዜ ወደ ግዜ፣ እየተባባስ ሄዶ፣ በህጋዊ መልክ የተደራጁ የፓርቲ አመራርን ሳይቀር እስከማሰር ተደርሷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ በሳላፍነው ሳምንት፣ ከመጠለያቸው በአፈራሽ ገብረ ሃይል የተፈናቀሉ ወገኖችን ሁኔታ ለመከታተልና ቅሬታቸዉን ለመስማት ብሎም አስፈላጊዉን እርዳታ እንዲያገኙ በቦታው ተገኝተው የነበሩት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞከራሲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ለእስር የተዳረጉበትን ሁኔታ አስተውለናል። ይህ ህገወጥ ድርጊት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን የማዋክብ ድብቅ ፍላጎትና አጀንዳ እንዳለው ተጨባጭ ማሳያ ሆኖ አልፏል።

በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ ወቅቱን ያልጠበቁ የቤት ማፍረስና ማፈናቀል እርምጃዎች፤ የአለም ህዝብን ስጋት ላይ ከጣለው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚከሰት የጤና አደጋ ጋር ተዳብሎ፣ ዜጎችን ለከባድ ችግር ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን ተከትሎ በሚከሰተው ስራ አጥነት እና የኑሮ መናጋትን ለሚፈጥር ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ መዘዝ የሚጋብዝ ድርጊት ነው።

ስለዚህ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ እና በአሁኑ ግዜ ሙሉ ትኩረቱን በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በሚመጣዉ የወረርሽኝ ስርጭትን በመከላከል ላይ እንዲያውል እኛ ከዚህ በታች ስማችን የተዘረዘረዉ ጉዳዩ ያሳሰበን ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ ጥሪ እናቀርባለን። በዚህ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ፣ ዜጎችን በሃይል ከመጠለያቸው ማፈናቀል፣ ስር የሰደደ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ ይኖረዋል ብለንም እናምናለን። በዚህ ግዜ፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንደ ሽፋን በመጠቀም ዜጎችን ከመኖሪያ ቤታቸዉ እና ስፍራቸዉ ማፈናቀል፣ ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ፤ በማንኛዉም መልኩ የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን በአንክሮ ማስገንዘብ እንወዳለን።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙን ለመከላከል የተጣለው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን እንደ ማጥቂያ ስበብ በመጠቀም፣ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ፤ የሰባዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው ያልተገባ የሃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም በአጽንኦት እንጠይቃልን።

ባለፈው ሁለት ሳምንት በመንግስት ጸጥታ ሃይሎች አዲስ አበባ ውስጥ ንጹሃን ዜጎችን በጥይት የመግደል እና ማቁሰል ድርጊቶች ተፈጽመዋል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ተላልፋቹሃል በሚል ስበብ ግለሰቦች ላይ ያልተገባ የሃይል እርምጃ ሰለባ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የህግ ባለሙያ እና ስብዓዊ መበት ተሟጋቿ ወይዘሮ ኤልሳቤት ከበደ አግባብነት በሌለው ሁኔታ በእስር እንድትቆይ ተደርጓል። ይህን እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ የተወሰደው የእስር እርምጃ ተቀባይነት የሌለው ህገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ ድርጊቱን በጥብቅ እያወገዝን፣ ከዚህ ተግባር በስተጀርባ ያሉ የመንግስት ተቋማትም ሆኑ ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ተረኛ ነን ባይ ግለሰቦች፣ ጉዳይ ተመርምሮ፣ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ ጥሪ እናስተላልፋለን። ከዚህ ሌላ፣ አቶ እስክንድር የግል ተንቀሳቃሽ ስልኩን ለፖሊስ በምርመራ ወቅት ቢያስረክብም፣ ከእስር ከወጣ በኋላ ስልኩ እንዳልተመለሰለት ለማወቅ ችለናል። ይልቁንም ስልኩን ህግን ባልተከተለ መልኩ በመበርበር የግል ፋይሎችንና የተለያዩ መልእክቶችን ለመውሰድ እየተደረገ ያልው ሙከራ እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን። ይህ ከፍርድ ቤት ተእዛዝ ውጪ፤ የግለሰብ ስልክንም ሆነ ሌላ ንብረት መቀማት፣ መረጃ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ህገወጥ ድርጊት፤ ፖሊስንም ሆነ ሌላ የመንግስት አካልን በህግ የሚያስጠይቅና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን እንገልጻለን።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በመጠቀም፣ የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለዉን ቀውስ ለብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ የምርጫ ቅስቀሳ መሳሪያነት ከመጠቀም እንዲቆጠብ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ እንቅስቃሴዎችን ከማዳከም እንዲታቀብ፤ እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ላይ እያደረገ ያለው የተቀናጀ አፈና በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ አጥብቀን እንጠይቃለን።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ – ዩኤስ አሜሪካ
ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ገብርዪ ወልደሩፋኤል – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ሞገስ ወልደሚካኤል – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አክሎግ ቢራራ- ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አሰፋ ነጋሽ – ኔዘርላንድ/አውሮፓ
ዶክተር ወንድሙ መኮንን – ብሪታኒያ/አውሮፓ
ዶክተር ግርማ ብርሃኑ – ስዊድን/አውሮፓ
ዶክተር ተድላ ወልደዮሃንስ – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አብርሃም አለሙ – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ሰማህኝ ጋሹ – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ – ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አብርሃም ጥበቡ – ዩኤስ አሜሪካ

ዶክተር ልዑልሰገድ አያሌው ዶክተር ገነት ስዮም አቶ ሙሉጌታ አያሌው አቶ ሃይለገብኤል አያሌው አቶ ጌታነህ ካሳሁን አቶ ሙሴ እንግዳሸት አቶ ያሬድ ሃይለማርያም አቶ መስፍን አማን አቶ ማስተዋል ደሳለው


https://zehabesha.info/archives/104756

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.