ስለገጠመ/ሙን ሕገ-መንግስታዊ ክፍተት/ቶች አንዳንድ ሀሳቦች

Tekelemicahel
ልጅ ተክሌ

በልጅ ተክሌ፤ ካናዳ፤ https://www.facebook.com/tsahlemariam

ችግሩ፤ እንደመግቢያ

 • ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ፤ ነሃሴ 23፤ 2012 አይካሄድም፡፡ ምክንያቱም፤ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 24 ባወጣው መግለጫ ላይ፤ በዚህ በሳንባ ቆልፍ በሽታ ወረርሽኝ ምክኛት የምርጫውን ሂደት በስርአትና በታሰበው መልኩ ማስኬድ አልችልም በማለቱ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያንን የምርጫ ቦርድ ሀሳብ አጽድቋል፡፡ ስለዚህ፤ በሕገመንግስቱ መሰረት፤ መስከረም 2013 ላይ ስልጣን መረከብ ያለበት አሸናፊ ፓርቲ አይኖርም፡፡ ሕገመንግስቱ እንዲህ ያለውን ክፍተት የሚሞላ ግልጽ ቀመር አላስቀመጠም፡፡ ስለዚህ <<<ምን ይውጠናል?>>> የሚለው ጥያቄ ነው እንደ ሕገመንግስታዊ ቀውስ የታየው፡፡

ቀውስ በሌለበት ቀውስ መፈልፈል

 • ኢትዮጵያ የገጠማት ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ ሳይሆን፤ ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ ወይም ውጥረት ወይም ታዬ ደንደአ እንዳለው ሕገ-መንግስታዊ ክፍተት ነው፡፡ ሕገመንግስታዊ ጥያቄዎች ወይም ክፍተቶች በየዘመኑ ያጋጥማሉ፡፡ መፍትሄው እነዚያን ሕገመንግስታዊ ጥያቄዎች እየፈቱ፤ ክፍተቱን እየደፈኑ መጓዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰለጠኑ የሚባሉት አገሮች ሁሉ፤ ሕገመንግስቶቻቸውን እየከለሱ፤ እያሻሻሉ፤ እየጠገኑ፤ የሕግመንግስታቸውን ቀዳዳ እየጣፉ ነው እዚህ የደረሱት፡፡ እንጂ፤ ክፍተት በታየ ቁጥር፤ በግድ አርገብግቦ፤ ጋዝ አርከፍክፎ፤ ቀላሉን ነገር ማቀጣጠል፤ ችሎታም ለአገር መቆርቆርም አይደለም፡፡

 

 • በዚህ ክፍተት ወይም ቀውስ ዙሪያ ብዙ እየተባለ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ አብሮነት የተሰኘ የሶስት ፓርቲዎች ቅንጅት ያወጣው፤ ወንድሜ ጃዋር ያራገበው፤ እና ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦችም የሚያራምዱት፤ ብልጽግና እኛን ካላወያየ፤ ካልተደራደርን፤ ወይም (በአራዳ ቋንቋ) ስልጣን ካላጋራን፤ ሕገ-መንግሰታዊ ቀውስ ይፈጠራል፤ አገሪቱ ወደለየለት ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚለው የሚለው ነው፡፡ ጤናማም ጠቃሚም አይደለም፡፡ እኔ ይሄንን ቀውስ በሌለበት ቀውስ መፈልፈል ወይም መደገስ እለዋለሁ፡፡

 

እስካሁን ሌላስ ምን ይባላል?

 • አብሮነት ያወጣው መግለጫ ቀጥሎም፤ እስከ መስከረም መጨረሻ፤ የአብይ መንግስት ምርጫንና ሕገመንግሰታዊ መሻሻልን በተመለከተ፤ እጁን አጣጥፎ ይቀመጥ፡፡ ‹‹‹ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ››› ያንን ተከትሎ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ያኔ ብልጽግና ስልጣኑ ባበቃ ግዜ፤ ከኛ እንደአንዱ ይሆናል፡፡ የግድ እኛን አካቶ ከመጓዝ ውጪ ምንም ምርጫ የለውም የሚል ነው፡፡ ይሄንን ሕገመንግስታዊ ቀውስ ለማከም፤ ብልጽግና የግድ ከኛ ጋር መደራደር ወይም መስራት አለበት፡፡ መግለጫው የኤዴፓ ፌስቡክ ገጽ ላይ ይገኛል፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  የአንድ አገር ህዝቦች ሁለት ዜግነት - ቬሮኒካ መላኩ

 

 • ይሄንን ቀውስ የሚጋብዝ አካሄድ ሕወሀት በከፊል፤ እና ሌሎች ታዋቂና አዋቂ ግለሰቦችም ይደግፉታል፡፡ የዛሬ ስድስት ወር አገሪቱ ገደል ትገባለች፤ ስለዚህ ገደል አፋፍ እስክንደርስ ማንም ምንም እንዳያደርግ፡፡ ገደል አፋፍ ላይ ያለን ምርጫ ተያይዘን ማለቅ ስለሆነ፤ ያንን ለማስቀረት ስንል እንድንነጋገር ግድ ይሏል፡፡ ስለዚህ እስከዚያ ዝም እንበል፡፡ ወይም ትኩረታችን ኮሮናን ማጥፋት ላይ ብቻ ይሁን፡፡ ከሕገ-መንግስታዊ ቀውስ ይልቅ ኮሮና ይከፋል አይነት ሀሳብ ነው፡፡ እና አገር በስልጣን ዙሪያ መሸሽኮርመም ስለሚበዛ ነው እንጂ፤ ስልጣን እንካፈል ነው ዋንኛው ሀሳብ፡፡ በግልጽ እንደዚያ ማለት ነውር የለውም፡፡ እንደውም መብት ነው፡፡ ግልጽነት ግን የለም፡፡

ሕገ-መንግስታዊ ትርጓሜና፤ ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያ

 • መንግስት የቀጠራቸው አጥኚዎች፤ ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ፤ ሕገመንግስታዊ ትርጓሜ መጠየቅ፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅን እና ፓርላማውን በመበተን ተጨማሪ ስድስት ወር አገኝቶ ምርጫ ማድረግን እንደመፍትሄ ሀሳብ ሰነዘሩ፡፡ አብሮነት፤ ሕወሀትና አንዳንድ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች፤ ለተፈጠረው ወይም ለሚፈጠረው ቀውስ መፍትሄው፤ ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ ወይም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወይም የፓርላማው መፍረስ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ውይይት ወይም ከመደበኛው ሕግ ወይም ሕገ-መንግስት ወጣ ያለ ፖለቲካዊ ድርድር ነው አሉ፡፡ ስልጣን እንካፈል ነው ነገሩ፡፡ እንጂ መከራከሪያቸው ብዙም ውሀ አይቋጥርም፡፡

 

 • ለምሳሌ፤ ከፓርላው መበተን ጋር በተያየዘ፤ አብሮነት ያስቀመጣቸው መከራከሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ‹‹‹የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 60ን በተመለከት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግስት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም አይደለም፡፡ በተጨማሪም፡ እንዲያውም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ በህግ የተሰጠን የስራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የስራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግስት የስራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡››› የአብሮነት ሀሳብ ነው፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮሞ ህዝብ በይፋ ከታወጀበት ጦርነት ራሱን የመከላከል ህጋዊ መብት አለው! - ትዕግስትም ልክ አለውና!

 

 • ይሄ ግን አንድ አተረጓጎም ነው፡፡ የሕገመንግስቱ አንቀጽ 60(1) አብሮነት እንዳለው ብቻ አይተረጎምም፡፡ የኔ የሕገ-መንግሰቱ አነባበብና አረዳድ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ በርግጥ በሕገመንግስቱ አንቀጽ 106 መሰረት፤ ገዢው የአማርኛው ሰነድ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሕገመንግስት፤ የእንግሊዘኛው ቅጂ አንቀጽ 60 (1) እንዲህ ይላል ‹‹‹With the consent of the House, the Prime Minister may cause the dissolution of the House before the expiry of its term in order to hold new elections.›››  የአማርኛውና የእንግሊዘኛውን አንቀጽ፤ ከአንቀጽ 60(5) ጋር አንድ ላይ ስናነበው የሚሰጠን ትርጉም፤ ሕገመንግስቱ በርግጠኝነት የሚናገው፤ ገዢው ፓርቲ ስልጣኑ ከማብቃቱ በፊት ፓርላማውን መበተን ስለመቻሉ እንጂ፤ ምርጫውን የሚያደርገው የተመረጠበት ጊዜው/ተርም ከማለቁ በፊት ነው ወይስ በኋላ፤ በአምስት አመቱ ውስጥ፤  የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡

 

 • አንቀጹ፤ መንግስት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ስምምነት፤ ፓርላማውን መበተን ስለመቻሉ የሚናገው በርግጥም የዚያ መንግስት ስልጣኑ ከማለቁ በፊት፤ በአምስት አመቱ ውስጥ ነው፡፡ በርግጥም ተርሙ ያለቀ ፓርላማ፤ ምኑ ይበተናል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ፓርላማው ከተበተነ በኋላ፤ ምርጫው የሚደረገው ለፓርላማው የተቀመጠው፤ 5 አመቱ ስልጣኑ ከማለቁ በፊት ነው ወይስ በኋላ የሚለው ግን አሻሚ ነው፡፡ አንቀጽ 60(5) ላይ መንግስት ፓርላማውን ካፈረሰ በኋላ፤ እስከሚቀጥለው ምርጫ በአደራ ሊያስተዳድር ይችላል የሚለው አንቀጽ የሚጠቁመው፤ ምርጫው መንግስት ጊዜውን/ተርሙን ከመጨረሱ በኋላም ሊደረግ እንደሚችል ነው፡፡

 

 • ይህ አንቀጽ፤ አከራካሪ ስለሆነ፤ ወደሕገመንግስት ትርጓሜ ነው የሚወስደን፡፡ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል፡፡ ፓርላማው ጊዜው የሚያበቃው ሰኔ ሰላሳ ከሆነ፤ መንግስት ሰኔ 29 ፓርላማውን በትኖ፤ በቀጣዮቹ 6 ወራት ውስጥ ምርጫ ማድረግ ይችላል፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች የፓርላማውን እድሜ እስከ መስከረም መጨረሻ ያደርሱታል፡፡ ይሁን እንጂ፤ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 58(3) የምክርቤቱ እድሜ 5 አመት ነው ቢልም፤ ንኡስ አንቀጽ 2 ግን የምክርቤቱ የስራ ግዜ፤ ከመስከረም የመጨረሻ ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ነው ስለሚል፤ አምስት አመቱ ራሱ የቱ ጋር ነው የሚያበቃው የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ስራውን ሰኔ 30 የዘጋን ምክርቤት ለጥጠን ወደ መስከረም መውሰድ እንችላለን ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  "በእኔ ስም አይሆነም!" "NON IN MIO NOME" - ሕዝብን የጨፈጨፈ ገዳይ ጀግና አይደለም!

 

 • የሆነ ሆኖ፤ መንግስት፤ አንቀጽ 60(1) በሚፈቅድለት መሰረት፤ ምክርቤቱን ከሰኔ 30ም ይሁን መስከረም 30 በፊት አፍርሶ፤ አንቀጽ 60(5) በሚፈቅድለት መሰረት፤ የእለት ተእለት ስራዎችን እያከናወነና፤ የምርጫውን ስራ እየሰራ፤ መቆየት ይችላል፡ ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ጉዳዩ ተቃዋሚዎች እንደሚያስቡት ቀጥተኛ አይደለም፡፡ አከራካሪ ነው፡፡ ስለዚህም ይሄ አሻሚ ትርጉም፤ የፌዴሬሽኑ ምክርቤት ትርጓሜ ያስፈልገዋል፡፡ በርግጠኝነት፤ በልምድ እንደምናውቀው፤ የፌዴሬሽን ምክርቤት ጥያቄውን በዚህ መልኩ ይተረጉመዋል፡፡ ጥያቄው የሚሆነው፤ 2 አመት ለዝግጅት ያልበቃው አብይ፤ ከዚያ በኋላ በሚያገኘው 6 ወር ብቻ ምርጫ ማድረግ ይችላል ወይ፤ እና የኮሮናው ነገር መቼ ያበቃል የሚለው ነው፡፡

 

 • ለአገራችን የሚበጀው፤ አብይ በማናቸውም መንገድ በቀጣዮቹ ወራት ምርጫ ማድረግ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ለገጠመን ችግር ያሁኑ ሕገመንግስት ውስጥ መፍትሄ መቆፈር ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ ለሳላሳ አመታት ሕጋዊ እውቅና ወይም ቅቡልነት በሌለውና በላዩ ላ በጉልበት በተጫነበት መንግስት/ስርአት ወገቡ የጎበጠ ሕዝብ፤ ሌላ ተጨማሪ አመታት በዴሞክራሲዊ መንግስት ጥማት መሰቃየት የለበትም ባይ ነኝ፡፡ አስረዳለሁ፡፡

 

 • እስኪ አረፍ በሉና፤ ትንሽ ትንፋሽ ወስደን፤ በክፍል ሁለት እንቀጥላለን፡፡

 

1 Comment

 1. ይሄ ሰውዬ በተለያየ ጊዜ እንደታዘብንው እይታ ፈላጊ እንጅ የሀገር ጉዳይ የሚያስጨንቀው ባለመሆኑ አምዱ የሀገራቸው ጉዳይ እረፍት ለነሳቸው ዜጎች ቢተው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.