/

የኢትዮጵያ ሰራተኞች የዘመናት ዉጣ ዉረድ የበዛበት የትግል ጉዞ!! – በዳዊት ሳሙኤል

በዳዊት ሳሙኤል
ከበርሊን ከተማ ( [email protected] )

Ethiopian Labor Day
Ethiopian Army Marching on Labor Day

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበር የምክር ቤት አባል

( እኔ አሁንም በስደት ብሆንም በሀገሪቱ ዉስጥ በነበረዉ አፋኝ ስርአት ፍትህ አጥቼ የተመረጥኩበትን የሰራተኛ መብት ትግል እንዳላገልግል ብደረግም ህጋዊ አባልነቴ እንደተጠበቀ ነዉ ብየ ስለማምን አሁንም እንዳለሁ እቆጥራለሁ)

የዚህ ፅሁፍ መታሰቢያ

የኢትዮጵያ ሰራተኞች አንድነት ማህበር ( ኢሰአማ) በ1950 ዎቹ መጀመሪያ በብርቱ ትግል አቋቁመዉ የነበሩትንና በጥልፍልፍ የተንኮል ሴራ ብስጭት የሰራተኛዉን የትግል ችቦ ከለኮሱ በኋላ እራሳቸዉን ያጠፉትን ጓድ አበራ ገሙን፣

እንዲሁም በሀገራችን ላለፉት 28 አመታት ከህግ በላይ ሁነዉ ሀብታችንንም ፣ ጉልበታችንን ከሸክ አላሙዲን ጎን በመሆን ኢትዮጵያዉያንን ሰራተኞች በባርነት ቀፍድደዉ ይዘዉ በነበሩበት ወቅት ሰራተኛዉ መብቱን እንዲያሰከብር ዘወትር በመቀስቀስ ላይ እንዳሉ በሽምግልና ዘመናቸዉ በህገወጥ መንገድ ከስራ ተባረዉ በማይሰራዉ በወያኔ ካንጋሮ ፍርድ ቤት ለአመታት ተመላልሰዉ ፍትህ በማጣት ተበሳጭተዉ በስኳር ህመም እና በኩላሊት በሽታ ህይዎታቸዉ ላለፈዉ ለሸፍ ግርማ ወ/ ሰንበት ይሁንልኝ፣፣ እኝህም ሰዉ ልክ እንደ ጓድ አበራ ገሙ ባንድ ወቅት ከጓደኞቼ ጋር ከድርጅቱ ሰራተኛ በሚስጥር የሰበሰብነዉን ብር ልሰጣቸዉ ስንሄድ ‘‘ ልጆቼ እኔን የሀሰት ምስክር አዘጋጅተዉ ግቢዉ ዉስጥ ለሌላ ስራ ጉዳይ ለደቂቃዎች በተንቀሳቀስኩበት ወቅት ስራዉን ለቆ ሂዷል ብለዉ በማስመሰከር በፍርደ ገምድልነት አስፈርደዉ በእርጅና ዘመኔ ከስራ አስዎጡኝ፣፣ ምክንያታቸዉ ለምን ሰራተኛዉን መብቱን እንዲያዉቅ ታደርጋለህ ነበር፣፣ ዳኛዉም በህጉ ላይ አንድ ሰራተኛ ስራዉን ሳያሳዉቅ ያለ በቂ ምክንያት ለአምስት ተከታታይ የስራ ቀናት ከስራ ገበታዉ መቅርት እንጅ በድርጅቱ ቅጥር ገቢ ለስራ የተንቀሳቀሰ ሰዉ እንደማይባረር ጠፍቶት አይደለም፣፣ ነገር ግን እጃቸዉ እረጅም የሆኑ አረመኔዎች ተፅእኖ ስላለበት ፍትህን አጣኋት፣፣ እናንተ ትግላችሁን ቀጥሉ ስላደረጋችሁልኝ እርዳታ እግዚእብሄር ብድሩን ይክፈላችሁ‘‘ ብለዉ የተናገሩት ቀስቃሽ ምክር ዛሬ እንደሰማሁት በህሊናየ አሁንም ያቃጭልብኛል፣፣

ይህን ስል ግን በአለማችን የሰራተኛዉ መብት እንዲከበር ለዘመናት የተዋደቁትን ሰራተኞች ሁሉ በመዘንጋት አይደለም፣፣ ወይም በሀገራችን እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ በየትኛዉም አለም የተከበረዉን ተገቢ ክፍያ፣ እረፍት፣ የጤንነት ዋስትና፣ የስራ ዋስትና እና የመሳሰሉትን መብቶች ተነፍገዉ ያሉትን ሰራተኞች መስዋትነት በመዘንጋት አይደለም፣፣ እንኳን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ131 ኛዉ እንዲሁም በሀገራችን ለ45 ተኛ ጊዜ ለሚከበረዉ የሜይ ደይ በአል በሰላም አደረሳችሁ!!

 

የሰራተኛ መብት ትግል የት መጣ በሀገራችን!

በሀገራችን የዘመናዊ የሰራተኛ ቅጥርና ስለ መሰረታዊ የሰራተኞች መብት እንቅስቃሴ የተጀመረዉ በዳግማዊ ሚኒሊክ ዘመን የኢትዮጵያ ፈረንሳይ የአሁኑ ( የጅቡቲ ) የምድር ቧቡር ሰራተኞች በወቅቱ በነበረዉ የኢትዮጵያዉያንና የፈረንሳይ ሰራተኞች የአድልኦ ክፍያ ምክንያት ኢትዮጵያዉያን ሰራተኞች የተለያዩ አመፆችን ያካሂዱ ነበር፣፣ በተጠናከረ ሁኔታ ግን ትግሉን የጀመሩት በ1950 ዎቹ በነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምና ፕሮፌሰር በረከት ሀብተ ስላሴ ከጀርባ ሁኖ በማደራጀት እነ ጓድ አበራ ገሙ የመጀመሪያዉን የ1953 ቱ የኢትዮጵያ ሰረተኛ አዋጅ እንዲወጣ ከፍተኛ ትንቅንቅ ተደርጓል፣፣ የተለያዩ የፅሁፍ ምንጮች እንደሚያስረዱት በዚህ ወቅት ሰራተኛዉ እንዳይደራጅና ችግሩን ለንጉሰ ነገስቱ እንዳያቀርብ ከፍተኛ ሴራ ይሰሩ የነበሩት ሚኒስቴር አሁን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ብለን የምንጠራዉ መስሪያ ቤት ሀላፊ የነበሩት ሰዉ ብዙ ሸፍጥ ይሰሩ ነበር ይባላል፣፣ ይህን ሰዉ ደርግ ያለ ፍርድ ከረሸናቸዉ ስልሳ ሚኒስትሮች ዉስጥ አንዱ ነበሩ፣፣

አስገራሚዉ ነገር ግን የሀማሴኑ ኤርትራ ተወላጅ አቶ በየነ ሰለሞን ስለ ኢትዮጵያ ሰራተኞች ትግል በፃፉት መፀሀፍ ላይ ንጉሱ የሰራተኛዉን መብት የሚደነግግ አዋጅ ቢወጣ ተቃዉሞ እንዳልነበራቸዉ ፅፈዋል፣፣ በነበረዉ ጥልፍልፍ ሴራ ምክንያት ግን አቶ አበራ ገሙ እቤታቸዉ ዉስጥ ‘‘ እናንተ ትግሉን ቀጥሉ፣፣ እኔ ግን ይህንን ዉርደት እያየሁ ከምኖር ሞትን እመርጣለሁ ብለዉ ‘‘ ራሳቸዉን በሽጉጥ እነዳጠፉ ይነገራል፣፣ ለዚህ ዉሳኔና ተስፋ መቁረጥ የዳረጋቸዉ ክስተት ጥያቄዉን ለንጉሱ ለማቅረብ ብዙ ዉጣ ዉረድ ከተከፈለ በኋላ ንጉሱን ለማነጋገር እድል ተገኜ፣፣ ቤተ መንግስት በር ላይ በቀጠሮዉ ሰአት ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ የሰራተኛዉ ተወካዮች በሰአታቸዉ ከተገኙ በኋላ ይህ ከላይ ደርግ የረሸናቸዉ ሰዉ ተወካዮቹን ለሁለት ከፍለዉ አንደኛዉ ግሩፕ በጀርባ በር ሌለኛዉ ግሩፕ በፊት ለፊት በር በየተራ እየገባ እንዲያነጋግር የሚል የዉሸት ፕሮግራም በማዉጣት ንጉሱ ቤተ መንግስት ዉስጥ እየጠበቁ ባሉበት ሰአት ከዉጭ እየጠበቁ ያሉትን የሰራተኛ መሪዎች ለየ ግሩፑ አንደኛዉ ግሩፕ አነጋግሮ ወጥቷል ስለዚህ እናንተ ወደ ቤታችሁ ሂዱ በማለት ሁሉንም በዉሸት መረጃ ያሰናብቷቸዋል፣፣

እነ አቶ አበራ ገሙ በኋላ ሁለቱም ግሩፕ ተገናኝተዉ እንዴት ነበር ከንጉሱ ጋር የነበረዉ ዉይይት ? ብለዉ እርስ በእርስ ሲጠያየቁ እንደተሸዱ ገባቸዉ፣፣ በዚህ ቅፅበት ነዉ እንግዲህ በከባድ ብስጭት የታገሉለት የሰራተኛ አዋጅ ሲወጣ እንኳን ሳይመለከቱ ራሳቸዉን ያጠፉት፣፣ ለአቶ አበራ ወደ ደብረ ዘይት አካባቢ አንዲት የተዳከመች ትስራ አትስራ የማትታወቅ የማሰልጠኛ ተቋም አለች ከሚባለዉ ዉጭ ምንም አይነት መታሰቢያ በስማቸዉ አልቆመላቸዉም፣፣

 

ሰራተኛዉ በዘመነ ደርግ

የኢትዮጵያ ሰራተኞች በዘመነ ደርግ የፖለቲካ ድርጅቶች የመታገያ አጀንዳዎች ነበሩ፣፣ ከፍሉ ታደሰ ስለ ኢህአፓ ታሪክ፣ ፍቅረ ስላሴ ወግ ደረስ ፣ ገስጥ አየለ ስለ ወታደራዊዉ መንግስት ታሪክ፣ መራራ ጉዲና ስለ ፐለቲካ ትግሉ ምስቅልቅል፣ እንዲሁም የኢሰማኮ ሰነዶች እንደሚያስረዱት ሁሉም የየእራሱን ሰርጎ ገብ በማስገባት የሰራተኛዉን መሰረታዊ መብት ለየቆሙለት የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ እንዳደረጉት ሰነዶቹ ያስረዳሉ፣፣ ብዙ ሰራተኞችና የሰራተኛ መሪዎች በዚህ ምስቅልቅል ዉስጥ ተረሽነዋል፣፣ ደርግ እስከ አሁን ካሉት እጅግ የተሸለ ለሰራተኛዉ ሙሉ መብት የሚሰጥ ሊባል በሚችል መልኩ በ1968 አዋጅ አወጣ፣፣ ሰራተኛዉን እስከ ታችኛዉ እርከን ድረስ አደራጀ፣፣ ከሶሻሊስት አገሮች በተገኜ እርደታ አዲስ አበባ የሚገኜዉን ባለ አስራ አንድ ፎቅ ህንፃ አስገነባ፣፣ በርግጥ በንጉሱ ዘመንም ሜክሲኮ አደባባይ ላይ የአሜሪካ ጥቁር ሰራተኞች በሰጡት እርዳታ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገንብቶ ነበር፣፣

 

የዘመነ ወያኔ ምስቅልቅል

ወያኔ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ የመጀመሪያ ስራዉ በሚባል ሁኔታ ዱላዉ ያረፈዉ በሰራተኛዉና በተቋሙ ላይ ነበር፣፣ በ1984 ዓም የነበረዉን የደርግ አዋጅ በመሻር ሌላ የሽግግር አዋጅ አወጣ፣፣ ሰራተኛዉን ለሁለት በመክፈል የግልና የመንግስት ሰራተኛ በማለት በአንድ ማህበር እንዳይሰባሰብ አደረገ፣፣ በልዩ ሁኔታ መምህራን እጅግ ጠንካራ ማህበር ስለነበራቸዉ ከመንግስት ሰራተኞች ማህበራቸዉ እንዲቆይላቸዉ ተደረገ እንጅ ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች በማህበር እንዳይሰባሰቡ ተደረገ፣፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በዶ/ር ታየ ወ/ ሰማያት የሚመራዉን በሀይል በማፍረስ ተለጣፊ ማህበር አቋቋመ፣፣ ዛሬ በስዊዘርላንድ በስደት የሚኖረዉ ወንድም ኅይሉ ኡርጌሳ በአካል አግኝቸዉ እንዳጫዎተኝ እሱንና እነ አቶ ዳዊ ኢብራሂምን በማባረር ማህበሩን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በቁጥጥሩ ዉስጥ አዋለዉ፣፣

ማህበሩ በአንድ ኮንፌደሬሽን ስር ዘጠኝ ፌደሬሽኖች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳንዳቸዉ ፌደሬሽኖች የየራሳቸዉ ፕሬዚደንት ይመራሉ፣፣ ምንም ባይረጋገጥም ሁሉም ፌደሬሽኖች በድምሩ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመት አባል አለን ይላሉ፣፣ ወያኔ በመጀመሪያ የኒወ ሊበራል የፖለቲካ ፍልስፍና ብርቱ አቀንቃኝ የነበረ ድርጅት በመሆኑና የአለም ባንክን ስትራክቸራል አድጀስትመንት ተግባራዊ በማድረግ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ድርጅቶች ሁሉ ከነ ሙሉ ንብረታቸዉና ሰራተኛዉ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ሲሸጥ ሰራተኛዉ እንደ እቃ አብሮ ለአዲሶቹ ዘራፊ ባለሀብቶች በተናጋሪ እቃነት አብሮ ተሸጠ፣፣ ተከትሎም 377/94 የሚባል ምንም አይነት የማስፈፀም ሀይል የሌለዉን የአሰሪና ሰራተኛ የሚባል አዋጅ አወጣ፣፣ በወቅቱም ትልቁ በኩራት በየ ምሽቱ የሚናገሩት መግለጫ የድርጅቶች መሸጥና የሰራተኞች ከስራ መቀነስ ነበር፣፣ ይህ ለዘመናት ከግራ ከቀኝ ሲላጋ የኖረ ተቋም ሀገሪቱ በጎሳ የፖለቲካ ድርጅቶች ስትከፋፈል ወያኔ ከየቢሄሩ በመጡ የሰራተኛን አለም አቀፋዊ ትግል ባልተረዱ ተሹዋሚዎች ቁጥጥር ዉስጥ አዋለዉ፣፣ ይህ ሲባል ግን በተቋሙ ዉስጥ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ እልክ አስጨራሸ ትንቅንቅ እያደረጉ ያሉ አሁንም ያሉ ያልተዘመራቸዉ ቆራጦች የሉም ማለት አይደለም፣፣

ወደ አዉሮፓ ከመጣሁ በኋላ አንድ ኢትዮጵያ ዉስጥ የኖረች ፈረንጅ አግኝቸዉ በፊት እጠራጠር የነበረዉን የወያኔን መዋቅር እንደነገረኝ እና ወደፊት በዝርዝር የምፅፈዉን ለመግቢያ ያክል በኢህአዴግ ዉስጥ የወጣቶች፣ የሴቶች ሊግ እንዳለዉ ሁሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚመራና የደህንነት ሰዎች በቀጥታ በቅርብ እርቀት ቢሮ ተሰጥቶአቸዉ የሚቆጣጠሩት የሰራተኛዉ ሊግ አለ፣፣ ይህንን ስሰማ እነዚያ ለሀቅ ለሰራተኛዉ መብት መከበር በዚህ አስፈሪ መረብ ዉስጥ ሁነዉ እየተናነቁ የነበሩ ወንድሞቸንና እህቶቼን ሳስባቸዉ ልቤ እጅጉን ደማ፣፣ የዚህ አይነቱ አወቃቀር በሁለተኛዉ የአለም ጦርነት የጀርመን ናዚ ፓርቲ ይከተለዉ እንደነበር በአዉሮፓ ዩንቨርሲቲዎች ስማር እጅጉን አስገረመኝ፣፣

ከላይ ከጠቀስኩት ከነ ድርጅቱ መሸጥ በተጨማሪ ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ብቻ በአንድ ቀን 3000 ሰራተኞች፣ 9000 የቴሌ ሰራተኞች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኝ የእርሻ ጣቢያ 800 ሰራተኞች የማህበር መሪዎችን ጨምሮ፣ በገፍ በህገ ወጥ መንገድ ከስራ እየተባረሩ በምትካቸዉ የፖለቲካና የጎሳ ወገንተኝነት እየታየ መልሶ ሌሎች አዲስ ሰራተኞች ይቀጠሩ ነበር፣፣ አዲስ አበባ ዉስጥ የተባረሩ ሰራተኞች አራት አምስት ልጆቻቸዉን መንገድ ላይ በማስቀመጥ በየ ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ‘‘ከዚህ መስሪያ ቤት ያለ አግባብ ተባርሬ ወግን እርዱኝ ‘‘ የሚሉ ማስታወቂያዎችን ማየት የዘወትር አሰቃቂ ትይንት ሆነ፣፣ አንዳንድ የዉጭ ሀገር ድርጅቶች በመስሪያ ቤታቸዉ ዉስጥ እስር ቤት በማቋቋም ሰራተኛን ያስሩ ነበር፣ ሴቶች በየ ድርጅቱ በጉልበት በዉጭ ሀገር ሰዎች ይደፈሩ ነበሩ፣ በአበባ እርሻ ዉስጥ በአለም የተከለከሉ ኬሚካሎች በገፍ ወደ ሀገራችን እየገቡ ስራ ላይ ይዉሉ ስለነበር መሬቱን ከማበላሸታቸዉ በጨማሪ ሰራተኞች አይናቸዉ ጠፍቶ፣ የመተንፈሻ አካለቸዉ ተዘግቶ፣ ሴቶቹ መክነዉ፣ የቆዳ በሽታ ይዟቸዉ የተወሰኑት በየፍረድ ቤቱ እና በሰራተኛ ስብሰባ ላይ በሪፖርት መልክ ይቀርብ ነበር፣፣ ለዉጭ ሀገር ድርጅቶች የዉጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የነበሩት ባለስልጣናት ያለምንም ሀፍረት እርካሽ የሰዉ ሀይል አለን እያሉ በይፋ ያስተዋዉቁ

ነበር፣፣ ይህ እንግዲህ ሰዉ እርካሽ ስለሆነ ሳይሆን በሰሩት አፈናና መዋቅር ያሽመደመዱትን መሄጃ አልባ ሰራተኛ ለመግለፅ የሚጠቀሙበት ገላጭ ቃል ነበር፣፣

እኔ በነበርኩበት የሸክ መሀመድ ድርጅት ዉስጥ በዘመኑ በሀገሪቱ ዉስጥ ከእግዚአብሄር በታች ሁሉን ነገር ማድረግ ይችሉ የነበሩት እነ ተካ አስፋዉ፣ አብነት ገብረ መስቀል ከደህንነት ተቋሙ ጋር በመተባበር ሰራተኛዉን በቀጭን ትእዛዝ በገፍ ደመወዝ ይጨመርልኝ ብሎ ስለጠየቀ ብቻ ሲያባርሩ ያን ሁሉ ጉድ ግንባር ቀደም ሁኜ ተመልክቻለሁ፣፣ እነዚህ ሰዎች በወቅቱ የኢትዮጵያን ስፖርት ፌደሬሽን፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዉያንን ስፖርት ፌደሬሽን ፣ የተለያዩ ወስላታ የተቃዋሚ መሪዎችን በገንዘብ እያማለሉ የህዝቡን ትግል ሲያኮላሹ፣ የዉሸት የግል ጋዜጣ በማቋቋም መረጃን ሲያዛቡ፣ በሙስና የፍትህ ስርአቱን አለ ከተባለ ሲያዛቡ፣ በሀገሪቱ ላይ ሁለንተናዊ የባህል ዝቅጠት ሲያደርሱ ለተአምሩ በታሪክ አጋጣሚ በዚያ ቦታ ሁኜ አቅም አጥቼ አይ ነበር፣፣ ዛሬም እነዚህ ሰዎች ሶስት ጊዜ አክሮባት ሰርተዉ የለዉጡ ዋና አቀንቃኞች ሁነዉ ግምባር ቀደም ተሰላፊ ሁነዉ ሳይ ያለመታደላችን ነገር ያሳዝነኛል፣፣

 

ሰራተኛዉ ዛሬ!!

የኢትዮጵያ ሰራተኞች እና ማህበራቸዉ በሌሎች በሀገሪቱ ተቋማት ዉስጥ የታየዉ የመዋቅርም ይሁን የሰዉ ለዉጥ ለማድረግም ምንም ባልታሰበበት ሁኔታ በጨለማ ዉስጥ ይገኛሉ፣፣ ከላይ በጠቀስኩት መንገድ በህገወት መንገድ ባለቤትነታቸዉ የዞረዉን ድርጅቶች የያዙት ዘራፊ ባለሀብቶች በማኩረፍ ኢኮኖሚዉን ማሽመድመድ በመቻላቸዉ፣ ጥገናዊ ለዉት እንጅ አብዮት ተካሂዶ ሀገሪቱ ከደም መጣጮቹ ስላልተገላገለች፣ በነበረዉ የፖለቲካ ምስቅልቅል የኢኮኖሚዉ እንቅስቃሴ በመዳከሙ፣ ጠንካራ የሰራተኛ ተወካዮች ባለመኖራቸዉ፣ ሰራተኛዉ ለዘመናት በደረሰበት ማሸማቀቅም ከግንዛቤ እጥረትም የመደራጀት ባህሉ ደካማ በመሆኑ፣ አሁንም በተከሰተዉ የሳንባ ቆልፍ ኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የዛሬዉን አለማቀፍ የሰራተኞች ቀኝ በጨለማ ዉስጥ ሁኖ እያሰበዉ ይገኛል፣፣

 

ከጨለማዉ መዉጫዉ መፍትሄዎች

 • በሀገሪቱ የለዉጥ ሀይል ነኝ ብሎ የተነሳዉም ይሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደቀደመዉ ለየ እራሳቸዉ የፖለቲካ አጀንዳ የሰራተኛዉን ትግል ከመጎተት ተቆጥበዉ ሰራተኛዉ ነፃ ማህበር ኑሮት ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት አስተዋፅኦ እንዲያበክት የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ቢያበረክቱ፣፣

 

 • አሁን ያለዉ መንግስት ላለፉት ሰላሳ አመታት የተተገበረዉን አፋኝና ጥልፍልፍ መዋቅር በመተዉ የሰራተኛዉ መሪዎች አለም አቀፍ የሰራተኞች መብት በሚፈቅደዉ ኢትዮጵያም ተቀብላ ባፀደቀችዉ የሶስትዮሽ ስምምነት ( ILO Tripartizem ) መሰረት በትክክል አሰሪዎች፣ ሰራተኛዉ እና መንግስት የሚሳተፉበት የህግ ማዉጣት፣ የፖሊሲ ማፅደቅ፣ የዉጭ አገርም ይሁኑ የሀገር ዉስጥ ባለሀብቶች በሚያደርጉት የመዋእለ ነዋይ ፍሰት ሰራተኛዉን ባገለለ የሚደረገዉን አሰራር በማስቀረት ሰራተኛዉ የባለቤትንት ስሜት እንዲሰማዉ ቢደረግ

 

 • በሀገራችን የትምህርት ካሪክለምም ይሁን ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ሰራተኞችን የተመለከቱ ስልጠናዎች ቢዘጋጁ

 

 • ሰራተኛዉ እራሱን ከመቸዉም ግዜ በላይ በማደራጀት መብቱን እንዲያስከብር፣ የሀገሩን ሁለንተናዊ እድገት ለዉጥ አንዱና ዋናዉ አካል ሁኖ ራሱን ቢያዘጋጅ

 

 • ከዚህ በፊት የነበሩ አፋኝ ህጎች እንዲቀየሩ፣ እንዲሻሻሉ ቢደረጉ

 

 • ሰራተኛዉም ይሁን አሁን ያሉት ማህበራት የሰራተኛዉን ጉዳይ የሚዘግቡ ሚዲያዎች እንዲኖሩ ቢሰሩ

 

 • ከዚህ በፊት በህገወጥ መንገድ የተዘረፉ፣ ባለቤትነታቸዉ የዞሩ ንብረቶች እንደገና ተመርምረዉ ህጋዊ እርምጃ ቢወሰድ

 

 • ሰራተኛዉ እራሱን አደራጅቶ መብቱን ከሌሎች ሀይሎች ከሚጠብቅ ይልቅ በፖለቲካዉ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርግ፣፣ ( በብዙ የአለማችን ሀገሮች ራሳቸዉን የቻሉ የሰራተኛ ፓርቲዎች አሉ በአፍሪቃም በብዙ ቦታዎች መሪዎች ስልጣን ለመያዝ የሰራተኛዉን ድጋፍ ካላገኙ የማይሳካላቸዉ የሆኑ ብዙ አገሮች አሉ፣፣ ምሳሌ ደቡብ አፍሪቃ )

1 Comment

 1. የዚህ አይንት መሳጭና የነበረዉን እዉነታ ፍንትዉ አድርጎ አሁን መደረግ እስካለበት መፍትሄ ድረስ ያቀረበ ሰዉ አላየሁም:: ሁለት ግዜ በተመስጦ አነበብኩት:: ለዘሀበሻዎች የምመክረዉ ይህንን ፅሁፍ በድምፅ ብታቀርቡት ብዙ የዘሀበሻ ተመልካች ሊያየው ይችል ነበር : በሀገሪቱ የሰራተኛ ትግል እንዴት ለዉጥ ያመጣ ነበር::
  ለፀሀፊዉ የምመክረዉ ግን በትክክል ሁሉንም ነገር ሰራተኛዉን ወክሎ በፊት ለፊት ብዘ ነገር ያየ ሰዉ በመሆኑ በሬድዮ ቃለ መጠይቅ፣ ተከታታይ ፅሁፎች፣ ቢያቀርብ ብዙ ለዉጥ ለማምጣት እምቅ ሀይል እንዳለዉ ያሳያል::
  ለመሆኑ ግን የዚህ አይነት ታሪክ ይዘህ እስካሁን ለምን ወደ ህዝብ አልቀረብክም?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.