“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ የዜጎች ሰብዓዊ መብት መጣስ የለበትም” ኢሰመኮ

Policeይህንን የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸት ገብሬ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች በፀጥታ ኃይል አባላት ጥቃት ደረሰብን የሚሉ ሰዎች መሰማታቸውን ተከትሎ ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው።

ከቅርብ ቀናት መደበኛና መደበኛ ባልሆነ መልኩ በስፋት መነጋገሪያ እየሆነ የመጣው በፀጥታ አካላት ተፈጸሙ የሚባሉ የመዋከብ ሲከፋም የመደብደብ ክስተቶች የገጠማቸው ሰዎች ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።

በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የገለፁ ሁለት ግለሰቦች ጉዳዩን አጉልተውት፤ የመብቶች ጥሰትና አቤቱታ የማቅረቢያ መንገድ አለመኖር አትኩሮት ስቧል።

ይህንን በተመለከተና ዜጎች ሕግን በሚጥስ አኳኋን በፖሊስ ወይንም በሌሎች የፀጥታ አካላት ጥቃት ከደረሰባቸው ጥቆማ የሚሰጡባቸው መንገዶች መኖራቸውን ለማጣራት ቢቢሲ የሚመለከታቸውን አካላት ጠይቆ ነበር።

ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባዮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ መሠረት ይፋዊ አስተያየት መስጠት የሚችለው የሰላም ሚኒስትር መሆኑን በመግለጽ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከዚህ ባሻገርም ስለተባሉት ክስተቶችና ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ ቢቢሲ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸት ገብሬን ጠይቆ በሰጡት ምላሽ ለኮሚሽኑ የቀረበ ቅሬታ ያለመኖሩን ተናገረው፤ “ይሁንና ለማኅበራዊ ደህንነት ሲባል በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሊጣሱ አይገባም” ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ እሸት ጨምረውም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከተከሰቱ መከታተሉን እንደሚቀጥል ይነገራሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም በቅርበት የሚከታተለው ኮሚሽኑ ከአዋጁ ድንጋጌ በኋላ ከሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አንጻር ሁለት መግለጫዎችን አውጥቷል።

እነዚህም የሰብዓዊ መብቶች መከበር አስፈላጊነትና ከግል ተሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ጋር በተገናኘም በመዘዋወር ነፃነትና በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚጣል ማናቸውም አይነት ገደብ የሰብዓዊ መብቶች መርህን የተከተለ መሆንእንደሚገባቸው የሚያመለክቱ ናቸው።

ኮሚሽኑ በመግለጫዎቹ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት የሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ በሕገ መንግሥቱና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎችና መርሆች መሰረት የተመራ ሊሆን ይገባል ብሏል።

በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም ለመከታተል የተቋቋመው ቦርድ ከነገ አርብ ጀምሮ በለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎችን አያያዝ እንደሚገመግም የገለፀ ሲሆን አያይዞም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ክትትል አደርጋለሁ ብሏል።

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት ባወጣችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአራት በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዳይሰበሰቡ፣ ብዙ ሕዝብ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚያመሩ ሰዎችም የፊት ጭምብል እንዲለብሱ ቢያዝዝም ተግባራዊ አለመደረጋቸው የበሽታውን የመሰራጨት ዕድል እንዳያገኝ ስጋታቸውን የሚገልፁ አሉ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.