እግዚአብሔርን ተቆጣሁት ወደላይ መስፍን ወልደ ማርያም

mesfin እግዚአብሔርን ተቆጣሁት ወደላይ መስፍን ወልደ ማርያምመስፍን ወልደ ማርያም
ሚያዝያ 2012

በደርግ ዘመን ሰው አውሬ ሆኖ ‹‹ዛሬኮ አንድም አልገደልኩም!›› በሚባልበት ክፉ ዘመን በጉለሌ ኪዳነ ምሕረት (ይመስለኛል) የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ንግግር ተጋብዤ ምነው ግፍን በየመንገዱ እያየን ሁላችንም ዝም አልን? በማለት አሳዝኜ ነበር፤ በእንግሊዝኛ፤ ከዚያም እግዚአብሔርን ተቆጥቼው ነበር! ፡—

አረ ስማ እግዚአብሔር!
ተቸገረ ፍጡር፤
እስከመቼ ድረስ ዝም ብለህ ታያለህ?
አይሰለችህም ወይ አቤት! አቤት! ሲሉህ?
ቸግሮህ ይሆን ወይ ብልሃቱ ጠፍቶብህ?
ባንተው እጅ ሥራ በገዛ ትንፋሽህ!
….
የኢጣልያ ፋሺስት ግፍ፣ የጃንሆይ ማባበል፣ የደርግ ጭካኔ፣ የወያኔ እኩይነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ምንም አላስተማረውም፤ ዛሬ ኮሮና አስተምሮት እንደሆነ እናያለን፤ እኔ ግን አይመስለኝም፤ እንዲሁ ሲናደድ እየደቆሰ ያስለቅሰናል እንጂ! እኛም አናርፍ እሱም አይለቀንም! እርስበርሳችን ማፋጀቱ የማያርመን ሲሆንበት ይቺን ለዓይን የማትበቃ ገዳይ ላከብን!
የየሃይማኖቱን ካህናት እንደኮሮና አፋቸውን የፈታላቸውና ነጻነት የሚባል ነገር መኖሩን ያሳወቃቸው ጊዜ የለም!

2 Comments

  1. ምን ችግር አለበት ይቆጡት ወደላይ ወደታችም ቢሆን ወደ እሚገኝበት። መላሽ ግን የለም። ሰው በከንቱ ይደክማል። የዓለም ህዝብ መተራመሱ ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም የሚገድለንና የሚያገዳድለን ነገር ጠፍቶ አያውቅም። ከአንደኛው ጦርነት በፊትም በተገኘው ስለት ሁሉ ስንገሸላለጥ እንደኖርን ያለፉው የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ። ትንሽ ሰለጠን ስንል ደግሞ የመግደያ መንገድን በማሳመር በአንደኛውና በሁለተኛ ጦርነት ይህ ነው የማይባል ሰቆቃዎች በራሳችን ላይ አድርሰናል። እልፍ ሰዎች የፈጣሪን መኖር ጠይቀዋል። አንድ ጸሃፊ ሲናገር ፈጣሪ እንደ ሌለ ማወቅ ከፈለግ “በህጻናት ላይ የደረሰውን ግብ ማየት ነው ብሎአል” እውቁ ደራሲ Christopher Hitchens ደግሞ እንዲህ ይለናል ” That which can be asserted without evidence, can be dismissed without evidence.” የፈጣሪን መኖር በጣታቸው ጠንቁለው ሊያመላክቱን የሚፈልጉ ሁሉ ራሳቸውን ያሞኛሉ እንጂ የሚጨበጥ ነገር የለም። ታዲያ ከዚህ ጋር አብሮ እኔን በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይወዳታል ህዝቡም ጸሎትና ምህላ ወዳጅ ነው ሲባል? ይህ ውሸት ነው። ሃበሻ የክፋት ቋት ነው። የሚጸልየው ጠላቴን ጣልልኝ ከሆነ እስማማለሁ። ከጎረቤቴ ጋር ሰላም ስጠኝ እንዳልሆነ ግን አምናለሁ። ፕሮፌሴሩ እንዳሉት ቀድሞም መገዳደል አሁንም መግደለ ነው። ተንኮላችን ማለቂያ የለውም። ሰው መዝረፍ፤ መደብደብ፤ በሃሰት መመስከር፤ መወነጃጀልና መጠላለፍ አብሮ መክሮ አፍትልኮ ከምክሩ በመውጣት ሌላውን ለሞት መዳረግ የሃበሻው የአለፈና የአሁን የፓለቲካ መሰሪነት ምልክት ነው። አሁን ደግሞ በዘርና በክልል እንዲሁም ቋንቋው የተደባለቀ ሰመ ነጻነት ከበሮ ይዞ ቢያዘልለውም ከረሃብና ከቸንፈር ነጻ ሊያደርገው አልቻለም። በቅርቡ በወጣ ዘገባ በአለም ላይ ከሚገኙ 195 ሃገሮች መካከል 55 ለከፍተኛ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ዘግቧል። ኢትዮጵያ ከእነዚህ በረሃብ ተመቺዎች ውስጥ አንዷ ናት። ከወደ ቻይና መንጭቶ አለምን አፍኖ የያዘው የኮሮና ቫይረስ ደግሞ አለን የሚሉትን ሁሉ መናጢ ድሃ እያደረጋቸው በመሆኑ ዓለማችን ምጥ ውስጥ ናት። መልሱ ግን ከሰማይ ሳይሆን በሳይንስ ብቻ የሚገኝ ነው። ነጋ ጠባ እግዚኦ ከማለት በተግባር የኮሮና ቫይረሱን ለመከላከል የሚረድ ነገሮችን በተናጠልም ሆነ በግል ለመዋጋት የሚቻለውን ማድረግ ይበጃል። ያው ቫይረሱ በራሱ ጊዜ ይደበቃል። ያኔ እፎይ ስንል ደግሞ ተመልሰን በቆንጭራ የሰው አንገት እንቀላለን። ሰለሆነም
    አንድ እውቅ የሃገራችን ጸሃፊ እንዳሉት “ሲገድሉና ሲገዳደሉ ኖሩ” ነው የታሪካችን ጅማሬና ፍጻሜ። ፕሮፌሴሩ ፈጣሪን መቆጣታቸው መልካም ነው። እኔ ግን ፈጣሪን ከመቆጣት ራሳችንን ተቆጥተን የሌሎችን የተሻፈፈ ጉዞ ለማስተካከል ሃይ ብንል ይሻላል ባይ ነኝ። ሌላው ሁሉ ለአዋፋት እንደተበተነ ጥሬ ነው። መልሶ መልቀም ያስቸግራል።

  2. ውድ ተስፋ፣
    የፕሮፌሰር መስፍንን አባባል ቃል በቃል ወሰድከውና ትርጒሙን አሳሳትክ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.