ሮምን የወረረው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ወታደር አበበ ቢቂላ

Abebe Bekele
ኢትዮጵያዊ ወታደር አበበ ቢቂላ

አበበ ቢቂላ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በቀድሞው የሸዋ ጠቅላይ ግዛት በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ አካባቢ ልዩ ስሟ ጃቶ በምትባል ሥፍራ ተወለደ። ወጣቱ አበበ እንደአካባቢው ባሕልና ልማድ በእረኝነትና በትምሕርት ተሰማርቶ በ12 ዓመቱ የቄስ ትምህርቱን አጠናቀቀ። አበበ ገና በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥር የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል።

በ1944 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በክብር ዘበኛ ሠራዊት በወታደርነት ይቀጠርና በገና ጨዋታ እና በስፖርት እየዳበረ ቆየ። ክቡር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ ሲገባም፤ ከስፖርት ጋር ይበልጥ ተቀራረበ እንጂ አልተራራቀም። ከውትድርና አገልግሎት ጎን ለጎን፤ በሠራዊቱ የስፖርት እንቅስቃሴ በተለይም በአትሌቲክስና በገና ጨዋታ ጎልቶ ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም።

በኅዳር ወር 1948 ዓ.ም በአስራ ስድስተኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የኢትዮጵያን ቡድን ለመቀበል በተደረገው ሰልፍ ላይ ከለበሱት ልብስ ጀርባ በኩል የአገራቸው ስም ‹‹ኢትዮጵያ›› የተጻፈበትን መለያ ልብሳቸውን ለብሰው አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩትን ወጣቶች ባየ ጊዜ ከፍ ያለ የኩራት ስሜት ተሰማው።

አበበ ሁኔታውን በዝምታ ማለፍ አልቻለም። ‹‹እነዚህ ስፖርተኞች እነማን ናቸው ?›› ብሎ ጠየቀ። ስፖርተኞቹ እነማሞ ወልዴና እነ ባሻዬ ፈለቀ ነበሩ። የአትሌቲክስ ፍቅር ወደ አበበ ውስጥ የዘለቀው ከዚያች አጋጣሚ በኋላ እንደሆነ ይነገራል። ‹‹ኢትዮጵያ›› ተብሎ የተጻፈበት ልብስ ለመልበስና በዓለም አቀፍ ውድድር አገሩን ወክሎ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ጥረት ጀመረ። በዚሁ ዓመት የጦር ሠራዊት ብሔራዊ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ተካፈለ። በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩት አትሌት ዋሚ ቢራቱና ሌሎች አትሌቶችም ጋር ተወዳደረ።

ዋሚ ቢራቱ የወቅቱ የአምስት ሺ እና የ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት ስለነበሩ፤ በዚሁ የማራቶን ውድድር እንደሚያሸንፉ ቢጠበቅ አይገርምም፤ ምክንያቱም ሩጫውን በቀዳሚነት እየመሩ ነበር። ከተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች በኋላ ግን ስታዲዬም ውስጥ የነበረው ሕዝብ ውድድሩን ከሚዘግቡ ጋዜጠኞች ‹‹አበበ ቢቂላ እየመራ ነው›› የሚል ያልተጠበቀ ዜና ሰማ። ‹‹ማን ነው አበበ? ይህ አዲስ ባለታሪክ ማነው?›› በማለት በአድናቆት ሲጠብቅ የነበረው ሕዝብ መልስ አገኘ። አበበ ቢቂላ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር አሸነፈ።

አበበ ቢቂላ በሌሎች ውድድሮችም አሸነፈ። በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ርቀቶች በአትሌት ዋሚ ቢራቱ ተይዞ የቆየውን ብሔራዊ ሪከርድ ሲሰብር፤ ብዙዎች ኢትዮጵያ አዲስ ጀግና አትሌት ማፍራቷን ተናገሩ። የአበበ የመጀመሪያ ህልምም እውን ሆነ። በውድድሮች ባሳየው ድንቅ ብቃት ለኦሊምፒክ ቡድን ተመረጠ።

በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች በጥሞና ይከታተሉ የነበሩት ስዊድናዊ አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን፣ የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ እንዲለማመድና፣ የሮም ኦሊምፒክ እስኪቃረብ ድረስም ከሁለት ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የመሮጥና የአንድ ሺ 500 ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሠራ አደረጉት። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የሮም ኦሊምፒክ ላይ ሲያልመው የነበረውን ‹‹ኢትዮጵያ›› ተብሎ የተፃፈበት የብሔራዊ ቡድን ትጥቅ በመልበስ በ1952 ዓ.ም ወደ ሮም አመራ።

በሮም ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመሳተፍ ከአሰልጣኙ ጋር ወደ ሮም ካመሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መካከል ለማራቶን ሩጫ የተመረጡት አበበ ቢቂላ እና አበበ ዋቅጅራ ነበሩ። ይሁን እንጂ ከ83 አገራት የተውጣጡ ከአምስት ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሊምፒክ ላይ የዓለም ሕዝብ ትኩረት በአውሮፓውያን አትሌቶች ላይ ነበር። ስለኢትዮጵውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍሪካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችልም አልተጠበቀም፤ ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሊምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅምና።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.