ተስፋ የተጣለበት የጎርጎራ ‘ወርክሾፕ’ ተስፋ አስቆራጭ ጉዞ ላይ ነው

ባሕር ዳር፡
ሚያዝያ 12/2012

ዘመናዊ ጀልባዎችን እና ሌሎችም ምርቶችን እንዲያመርት ታስቦ የተሠራው የጎርጎራ ወርክሾፕ ተጥሎበት ከነበረው ክልላዊ ተስፋ እያሽቆለቆለ ነው፡፡

በጎርጎራ ወደብ የተገነባው ይህ ወርክሾፕ ዘመናዊ ጀልባ፣ የፈሳሽ መያዣ ጋን (ታንከር)፣ መኪና ማደስ፣ የእንጨትና የብረት ቁሳቁስ ለማምረት እንደሚያስችል ታሳቢ ተደርጎ ነበር። ወርክሾፑ ዘመናዊ ጀልባዎችን በማምረት በጣና ሐይቅ ዘመናዊ እና ፈጣን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ እና በሀገሪቱ ለሚገኙ ሌሎች ሐይቆች ዘመናዊ ጀልባዎችን እያመረተ እንደሚሸጥ ታስቦም ነበር። ወርክሾፑ ዘመናዊ ጀልባዎችን መሥራት ቢጀምርም ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙ እየቀነሰ መጥቷል።

የወርክሾፑ ሠራተኞች ለአብመድ እንደተናገሩት ወርክሾፑ ዘመናዊ ጀልባዎችን እና ሌሎች ዕቃዎችን ማምረት ቢችልም አሁን ላይ ግን በሚፈለገው ልክ መሄድ ተስኖታል። የደንበኞቹ ቁጥር መቀነሱንና በገቢው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፈጠሩንም አብራርተዋል፡፡ በዚህም ለሠራተኞቹ ተገቢውን ጥቅማጥቅም ማስከበር ባለመቻሉ ሠራተኞቹ በየጊዜው እየፈለሱ ተቋሙ መለማመጃ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ አስፈላጊውን ግብዓት እንዲያሟላ እና ለሥራ ምቹ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጠይቀው ምላሽ እንዳልተሰጣቸውም ነው ሠራተኞቹ የተናገሩት፡፡

በጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት የጎርጎራ ወደብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ውበቱ ወርቅነህ ወርክሾፑን ለማስፋፋት እና ማሽኖችን ለማሟላት የበጀት እጥረት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

94014768 1238366586338333 3970650106411089920 n

የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙላት ፀጋ የስፍራው ከከተማ መውጣት ለወርክሾፑ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ የበጀት ውስንነት ስላለበት ለሠራተኞች የሚከፍለው ክፍያ አነስተኛ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ “ይህም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ ሠራተኞችን ማቆዬት አላስቻለንም። የወርክሾፑን ችግር መፍታት ቀላል አይደለም፤ ወርክሾፑን ማዘመንና የሠራተኞችን ጥቅማ ጥቅም በልዩ ሁኔታ መክፈል ካልተቻለ ችግሩ ይቀጥላል” ብለዋል።

በቀጣይ ድርጅቱ ምን ዕቅድ እንዳለው አብመድ የጠየቃቸው ሥራ አስኪያጁ መልሳቸው ‘‘የለም’’ ሆኗል። ነገር ግን ከአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ጋር አብሮ ለመሥራት መንግሥት ያስቀመጠው አቅጣጫ መኖሩንና የታሰበው ከተሳካ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አድርገዋል፡፡ በወርክሾፑ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከባድ መሆኑንም ገልጸዋል። ለወርክሾፑ መንግሥትና ባለሀብቱ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

አብመድ የጎርጎራ ወርክሾን የተመለከቱ ተከታታይ ዘገባዎችን መሥራቱ ይታወሳል፤ ወርክሾፑ የጀልባ፣ የግብርናና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን በማምረት የልኅቀት ማዕከል የመሆን ሕልም ሰንቆ ነበር፡፡

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ/ አብመድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.