አፄ ሚኒሊክ‹‹….ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን መድከም አለበት።»

minilikአፄ ሚኒሊክ‹‹….ማንም ሰው ለመማርና ለመሠልጠን መድከም አለበት።»
የስልጣኔ አባት፤ ጥበበኛ መሪ፤ዳግማዊ አጤ ምኒልክ!
•‹‹…..ምኒሊክ ዘመናዊ ኢትዮጵያን የፈጠረ ሰው ነው…›› ጳውሎስ ኞኞ
•ስም-ዳግማዊ አጤ ምኒልክ
•ማዕረግ-ንጉሰ ነገስ ዘኢትዮጵያ
•የስልጣን ቆይታ-1882-1906

ዳግማዊ አጤ ምኒሊክ ከሸዋው ንጉስ ሀይለ መለኮት ስላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ለማ አድያም ቅዳሜ ነሃሴ 12 ቀን1836 ዓ.ም ደብረ ብርሃን አካባቢ አንጎለላ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ እንደተወለዱ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከ1858 እስከ 1906 በነበራቸው የስልጣን ቆይታ ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ እጅግ ስራ ወዳድ ፣ትሁት ሰው ነበሩ፡፡ሥራ ወዳድ በመሆናቸውም በርካታ የስልጣኔ ስራዎችን ወደ አገራችን አስገብተዋል፡፡

በዘመናቸው በአውሮፓ የነበሩ የስልጣኔ ስራዎችን ሁሉ ወደ አገራቸው አስገብተዋል፡፡ ለሌሎች ለማስለመድም ለመጀመርያ ጊዜ የሚገባውን አዲስ ነገር ሁሉ መጀመርያ እርሳቸው እየተጠቀሙ ሌሎች እንዲሞክሩት ያደርጉ ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መኪና የገባው በአጤ ምኒሊክ ዘመን ነበር፡፡ የመጀመሪያዋን አውቶሞቢል ያሽከረከሩም አጤ ምኒሊክ ናቸው፡፡ በታሪክም የመጀመሪያውን ትክክለኛ መንጃ ፈቃድ የተቀበሉ ምኒልክ ናቸው፡፡

‹‹የእህልን ወፍጮ›› ‹የሰይጣን ስራ› ነው ተብሎ ይታመን በነበረበት ጊዜ ጋኔን አለመሆኑን ለማሳወቅ በተግባር ያሳዩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ንጉስ አጤ ምኒልክ ናቸው፡፡ስልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስገቡበት ወቅትም ‹‹ጋኔኑ ከዙፋኑ አጠገብ ይውጣ›› በማለት የዘመኑ የሀይማኖት አባቶች ከባድ ተቃውሞ ቢያነሱምባቸውም በማሳመን ስልክን የተጠቀሙ እርሳቸው ናቸው፡፡ ብስክሌት ‹‹መንዳት››ተምረው ያሽከረከሩም እሳቸው ናቸው፡፡ጣይቱንም ብስክሌት‹‹ መንዳት›› አስተምረው አስተምረው የሀገራችን ሴቶች ከመሸፋፈንና ከማፈር እንዲዎጡ አርዓያ ሆነዋል፡፡

ሆቴል መመገብ ነውር አለመሆኑን ለማስተማር ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሆቴል ከፍተው በገንዘባቸው መኳንንቶችን እየጋበዙ ከሆቴል መመገብ ያስተማሩ ምኒልክ ናቸው፡፡ የተለያዩ አበቦችና ጽጌረዳዎችን ከአውሮፓ እያስመጡ ያራቡ እና ያስተዋወቁ ናቸው አጤ ምኒልክ፡፡ የባህር ዘፍ፣የኮክ፣እንጆሪና ሌሎች እፅዋትንም አስተዋውቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ ፖስታ ቤት፣ ባንክ ቤት፣ ሲኒማ ቤት፣ማተሚያ ቤት እንዲከፈት፣ የሙዚቃ ትምህርት ክፍልም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭን ያስተገበሩና ባቡር ያስገቡ፣ዘመናዊ የመንገድ ስራ ያስጀመሩ… በርካታ የቴክኖሎጅ ስራዎችን በማስተዋወቅ ኋላ ቀርነትን ፊት ለፊት የተጋፈጡ…ዘመናዊነትነትን ያስተዋወቁ ዘመናዊ ሰው ናቸው፡፡

ምንጭ፡- ‹‹አጤ ምኒሊክ›› የተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መፅሀፍ አጤ መልካም ልደት!!
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ