“ገበያው ፈርሷል፤ በኢኮኖሚው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን” ክቡር ገና

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/ 2012
ጌትነት ምህረቴ

%name “ገበያው ፈርሷል፤ በኢኮኖሚው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን”  ክቡር ገናበቻይና ኡሃን ግዛት ሁቤ ከተማ ጀምሮ ወደ ሌሎች አገራት የተዛመተው የኮሮና ቫይረስ የዓለምን ኢኮኖሚ እየጎዳው ይገኛል። ብዙ አገራት በረራዎችን አቋርጠዋል፣ድንበራቻውን ዘግተዋል፤ ህዝባቸው ከቤት እንዳይወጣ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ይህም በዓለም ኢኮኖሚው ላይ ከባድ ጫና አሳርፎል። የኮሮና ቫይረስ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ባለው ጉዳት ምክንያት ግማሽ ቢሊዮን ዜጎች ወደ ድህነት አረቋ የሚዘፍቅ መሆኑን የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር ያሳተመው ጥናት ቫይረሱ ለተወሰኑ ወራት የሚቆይ ከሆነ በርካቶች ሥራ-አጥ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል። በቅርቡ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽን በሠራው ጥናት እንደሚጠቁመው ቫይረሱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 60 በመቶ ሰዎች ሥራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ይገምታል። እንዲሁም ጥናቱ ከዘጠኝ ሚሊየን በላይ ሰዎች ተሰማርተውበታል በሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ሦስት ሚሊየን ሰዎች ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ይላል።

በአባዛኞቹ ዓለም አገራት ሆነ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ሲባል የወሰዱትን ውሳኔዎች ኢኮኖሚውን እያዳከሙት ነው። ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶች አገራቱ በራቸው በመዝጋታቸው ቁሟል። ከባህርማዶ ወደ አገር ውስጥ ይደረግ የነበረው የጎብኚዎች ፍሰት ተቋርጧል፤ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቆሟል። የሰዎች ዝውውር ተገድቧል የሚሉት የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚና ኢኮኖሚስት አቶ ክቡር ገና በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ጋር የተያያዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል። በዚህ ምክንያትም ለእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምርታቸውን የሚያስረክቡ ፋብሪካዎች ማምረታቸውን ቀንሰዋል ወይም አቁመዋል። ተያይዞ የሚመጣው የኢኮኖሚ ሰንሰለት ምክንያት ኢኮኖሚውን አዳክሞታል ይላሉ። እንደ ክቡር ገና ገለፃ፤ በተለይ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ሥራ አጥነትን በመጨመር፣ ድህነትን በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታውሰው ይህ አዋጁ ህብረተሰቡን ፍርሃት ውስጥ ስለሚከተው የተዳከመውን ኢኮኖሚውን ይበልጥ ሊያቆመው ይችላል። ችግሩን ለመፍታት ወደ ቀድሞው የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መመለስ ያስፈልጋል። አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሁሉም ሥራውን መሥራት አለበት።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ሌሎች የተወሰኑ አገራት ደንበራቸውን መዝጋታቸውና ህዝቡ ከቤቱ እንዲቀመጥ ውሳኔ ማሳለፋቸው ካላቸው የኢኮኖሚ ጥንካሬ ሊሆን ይችላል እንጂ ተገቢ አይደለም ያሉት ክቡር ገና፤ ልክ እንደ ቻይናን፣ ኮሪያ፣ ስዊድን፣ ሜክሲኮና ኩባ ሰው እንዲጠንቀቅ በማድረግ ኢኮኖሚውን ማስቀጠል እንጂ ኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ማስቆም ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። እናም ኢትዮጵያም እነዚህ አገራት የተከተሉትን መንገድ መከተል አለበት የሚል አቋም አላቸው። ምክንያቱም የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ተገትቶና ህዝቡ ቤቱ ተቀምጦ የቫይረሱ ስርጭት ተግትቷል ለማለትና ላለማት ምንም ማስረጃ ስሌለን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ በኢትዮጵያ በዕድሜ የገፉትና ለተጓዳኝ በሽታ ያላቸው ሰዎችን እንዳይጠቁ መከላከል አለብን እንጂ በጅምላ ለጥንቃቄ ተብለው የተወሰዱ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ጠቅላላ የህብረተሰቡን የወደፊት ዕድሉን የበለጠ ሊጎዱት የሚችሉ እንጂ የሚያሻሽሉ አይደሉም ብለዋል።

አሁን ባለንበት ሁኔታ በብድር እንደገና የአገር ኢኮኖሚ መገንባት አይቻልም የሚል እምነት ያላቸው ክቡር ገና፤ በሌሎች አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሲባል የተወሰዱ እርምጃዎች የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ቁሟል፤ ወደቦች ተዘግተዋል፣ አውሮፕላን ወደፈለገው ቦታ አይሄድም፣ ኢንቨስትመን ቁሟል፣ የሰዎች ዝውውር ተገድቧል። የንግድ ልውውጥ ተዳክሟል። ሆኖም ህብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፋለጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በማድረግና የተመረጡ የጥንቃቄ ሥራዎችን በማከናወን የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እንዲነቃቃ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ ።

መንግሥት ኢኮኖሚውን እንዲያንሰራራ ሦስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ላይ የተመረጡ እርማጃዎችን መውሰድ አለበት። በተለይ በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚመረተው የግብርና ምርት ከዋጋ መናር በስተቀር ብዙ የገበያ ችግር አያጋጥመውም። ስለዚህ መንግሥት የግብርናው እንቅስቃሴ ይበልጥ ማሻሻልና ማጠናከር አለበት። በአንፃሩ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪው ዘርፎች በቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት በተወሰዱ ውሳኔዎች በአጠቃላይ ቁመዋል ማለት ይቻላል። አብዛኛው ሠራተኛ ያለ ሥራ ቤቱ ተቀምጧል። ምንም እንኳ ደመወዝ እንዲከፈለው በመንግሥት ትዕዛዝ ቢተላለፍም ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ባለቤቱ ፈቃደኝነቱን ካላሳየ መበተኑ አይቀርም።
እነዚህ ሁለት ዘርፎች ወደ ቀደመ እንቅስቃሴቸው ለመመለስ ፈታኝ መሆኑን የሚገልፁት ክቡር ገና፤ ሁለት የመፍትሄ አማራጮችን ያስቀምጣሉ። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሣለጠ ንግድ እንዲካሄዱ ሰዎች ገንዘብ በእጃቸው መኖር አለበት። አንደኛ እንደነ አሜሪካ መንግሥት ሥራቸውን አቁመው ቤት ለተቀመጡ ዜጎች ገንዘብ መስጠትና እነዚህ ዜጎች ገንዘብ ሲያገኙ ገበያ ሄደው ይገዛሉ፤ አገልግሎቶችን ይጠቀማሉ። ይህም ኢኮኖሚው እንዲያገግምና እንዲያሰራራ ሊያደርግ ይችላል። ውጤታማነቱ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም ከእኛ አገርም ቢሞከር ጥሩ ቢሆንም ገንዘቡ ለማን ተሰጥቶ፤ ለማን አይሰጥም የሚለው አስቸጋሪ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም። እንደ ክቡር ገና ገለፃ፤ ሌላው ኢንዱስትሪው የሚያመርታቸው ምርቶች ለውጭና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚቀርቡ አሉ። በተለይ የኤክስፖርት ምርት የምንልክባቸው አብዛኛዎቹ የዓለም አገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተዘግተው የሚቆዩ በመሆኑ ገበያውን ለመጀመር ጊዜ ሊፈጅ ስለሚችል በቀላሉ ያንሰራራል ተብሎ አይጠበቅም። አገር ውስጥ ምርት ግን ማምረትና መሸጥ የሚቻል ቢሆንም ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን ማግኘት አደጋች ስለሚሆን ይህን የሚመጥን ዝግጅት ይፈልጋል። “የአገልግሎትና የኢንዱስትሪውን ዘርፎች የኢኮ ኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያሰራራ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ መቻል አለበት” የሚሉት ክቡር ገና፤ ምክንያቱም አሁን ያለው መንግሥት ለነፃ ገበያ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። ይህን ችግር ደግሞ ነፃ ገበያ ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። መንግሥት ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው የሥራ መስኮች ቅድሚያ የሚሰጥበት ስልትና ዕቅድ መንደፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

አሁን ባለንበት ሁኔታ ገበያ ችግር ሊፈታው አይችልም። አሁን ገበያ የለም ገበያው ፈርሷል፣ ወድቋል ማለት ይቻላል። ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ አይደለም ወይም ሙሉ ለሙሉ ቁመዋል፤ አዲስ ድርጅት እየተቋቋመ አይደለም፤ የገበያ እንቅስቃሴ ተዳክሟል የሚሉት ክቡር ገና፤ መንግሥት ቁጭ ብሎ ኢኮኖሚው እንዲያሰራራ የሚያስችለውን ዕቅድ መዘርጋት አለበት። ዕቀዱ ደግሞ ሥራ ላይ እንዲውል የመንግሥት አሠራሩን በሙሉ እንደገና ማስተካከል ይኖርበታል ሲሉ ያስረዳሉ

እንደ ኢኮኖሚው ምሁር ገለፃ፤ ኢኮኖሚውን እንዲያንሰራራ መንግሥት ቀዳሚ ሚና መጫወት አለበት። የዕቅድ አወጣጡንና አፈፃፀሙን ማጠናከር መቻል አለበት። ውጤት በሚያመጡት ኢንዱስትሪዎች ላይ ማተኮርና መደገፍ አለበት። ምሳሌ የውጭ ንግድ ካልን የትኛው ምርት ነው የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኘ የሚችለው የሚለውን በመለየት ለእነዚህ የሥራ ክፍሎች የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።

1 Comment

  1. ባጋጣሚ ሳይሆን በግሎባሊስት ሳታኒስት ኢሉሚናቲ አይሁዶች(Synagogue of satan Revelation 2:9 3:9 Mathew Chapter 23)በእቅድ የሆነ ነው።ፕሮቶኮሎቹ በጥሞና ይነበቡ።ፈጣሪ ብትችሉ በአዲስ ኪዳን የወንጌል ህግ ኑሩ ካልቻላችሁ ደግሞ በኦሪት ህግ ኑሩ ብሎ ቀንበሩ ቀለልና ለዘብ ያለውን መመሪያ አዘዘን።እኛ ግን ሁለቱንም አይሆንም ብለን በፈጣሪ ላይ አመፅን።ስለዚህ ለዚህ አመፃችን እንዲስማማ ሆኖ ፈጣሪ በሰይጣን ህግ እንድንገዛ ለዲያብሎስ ህግ አሳልፎ ተወን።
    መንግስታትም በዚህ እይታ ወታደርና ፓሊስ አሰልፈው የሰይጣንን መመሪያ እየተቀበሉ በሰይጣን ህግ እንዲገዙን ተደረግን።
    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጉግማንጉጉ ኮሚንዝም መንፈስ አድፍጦ ከኖረ በኋላ እራሱን የበለጠ አጠናክሮ የኮሮና ጭንብል አጥልቆ ዳግም እየመጣ መሆኑን ይጠቁማል።
    ሰይጣንም በባህሪ ልጁ ስጋ ለብሶ ሲመጣ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ ነው የሚመጣው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.