በፋኖ ላይ የሚደረገው ጥቃት በዐማራው ላይና ዐማራ አንስቷቸው መልስ ባላገኙት መሰረታዊ ጥያቆዎች ላይ የተቃጣ ብሎም ዐማራ COVID19 በተሰኘው ተላላፊ በሽታ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተሸረበ ሴራ ነው!

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት                  ሓሙስ መጋቢት ፳፬ ቀን ፪ሺህ፲፪..         ቅጽ ፯ቁጥር ፲፱

Moresh 90 በፋኖ ላይ የሚደረገው ጥቃት በዐማራው ላይና ዐማራ አንስቷቸው መልስ ባላገኙት መሰረታዊ ጥያቆዎች ላይ የተቃጣ ብሎም ዐማራ COVID19 በተሰኘው ተላላፊ በሽታ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተሸረበ ሴራ ነው!

በኢትዮጲያ ሀገራችን ላይ የተጫነው የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝ ”መሬት ላይ በሌለ የብሔር ጭቆና ወይም ቅኝ ገዥነት” ትርክት ላይ ተመስርተው፤ ኢትዮጵያን ማዳከም የሚፈልጉ የውጪ ኃይሎች የቀረጹላቸውን የዘውግ ከፋፋይ መርህ ተጠቅመዋል።በዚህም መሰረት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በተሰኘ የአፓርታይድ ሥርዓት ቀርጾ ሀገር ሲያተራምስ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና አንድነቱን ከተነፈገ ሦስት አስር ዓምታት ተቆጥረዋል። በተለይ ዐማራው በአውራ ጠላትነት ተፈርጆ በማንነቱና በህልውናው ብዙ አሰቃቂ ግፎች ሲፈጸምበት ቆይቷል። አሁንም ስማቸውን ለውጠው የመጡት የወያኔ ግብረአበሮች በዐማራው ላይ ያነጣጠረ ግፍና በደሉን ቀጥለውበታል። ለዚህም ማሳያው ከብዙ በጥቂቱ፣

  • የገዢው ኦዴፖ ቁንጮ መሪዎች በተለመደ ዐማራውን በሚያጥላሉበት የውሸት ትርክት “ትምክህተኛውን በሰበረን ቦታ ሰብረነዋል” እያሉ በየአደባባዩ በየጊዜው በተረኝነት እብሪት ሲፎክሩ መሰማቱና የአዴፓ ባለሥልጣናትም ከጎናቸው ቁጭ ብለው ሲያጨበጭቡ መታየታቸው፣
  • ለውጥ ተብየው ከመጣ በኋላም የዐማራ ህዝብ መጤ እየተባለ ከቀየው መፈናቀሉ፣ ምንም እንኳን አዴፓ ለተፈናቃዮቹ በስማቸው ብዙ ሚሊዮን ብር ቢሰበሰብም፤ ተፈናቃዮቹ ግን የቆርቆሮ ዛኒጋባ ተነፍገው፤ ያለመጠለያና አይዞህ ባይ በሜዳ ተበትነው ክረምት ከበጋ፤ ዝናብ፣ ፀሀይና ውርጭ እየተፈራረቀባቸው የአውሬና የበሽታ ሲሳይ መሆናቸው፣
  • ዐማራው ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ ከሌሎች ወገኖቹ በተለየ መገለሉና መጨቆኑ፤ በተለይም ዐማራው በብዛት በሚኖርባቸው ከተሞች ውስጥ ውክልና እንዳይኖረው በፖሊሲ የተደገፈ ማዕቀብ መጣሉ፣
  • የዐማራ ተማሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው፣ ዐማራ ስለሆኑ ብቻ ከትምህርት ገበታ መታቀባቸው ሳያንስ፣ ተማሪዎች በቄሮ/ኦነግ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ለአራት ወር ደብዛቸው መጥፋቱ፣ እስከ አሁንም የት እንደደረሱ አለመታወቁ፣ የታጋቾቹ ቤተሰቦች ለሚዲያ ብሶታቸውን በመናገራቸው ብቻ መታሰራቸው።
  • ከአዴፓ ቁንጮ አንዱ የሆኑት ገዱ አንዳርጋቸው ፋኖን ለማጥፋት ለካድሬዎቻቸው የማያደግም እርምጃ እንዲወሰዱ ሲወተወቱ መክረማቸው፣
  •  በኢንሳ ዐማራ ጠል በብሔረኞችን ሲያገለግሉ የኖሩት የአሁኑ የዐማራ ክልል ም/ፕሬዚዳንት የሥራው መግቢያ ያደረጉት “ብሔረትኝነትን እናጠፋለን” በሚል አገላለጽ በፋኖ ላይ የጥፋት ክተት ማወጃቸው፣ ይህንንም ተከትሎ በፋኖ መሪዎች ላይ ያላቋረጠ ማሳደድና ግድያ መፈጸሙ፣
  • ኦነጋውያን በቤተመንግስት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ፣ ዐማራ አንድ ዙር ልዩ ኃይል ሲያስመርቅ በጀቱ ለጦር እየዋለ ልማት እንዴት ይመጣል ባሉበት አፋቸው ኦዴፓ ግን ከልማቱ ጎን ለጎን የኦሮሞ ልዩ ኃይል ለ30ኛ ጊዜ ማስመረቁ ፣
  • ቄሮ በሚል ስም ተደራጅቶ በመላው ኢትዮጵያ ለአይን የሚቀፍና ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ወንጀል ሲሰራ፤ በሀገሪቱ ኦንጋውያንና  በቄሮ ኃይሎች በምትታመስበት ወቅት፤ አሁንም ለቄሮ የለውጥ ኃይል የሚል የጅምላ ሙገሳ ሲቸረው፣
  • በአንፃሩ ፋኖ የዚህ አለም ኑሮ ሳያሳሳው፤ እምቢ ለሀገሬ እምቢ ለነፃነቴ ብሎ ውድ ህይወቱን ገብሮ፤ አዴፓንም ጭምር ከወያኔ አገዛዝ ነፃ ያወጣቸው፣ ባለውለታቸው መሆኑ እየታወቀ በፋኖ ላይ የክተት አዋጅ መታወጁ፣ ፋኖ ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በዐማራ ላይ የተቃጣ የጥቃት ዕቅድ ነው፣ እንድንል ያስገድደናል።

ዛሬ ተረኛው አገዛዝ በሰላም ማስከበር ስም የሚያሳድደው ፋኖ ዐማራው በያለበት በነቂስ ወጥቶ በጎበዝ አለቃ በመደራጀት የጀመረው የህልውና፣ የማንነትና የአጽመእርስት ማስከበር ተጋድሎ ውጤት ሲሆን አስከአሁን ላላባራው የወያኔ /ኢህአዴግ አገዛዝ ዘር ተኮር የዘር የማጽዳትና ማጥፋት ዘመቻ የወለደው ነው። የፋኖ እንቅስቃሴ የወንበዴና የወንጀለኛ አካሄድ ሳይሆን፣ በማንኛውም መመዘኛ እጅግ ህዝባዊና ሰብዓዊ የሆነ እንቅስቃሴ ነው። ፋኖም አንድና ወጥ የህዝብ ልጅ ነው።

ስማቸውን በመቀያየር የለውጥ ጭንብል ያጠለቁት ተረኛዎቹ የኢህአዴግ ወራሾች የዐማራውን ጥያቄ አንግቦ የተነሳውን ፋኖን ለማጥፋት የሚያደርጉትን የሸፍጥ ስራቸውን አቁመው፣ ለፋኖ መፈጠር ምክንያት የሆኑትን ጥያቄዎች ማስተናገዱ ለሁሉም አንደሚበጅ ልናሳውቃቸው እንወዳለን።

ፋኖ የዐማራን ስነልቦና የተላበሰ፤ የቀደሙት አባቶቻችን የፅናት ተምሳሌት በመሆኑ በዐማራ ህዝብ ልብ ውስጥ ያለ የማንነት መገለጫ እንጅ አገዛዙ እንደሚለው ነጥለው የሚያጠፉት ”ወንጀለኛና ዘራፊ” ባለመሆኑ ”ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ቆቅ ናት ይሏታል” እንዲሉ የፋኖን መዋቅር በኃይል ለመደምሰስ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በዐማራ ህዝብ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመሆኑ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት አጥብቆ ይቃወማል።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በተለይ አሁን አለም ”COVID19” በተባለ ቀሳፊና ተላላፊ በሽታ ተጨንቆ ሰው በርቀት፣ ስይገናኝና ሳይነካካ የመከራውን ጊዜ ያሳልፍ ዘንድ አለም አቀፍ አዋጅ በታወጀበት ወቅት፤ የለውጥ መሪዎች ነን የሚሉት የኢህአዴግ ሰዎች የመንግስትን ስልጣን አንዲይዙ ከፍተኛ መስዋእትነትና አስተዋጽኦ ያደረገውን፤ የዐማራው ህዝባዊ አደረጃጀት አካል የሆነውን ፋኖን ለማጥፋት ጦርነት ታወጆ ነጋሪት እየተጎሰመ ነው። ይህ የሚያሳየው የወያኔ ምስለኔ የነበረው ታምራት ላይኔ በዐማራ ላይ ተሹሞ፣ ዐማራን በአርባ ጉጉ፣ በበደኖ፣ በሀረር ወዘተ በኦነግ እንዳስጨፈጨፈው ሁሉ ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ/ብልፅግና በአዴፓ ሞግዚትነት ዐማራን የማጥቃትና የማጥፋት የተቀነባበረ ሴራ ይዞ ብቅ ማለቱን ነው።

ይህ ፋኖን ለሁለት ከፍሎ ሰላማዊና ሰላማዊ ያልሆነ በሚል ጭንብል እያዘናጉ፣”መግደል መሸነፍ ነው” እያሉ ዐማራን ለማጥፋት መጣደፍ ኢ-ፍትሀዊ የሆነ አሳዛኝና ወቅቱን ያላገናዘበ የጭካኔ ጥግ ነው።

በህዝብ ዘንድ ታማኒነት ሳይኖረው፣ በሠራዊቱ ብዛት ብቻ የተማመነው አገዛዝ፤ የህዝብ ወገን የሆነውም ፋኖን ከመምታቱ በፊት ልብ ገዝቶ ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል። የጦር መንጋ ከተሰማራበት ሰራዊት ይልቅ በህዝብ ልብ ውስጥ በፍቅር ያለው ፋኖ ከጠላት ጋር እየተዋደቀ ሁሌም አሸናፊ ይሆናል። ስለዚህ ይህ በዐማራ ሕዝብ ላይ በኃይልና በግፍ እየተካሄደ ያለው ጥቃት እንደማይሳካ ታውቆ በአስቸኳይ እንዲቆም እንመክራለን።

ከጥፋቱ የማይማረው፤ ስሙን እየቀያየረ ብአዴን/አዴፓ/ዐማራ ብልፅግና በማለት ራሱን የሚጠራው ድርጅት፤ ዐማራ ጠል ለሆኑት የወያኔ አለቆቹ ዱላ ሆኖ ዐማራውን ሲያስጨበጭፍ የኖረ ድርጅት ነው። ዐማራም እንደቀንበር ተጭኖ ፍትህ የነፈገውን አዴፓን በተግባሩ አንቅሮ እንደተፋው ይታውቃል። አዴፓ አሁንም ለተረኞቹ የመደመር/ገዳ ፍልስፍና አራማጆች ሎሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ስለሆነ በለመደው የጥፋት ተግባሩ ቀጥሎበት ፋኖን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት የሚደረገው አንቅስቃሴ መሪ ተዋናይ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።

ስለዚህ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በፋኖ የዐማራ ህዝባዊ አደረጃጀት ላይ የሚደረገው ወታደራዊ አንቅስቃሴ በዐማራው ህዝብ ላይ የተቃጣ መሆኑን አያስገነዘብን፤ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት አካሎች ሰላምና አንድነትን ይደግፉ ዘንድ እንደሚከተለው ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የዐማራ ህዝብ ሆይ፣ አዴፓ ከቤታቸው ወጥተው የማያውቁና እውቀት ሊገበዩ የዩኒቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች፣ በርካታ ልጃገረዶችና ወንዶች ታፍነው እንደወጡ ከቀሩ አራት ወር ተቆጠረ። ወላጆች ጠዋት ማታ እያለቀሱ፣ የልጆቹን ደብዛ ያጠፋውን ወንጀለኛ መፋለም ሲገባው ዛሬም ልጆችህን ሊጨርስ ደግሷል።

አገዛዙ ፋኖን ለማጥፋት በማሰብ ”የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ ወደመጥፎ አቅጣጫ ሊመራ እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሣሪያ ፈትተው እጃቸውን እንዲሰጡ” የሚጠይቀው አስገዳጅ አዋጅ ታውጇል። ጥቃቱ በፋኖ ህልውና ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በዐማራው ህዝብ ላይ ያነጣጠረ አደጋ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሀል። በተለይም የዐማራ ወጣቶች በፋኖ ላይ የተቃጣ ምን ማለት እንደሆነ እንደምትገነዘቡ እናውቃለን። የፋኖ መጥፋት እቅድ የወልቃይትና የራያ ወዘተ ጉዳይ አደጋ ላይ መጣል መሆኑን ከግምት ውስጥ አስገብተን፤ ከጀኔራል አሳምነውና ከነሻለቃ አስቻለው ደሴ ሞት ትምህርት ተወስዶ፤ የሰላም ድርድር የሚባለውን ጨዋታ ከልዩ ሃይሉ ውድቀት ተምሮና ተገንዝቦ ከፋኖ ጎን በመቆም ወረራው የመፋለም ኃላፊነት አለብን።

 

የዐማራ ምሁራን፥ የዐማራ ምሁራን በሚል ስያሜ ፋኖን ለማስመታት መግለጫ ያወጡት ”የአዴፓ ምሁራን” ተግባራቸው ፊደል ከቆጠረ ሰው የሚጠበቅ አይደለም። መግለጫው ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ለባለስልጣናት ያደላ፣ መሆኑን ተገንዝባችሁ፣ እንደዐማራ ምሁር በሳልና ወቅቱን ያገናዘበ ወደሰላም የሚያመጣ መግለጫ በማውጣት ከህሊናና ከታሪክ ተጠያቂነት ትድኑ ዘንድ በትኩረት እንድታዩት በአጽንኦ አናሳስባለን።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፥ አሁን እንደሚታወቀው የበለፀጉት አገሮች ሊቋቋሙት ያልቻሉት፣ ”COVID19” የተባለ በሽታ አለምን እያስጨነቀ ነው። ኃያላን መንግስታት በጭንቅ ላይ ሆነው፣ በስንት ንፅህናና እንክብካቤ፣ በተሟላ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያ ታግዘው በቀን ከ1000 በላይ ህዝብ እየሞተባቸውነው። ትምህርት ቤቶችና ቤተ እምነቶች ከአስከፊው በሽታ ምክንያት ተዘግተው፣ ወላጆች ልጆቻቸውን፣ እህት ወንድሙን፣ ወንድም እህቱን ቁሞ መቅበር አልቻሉም።

በዚህ አስከፊ ወቅት፣ ለህዝብ ቁሜለሁ የሚል መንግስት ዐማራ ክልል ገብቸ ፋኖን ካላጠፋሁ እያለ መዛቱን አይቶ ጉዳዩ ከአለፈው የቀጠለ፣ ዐማራን በኮሮና ወረርሽኝ ጭምር የማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ተረድቶ፣ ከጎናችን እንዲቆም አደራ እንላለን። በተለይ ፋኖ የዐማራውን የህልውና፣ የማንነት፣ የአጽመርስትና የፍትህ ጥያቄዎች አንግቦ የተነሳ ይሁን እንጂ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የማያኮርፍየቀደሙት አባቶቹ ልጅ ነው። እንዲያውም ዐማራው ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ በሰላም፣ በመከባበር፣ በእኩልነትና በአንድነት አንዲኖር ይችል ዘንድ ግቡ ያደረገ ህዝባዊ ተቋም ነው። ስለሆነም ጥላቻን መሳሪያ ባደረጉ ወይኔ፣ ኦነጋውያንና መሰሎቻቸው አይዞህ ባይነት ሰላማዊ ዜጋን በግፍ ከሚገሉና ከሚያፈናቅሉ፣ የሰውን ልጅ ቀጥቅጦ መግደልና ዘቅዝቆ መስቀል ከማይሰቀጥታቸው፣ በይሉኝታ ቢስነት የነሱ ያልሆነን ከሚቀሙ፣ በአጠቃላይ ትልቁ ራዕያቸው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ትንንሽ ሀገሮችን መፍጠር ከሆነ ኃይሎች ጋር ፋኖን ማመሳሰል ዐማራን የማጥፋት ሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ እንዲል እንወዳለን። ፋኖንና የዐማራውን ተጋድሎ ከወንጀለኛው ኦነግና ቄሮለማመሳሰል የሚደረገውን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ወደጎን በማድረግ የዐማራው የህልውና ትግል ለኢትዮጵያ አንደሀገር ቀጣይነት መሰረት መሆኑን በመረዳት ነባር የጋራ አሴቶቻችንን በመያዝ ከዐማራ ጎን በአንድነት እንቆም ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።

የአገራችን የመከላከያ፣ የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች፥ እስከዛሬ ድረስ ስልጣን የያዘ ኃይል ስሙን እየቀያየረ በሰላም ማስጠበቅ ስም ብዙ ደም ሲያፋስስ እናንተም ግዴታ በመወጣት ስም ሌላውን እያጠፋችሁ እናንተም ስትወድቁ ኖራችኃል። መንግስት ህዝቡን እያባላና በሰራዊቱ እያስበላ የሚቀጥለው እናንተ ስትተባበሩት በመሆኑ፣ ከሕዝቡ ጎን ትቆሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በዲያስፖራ የምትኖረው ዐማራ ሆይ፥ አዴፓ ባገር ውስጥ ያለውን የገዢነት ኃይል ተጠቅሞ አማራውን በመንደርና በወንዝ የሚከፋፍልበትን አማራውን የማዳከም ስልቱን ወገናችንንም ላይ እየተጠቀምበት ነው። በተለይም በዲያስፖራ ባሰማራቸው ሆድአደር ወኪሎቹ ፋኖን ወንጀለኛ ለማድረግ የሚለፍፈው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ማንንም ሊያሳስት አይገባም። በተለያዩ የዐማራ አደረጃጀቶች ውስጥ በመሰግሰግ ወይም የራሳቸው እየተቧደኑ፤ በአማራ ምሁራን ማህበርነት፣ በዐማራ ወጣት ድርጅትነት፣ በአማራ ሚዲያነት፣ በተለያዪ የዲያስፖራ ዐማራ ማህበርነት፣ በዐማራ አክቲቪስትነት ስም እማህላችን የተሰገሰጉ የአዴፓን ቅጥረኛ ካድሬዎችን ለይቶ በማወቅና ማንነታቸውን ለወገናችን በማጋለጥ እንታገላቸው። አዴፓንና ቅርንጫፎቹን ከዐማራው ላይ አሽቀንጥሮ መጣል፤ ወያኔ/ ትህነግ፣ ኦነግና መሰል ዐማራ ጠል ኃይሎች በዐማራው ህልውናና ማንነቱ ላይ የጋረጡትን አደጋ ለማስወገድ ለተጀመረው ትግል በድል መጠናቀቅ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ዐማራ ነኝ የሚል ሁሉ በተለይ በዲያስፖራ ያለነው በሚገባ መገንዘብ ይኖርብናል።

 

ለኢትዮጵያ መንግስት፥ ምንም እንኳን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከላይ እስከታች በፌደራል መንግስት ውስጥ ያላችሁ ገዥዎች የዜጋን ሰላምና ደህንነት በዋና ከተማዋ አንኳን ማስጠበቅ የማትፈልጉ፣ ኃላፊነት መቀበል የማትችሉ፣ በግድየለሽነት ሁሉንም ነገር አላየሁም፣ አልሰማሁም፣ ወዘተ በማለት የተለመደ ስልት አድርጋችሁ ልትጠቀሙበት ብትሞክሩም ከተጠያቂነት አታመልጡም። ለሀገር ዳር ድንበር ጥበቃ መዋል ያለበትን ሜካናይዝ የፌደራል ሰራዊት የዐማራው ህዝብ ጥያቄ አንግቦ በተነሳው የፋኖ ተቋምና በዐማራ ህዝብ ላይ ማዝመታችሁ እናንተን ጨምሮ ለማንም እንደማይበጅ አንድታውቁትና ከታሪክ እንድትማሩ እናሳስባለን። ይህ በማድረጋሁች ለሚኖረው የወገን ሞትና የንብረት መውደም በተለይም በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ አንደምትሆኑ በአጽንኦ እንገልጻለን።

 

ዐማራው የህልውና፣ የማንነት፣ የአጽመእርስት እና የፍት ህ ጥያቄዎቹን በትግሉ ያስከብራል!

ሁሉም ዐማራ ለዐንድ አማራ፤ አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ!

ፋኖ ትግል የወለደው የዐማራው የቁርጥ ቀን አለኝታ ነው!

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.