እንኳንም ሞት አለ! – በላይነህ አባተ

banner 2በላይነህ አባተ ([email protected])

ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኮሮና በሽተኛ የአገሪቱ የህክምና አገልግሎቶች ማስተናገድ ስላልቻሉ የጣሊያን ሐኪሞች የህይውት ዘመናቸው የተገባደደውን እየተው ለመኖር ብዙ እድሜ ለቀራቸው አገልግሎት ለመስጠት እንደተገደዱ ዓለም ተመልክቷል፡፡

ይኸንን ህሊናን የሚፈታተን ውሳኔ በበለጠገችዋ ጣልያን የተመለከተ በዘራፊዎች በደኸየችውና በዘር የገመድ ጉተታ በተወጠረቺው ኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችለውን ኢፍትሐዊ የኮሮና ሕክምና ሂደት ታሰበው እንኳንም ሞት አለ ሊያሰኘው ይችላል፡፡ ህሊና ያለውና ከሙያ ሥነምግባር እስከመጨረሻው ያልተፋታ ምሁር ቢገኝ ፍትሀዊ የህክምና አገልግልቶትን በተመለከተ መንደርደሪያ የሚሆን ሐሳብ በታማኝነቱና በተነባቢነቱ በዓለም ተወዳዳሪ የሌለው የኒው ኢንግላድ የሕክምና መጽሔት በዚህ ወር እትሙ አቅርቧል፡፡*

ይህ መጽሔት የሰነዘረውን ሐሳብ ቃል በቃል ሳይሆን ለአንባቢያን በሚገባ መልኩ እንደዚህ ቀርቧል፡፡ የቀረበውን ሐሳብ እንደ መንደርደሪያ መንገድ መጠቀም እንጅ የምዕራባውያንን የሥነ ምግባር ጦማር እንደ ጦጣ ቀድቶ እንደ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም በሕዝባችን ጫንቃ የመጣሉን እውር አኪያሄድ ማስወገድ ይገባል፡፡

የሕክምና አካላዊና መንፈሳዊ እሴቶች ባጠሩበት በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ቅድሚያ አገልግሎት ማግኘት የሚገባው ማን እንደሆነ ለመወሰን የሚከተሉትን መርሆች እንዲመረኮዙ የህክምና ጠበብቶች በኒው ኢንግላንድ የህክምና መጽሔት አስፍረዋል፡፡

  1. የጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ አገልግሎት ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባው ተሌላው ማህበረ ሰብ የተለዩ ስለሆኑ ሳይሆን ቶሎ አገግመው ይህንን ወረረሽኝ ለመታገል የሚያስፈልጉ ኃይሎች ስለሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የጤና ባለሙያዎች እንደ ፊት መሸፈኛ፣ ክትባት፣ የማገገሚያ አልጋዎችና ላቦራቶሪ የመሳስሉ አገልግሎቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
  2. ለመድሀኒት ወይም ክትባት ምርምር መሞከሪያ በመሆን የሚሳተፉ ሰዎችም ቅድሚያ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በበእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደረገው ምርምር ለዓለም ሕዝብ መድህን የሚሆን መድሀኒት ወይም ክትባት ሊፈጥር ስለሚችል የሙከራ ሰዎች ቅድሚያ የህክምና አገልግሎት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይኸንን ማድረጉ ሌሎችም ለመሞከሪያነት በፈቃደኝነት እንዲመዘገቡ ይገፋፋል፡፡
  3. ተቁጥር አንድና ሁለት ውጪ ላሉ በሽተኞች የቅድሚያ አሰጣጡን ጠበብቱ የወሰኑት ጀርሚ ቤንታም የተባለ እንግሊዛዊ ፈላስፋ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በቀመረው ዩቲላተራሊዝም መርህ ተመርኩዘው ይመስላል፡፡ የዩቲላተላዝም ፍልስፍና ከፍተኛ ጥቅም የሚያመጣውን ወይም አብዛኛውን ሰው የሚጠቅመውን ወይም የሚያስደስተውን ተግባር ፈጥም ይላል፡፡ በዚህም መሰረት መጽሔቱ መዳን ለሚችሉ ብዙሐን ወይም ቢተርፉ ብዙ ዓመት ሊኖሩ ለሚችሉ ቅድሚያ ይሰጥ ይላል፡፡ የጣሊያን ሀኪሞች እየተገበሩ ያሉትም ይኸንን ይመስላል፡፡ “እግዜር የመረጠውን ጠርቶ ይውሰድ” በሚባልበት በእኛ አገር ይህ መርህ ዱላ ሊያማዝዝ ይችላል፡፡
  4. ቢተርፉ የመኖር እድላቸው ተመሳሳይ ዘመን ሊሆን የሚችሉ በሽተኞች የህክምና አገልግሎት “ቀድሞ የደረሰ ይውሰድ” በሚል መወሰን እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ ቀድሞ በደረሰ መሆን የሌለበት ምክንያትም ከጤና ተቋማት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ብቻ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን አንፃር ሲታይ ቀድሞ የደረሰ ይታከም ከተባለ ተህክምና አገልግሎት እጅግ እርቆ የሚገኘውን 85% የአገሪቱ ሕዝብ ይሙት ብሎ እንደ መወሰን ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር አገልግሎት አሰጣጡ በእጣ ወይም በሎተሪ መልክ ቢሆን የተሻለ ፍትሐዊ ይሆናል ባይ ናቸው፡፡
  5. የህክምና ቅድሚያ አሰጣጡ ሳይንሳዊ ምርምሮችን የተከተለ መሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ የኮሮና በሽታ ሽማግሌዎቹንና ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸውን የበለጠ እንደሚያጠቃ ሳይንስ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ በኮሮና ተመለከፍ በፊት የሚደረጉት እንደ ክትባት ያሉ መከላከያዎች ቅድሚያ ለእነዚህ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ በኮሮና በጠና ከታመሙ ግን የመትረፍ እድላቸው ስለሚያጠራጥር ከፍተኛ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው አልጋዎች ታክመው ሊዲኑ ለሚችሉ በሽተኞች ቢሆን ይመረጣል፡፡
  6. ኮሮናን ለመቆጣጠር የሚደረገው እርብርብ በስኳር፣ በኩላሊት፣ በጉበት፣ በልብና ሌሎችም በሽታዎች የሚሰቃዩትን በሽተኞች እንዳያስረሳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

አንባቢያን እንደተለመደው “ ድካምህ ከንቱ ነው በኢትዮጵያ ተውጪ ዘመናዊ ሕክምና የሚያገኙት ነፍሰ-ገዳይ ባለስልጣናት፤ በአገር ውስጥም የተሻለውን የህክምና አገልግሎት የሚያገኙት ዘርፈው የከበሩ ዲታዎችና ዘመድ ያላቸው” እንደሚሉኝ ይገባኛል፡፡

አንባቢ ባይነግረኝም ዘራፊና ባለስልጣኖች እያንዳንዱን ገበሬ ማህበር ሆስፒታል ማዳረስ የሚችል ገንዘብ በአውሮጳ፣ አሜሪካ፣ ኤስያና ደቡብ አፍሪካ የቁንጣን ቁርጠት ለመታከም እንደሚደፉ እገነዘባለሁ፡፡ የደፋው ቆብ የሚያስገድደውን ግዴታ መወጣት ቀርቶ ትርጉሙን የሚያውቅ ፓትርያሪክና ጳጳስ በላንባዲና ተፈልጎ የማይገኝበት ዘመን የደርስን መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ሼህ፣ ሃጂና ፓስተሮች ተነፈሰ ገዳዮች ሲወባሩና ሲላላሱ የሚውሉበት ወቅት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ሙያና ሥነምግባር እንደ ተተኮሰ ቀለህና እርሳስ ተለያይተው ምሁራን የነፍሰ ገዳይ ካድሬዎችና ሎሌዎች ሆነው የሚያገለግሉበት ዘመን እደሆነም አውቃለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሶቅራጥስ በቃላቸው ጸንተው እንደ ኢዮብ መከራን እየተቀበሉ የሚኖሩ ጥቂቶች እንዳሉ እገምታለሁ፡፡ እነዚህ ተፍትህና ተእውነት መቃብር በሚያለቅሱት እንባ የህሊና ዓይኖቻቸው የቆስሉ ጥቂቶች ያዳምጣሉ ብዬም አስባለሁ፡፡

ሌላውን ገድለው ወይም አስገድለው መኖር ለሚጓጉ፤ ሌላውን አስርበውና አስጠምተው ዲታ ለመሆንና ሽቅብ ለመሽናት ለሚቋምጡት፣ የሌላውን የመታከም እድል ዘግተው እነሱ ተፈውሰው ረጅም እድሜ ለመኖር ለሚሹ የምለው ስምንተኛ ክፍል ሳለሁ በአማርኛ ክፍለ-ጊዜ ሽንጤን ገትሬ የተከራከርኩበትን ርዕስ ነው:- እንኳንም ሞት አለ!

ነፍሰ-ገዳይ ዘራፊ ባለስልጣን ሆይ! ተባሩድህ የተረፈውን ሕዝብ በኮሮናና በሌሎችም በሽታዎች አስጨርሰህ አንተ ውጪ አገር ለመታከም ታቀድክ ዛሬ ብታመልጠው ነገ አንቆ ሲው የሚያደርግህ እንኳንም ሞት አለ፡፡

በመስቀልህ የማትገዛው ጳጳስና ፓትርያሪክ ሆይ! ተባሩድ፤ ተቆንጨራና ተታቦት ቃጠሎ ተርፈው አስራት የምትቀበላቸው ምእመናን በኮሮና ሲያልቁ ዝም ታልክ ይኸንን የአስራት ድሎትህን የሚነፍግ እንኳንም ሞት አለ፡፡ መንኩሰ ሞተን ረስተህና ለሥጋህ ሳስተህ በጎችህን እያሳረድክ የምትኖር ህሊና አልባ አለማዊ መነኩሴ እንኳንም ሲው የሚያደርግ ሞት አለ፡፡

ሙያህ የሚጠይቀውን ግብረገብነትና ስትመረቅ የማልከውን መሐላ እንደ ቀበኛ ላም ቦጫጭቀህ ነፍስ አጥፊዎችን በማገልገል ላይ ያለህ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ዳኛ፣ መሀንዲስ፣ የምጣኔ ሐብት በላሙያና ሌላህም በሆድህ ተገዝተህ ሕዝብህ ባለቤት እንደ ሌለው ጫካ ሲጨፈጨፍ ዝምብለህ ስለኖርክ እንኳን ሞት አለልህ፡፡ አሁንም ጅብ ተማሪን ሲያፍንና ኮሮናም ሕዝብን ሲጨረግድ ጪጭ ብለህ ተቀረህ እንኳን ቀን ጠብቆ ና የሚል ሞት አለህ፡፡

ሞት ተፊታችን እንደ ክረምት ጨለማ ተገትሮ ምድር ያልቻለውን ግፍ ተፈጠምን ሞት ባይኖር ህዋም የማይችለው ግፍ እንፈጥም ስለነበር እንኳንም ሞት አለ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

*Who Gets Health Resources in a Covid-19 Pandemic? The New England Journal of Medicine  https://www.nejm.org/doi/full/10.1056/NEJMsb2005114?query=featured_coronavirus

 

መጋቢት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

2 Comments

  1. ትንሽ አነጋርህ ስርዓት ቢኖረው(ዘርጣጭ ባይሆን) የምታነሳቸው ሀሳቦች እጅግ ጠንካራ ናቸው፣ስድቡ ግን አላስነብብ አለኝ፣ ቁጭትህን እጋራለሁና ምስጋናዬ ይድረስህ።

  2. Ato Biftu,

    Your comment has no an element of logic what so ever. If you could not read it, how did you know the writer raised very strong concepts?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.