/

ትኩረት ላልተሰጣቸው ቦታዎች ትኩረት ይሰጥ !

banner 2የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በዓለም ላይ በወረርሽኝነት  መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት ያሳወቀው በቅርቡ ነው። ቫይረሱ የሰውን ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ ፣የስልጣን ከፍታ፣  የሀብት  ደረጃ… ሳይለይም  በዚህ አጭር ጊዜያት በከፍተኛ  ደረጃ ተሰራጭቷል።

መጠነ ሰፊ ጉዳትም አስከትሏል። ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 182  የዓለም ሀገራት  በቫይረሱ ተጠቅተዋል። ከ259ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ  መያዛቸው ተረጋግጧል። እንዲሁም ከ 11ሺህ200 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሲሆን 88ሺ535 ሰዎች ደግሞ  ከበሽታቸው አገግመዋል።

ይሄ የሚያሳየው የቫይረሱ ስርጭት ፈጣንና የመተላለፊያው መንገድም ቀላል መሆኑን ነው። ይሄ ዓለምን ያስጨነቀው ቫይረስ  በኢትዮጵያም  ተከስቷል። በኢትዮጵያ  የኮሮና ቫይረስ  መኖር  በመንግስት ይፋ  ከሆነበት  ጊዜ ጀምሮ  ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች  መወሰድ ተጀምሯል።

በዓለም ጤና ድርጅት የተጀመረው የ”ጽዱ እጅ” ዘመቻ  እጅን በአግባቡ መታጠብ የኮቪድ 19ን ወረርሽኝ ለመግታት ቁልፍ መፍትሔ ነው የሚለውን  ምክረ ሀሳብ  በመቀበልም ዜጎች  እጃቸውን  በተደጋጋሚ ጊዜ በሳሙናና በውሃ  በመታጠብ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ የማስገንዘቡ  ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከማስተማሩና ግንዛቤ ከማስጨበጡ ጎን ለጎንም  የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች   እንዲዳረሱ  እየተደረገ ነው። በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት፣  በመንግስት እና በግል ተቋማት  በተለይ አገልግሎት ሰጪ በሆኑ መስሪያ ቤቶች አካባቢም  ተገልጋዮች እጃቸውን እንዲታጠቡ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማዘጋጀት  ቫይረሱን  የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም የህዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው  በዋና ዋና መንገዶች ላይ እጅን በማስታጠብ፣ እንዲሁም ሌሎች  የእጅ ንጽህና መጠበቂያዎችን  በማደል ትልቅ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። ይሄ በጣም የሚያስደስት  ለሀገርም ትልቅ በባለውለታነት የሚቆጠር ነው።

የበጎ ፍቃድ ተግባራትን መፈጸም ለራስም  በጎ ተግባር ለሚደረግለትም ዜጋ የሚያስደስት በመሆኑም ሊበረታታ ይገባል። ይሁን እንጂ አሁን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች  እጅግ አነስተኛ ናቸው። የተጀመረው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ቤተእምነቶች  አካባቢ፣ መድሀኒት  መሸጫ ቤቶች ፣ የገበያ ስፍራዎች… እጅ የማስታጠቡ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል። እጅን ደጋግሞ በሳሙናና በውሀ መታጠብ  ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አንዱ መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው።

ብቸኛ መከላከያ ግን አይደለም። ስለዚህ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ወጣቶች እጅ ከማስታጠቡ ጎን ለጎንም ተጨማሪ በመተላለፊያ መንገዶች ዙሪያ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን እንዲያስተምሩ መደረግ  አለበት። እንዲሁም  በበጎፈቃድ  አገልግሎቱ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለራሳቸውም በቂ  ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት መግለጫ ላይም  የኢትዮጵያ ህክምና ባለሙያዎች እስካሁን  ባልተሟላ ሁኔታና ቁሳቁስ  በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ለመደገፍ ላደረጉት  ጥረት  የመንግስት አድናቆትና ምስጋናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

በሽታው  የሚዛመት ከሆነ በትምህርትም  ሆነ በስራ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች ልክ እንደአገራዊ ግዳጅ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና በሽታውን ለመግታት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። መንግስት በራሱ ስር የሚገኙት ሆስፒታሎች በሽታውን ለመከላከል ዝግጁ እንዲሆኑ  አድርጓል። የግል ሆስፒታሎች በራሳቸው ዝግጅት እንዲያደርጉና አገራዊ ችግሩን በትብብርና በመረዳዳት ለማለፍ ሁለንተናዊ ጥረት ማድረግ ይጠበቃል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ዘመቻን በድል ለመወጣት በዓላማ ፅናት ፤ በስነምግባር ፤ ሃላፊነትን በመረዳትና በአግባቡ በመወጣት፤  በታዛዥነት ፤ በአክብሮት ፤ በታታሪነት  ከሁሉም በላይ ደግሞ በበጎ ፈቃደኝነት  ከመንግሥት  ጎን መቆም ያስፈልጋል። ጊዜው የሚጠይቀውም  ይሄንን  ሀላፊነት መወጣት ነው።

አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.