የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል

banner 2 የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏልበዓለማችን የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተና የሟቾችም ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የግንዛቤ ፈጠራና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየከወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፏል፡፡

ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ማንኛውንም በሽታ ለመከላከል ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የበሽታ መከላከያ መንገዶች ችላ ሳይል አጠናክሮ እንዲተገብር ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ሊደረጉ ከሚገቡ ጥንቃቄዎች አንዱ የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ ነው፡፡ ከጥንቃቄዎቹ ውስጥም፡-
• የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ
• በውኃ እና ሳሙና አዘውትሮ መታጠብ
• ለእጅ ንጽሕና መጠበቂያ የሚሠሩ ኦልኮል ነክ ምርቶችን አዘውትሮ መጠቀም
• ባልታጠበ እጅ ዓይን፣ አፍንጫ እና አፍን አለመንካት
• ቫይረሱን ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገሮች የመጡ ተጓዦች ሆነው የበሽታውን ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አለማድረግ በተጨማሪም ከ 1 እስከ 2 ሜትር ርቀት መጠበቅ
• ስለበሽታው በቂ መረጃ በማግኘት መተግበር ይገኙበታል።
እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከልም በሽታው ወደታየባቸው ሀገሮች የሚሄዱ ተጓዦችና ተጓዦችን ወደሀገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላት ጉዞው እንዲዘገይ ወይም እንዲቋረጥ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ማንኛውም ተጓዦች በሚሄዱባቸው ሀገሮች ሁሉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲተገብሩም ተጠይቋል፡፡

በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አንዱ አካል ሆኖ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያሉ ተግባራትንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ እንዳለው በሁሉም ወደ ሀገር መግቢያ ጣቢያዎች 521 ሺህ 795 በሙቀት መለያ እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሰባቱ መግቢያዎች 299 ሺህ 997 ሰዎች በሙቀት መለያ እንዳለፉና ከነዚህ ውስጥ 7 ሺህ 113 በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሀገራት የመጡ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡

በሽታውን ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት የመጡ ተጓዦች የጤና መረጃ ቅጽ ከመሙላታቸው በተጨማሪ ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ነው፤ ክትትል ያጠናቅቁ 1ሺህ 224 ሰዎች መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡ ሌሎች 9 መቶ 74 ሰዎች ደግሞ የጤና ክትትል ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ 54 ሰዎች የበሽታውን ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸው እና በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሀገራት የጉዞ ታሪክ የነበራቸው በመሆኑ በለይቶ መቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል፤ የ49 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን በማረጋገጡ ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀላቸውን መግለጫው አመላክቷል፡፡ አምስት የበሽታውን ምልክት ያሳዩ ግለሰቦች በለይቶ ማቆያ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።
በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት እስከ መጋቢት 2/2012 ዓ.ም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 113 ሺህ 851 ደርሷል፤ 4 ሺህ 15 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በግዛታቸው መኖራቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ቁጥርም 110 ደርሷል፡፡

መረጃውን ያደረሰችው ራሔል ደምሰው
ያጠናቀረው ኪሩቤል ተሾመ

1 Comment

  1. ኢትዬጵያ ውስጥ ገባ ተባለ ግን በመንግስት የጤና ባለሙያዎች ምንም የሚደረግ የመከላከል ቀድሞ የሚሰራ የዘመቻ ስራ የለም። ህዝብ ብዛት የሚገኝበት ቦታ ባለሙያ መሰራት ነበረበት ግን ምንም የለም። በፋርማሲና በአንዳንድ ቦታዎች የአፍ መሸፈኛ ማስክ፣ ጓንትና አልኮል ማግኘት አልተቻለም። በፈለጉት ገንዘብ ካልሸጥን በማለት መጨከን መንግስት አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት። ዝምታው ጥሩ አይደለም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.