/

የአድዋን ድል ስናስታውስ የሕዳሴን ግድብ ስኬታማ ለማድረግ የዓላማ አንድነት እንፍጠር – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

PDF ያንብቡ…አድዋና ሕዳሴ

የአድዋን ድል ስናስታውስ የሕዳሴን ግድብ ስኬታማ ለማድረግ የዓላማ አንድነት እንፍጠር

አምላካችን የባረከላትን ይህን ኃብቷን (ዐባይን) ለሕዝቦቻቸው ህይወትና ደህንነት ለማዋል እንዲጠቀሙበት ከጎረቤት ወዳጅ አገሮች ጋር በለጋስነት ለመካፈል ዝግጁ ብንሆንም፤ ይህን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚዋ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚና የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴጥቅምት 1957 ..

ነፋስ እንዳይገባባችሁ፤ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ፤ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ። የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንዱ ወገን ቢሄድና ደምበር ቢገፋ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉጠላታችሁን መልሱ፤ እስከ እየቤታችሁ እስቲመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ…”

                አጼ ምኒሊክ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከጻፉት ደብዳቤ የተቀዳ

 

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

aklog birara1
አክሎግ ቢራራ (ዶር)

የአድዋን መቶ ሃያ አራተኛ ዓመት የድል በዓል በሃገር ውስጥና ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እድሜ፤ ጾታ፤ ዘውግ፤ ኃይማኖት ሳይለያየው በደማቅ ነፋስ ሳይገባበት አክብሮታል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ራሳችን ቀና አድርገን በየትኛውም ዓለም ለመሄድና ለመኖር የቻልነው አገራችን ከቅኝ ገዢዎች ባርያነትና ቅጣት ነጻ ሆና የቆየች በመሆኗ ነው። ከላይ በአጭሩ ከእምየ ምኒልክየጠቀስኩት ታሪክ የመዘገበው ምክር ዛሬ በሕዳሴው ግድብ ለተከሰተው እጅግ የሚዘገንን፤ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ  ልክ የአድዋን ጦርነትና ድል በሚያስታውስ ሁኔታ አንቀበልም ብሎ ለቀሰቀሰው ሁኔታ አግባብ አለው። በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረ ጫናና ሴራ እየተካሄደ ነው።

በጉዳዩ ላይ የምንጮኸው ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለንም። የኢትዮጵያና የመላው የጥቁር አፍሪካን ነጻነት፤ መብትና ክብር የሚደግፉ ታዋቂ ግለሰቦችና በአሜሪካ ምክር ቤት ተሰሚነት ያላቸው አባላትም በአሜሪካና በዓለም ባንክ የሚደረገው ጫና በመቃወም ላይ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የታወቁት የሰብአዊ መብት ጠበቃ፤ ሬቨረነድ ጀሲ ጃክሰን የጻፉት ሃተታ የሚመሠገን ነው። በአጭሩ፤ የፕሬዝደንት ትራምፕ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂደው ጫና መቆም አለበት የሚል ነው። በበኩሌ፤ የአሜሪካንና የዓለም ባንክን አድሏዊ አቋም አወግዛለሁ።

የዚህ ሃተታ ዋና ምክንያት፤ የጋራ የሆነውን የሕዳሴን ግድብ ስኬታማነት—የአሁኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትኪረት እና በተከታታይነት የአባይን ወንዝ ባለቤትነት፤ ተጠቃሚነትና ጤናማነት—የምታደገው በጋራ መሆኑን ለማሳሰብ ነው። የተፈጠሮ ኃብቱ ባለቤት እኛው ኢትዮጵያዊያን ነን። በተመሳሳይ፤ ችግሩን ለመፍታት የምንችለውም እኛው ራስችን ነን፤ አሜሪካኖች ወይንም ዓለም ባንክ ወይንም ሌላ ሶስተኛ አካል ሊሆን አዩችልም።

የአሜሪካ አቋም ምንድን ነው?

እንደሚታወቀው፤ በአረብ አገሮችና በእስራኤል መካከል የተፈጥረው ትውልድ ተሸጋጋሪ ተግዳሮት የዓለም የኃይል አሰላለፍን በየጊዜው ሲቀይረው ይታያል። ግብፅ የአረብ ሊግ መሪ ነኝ የሚል እምነት አላት። አሜሪካ ግብፅን የምትደግፍበት ምክንያት በሁለት አስኳል ጉዳዮች ይሽከረከራል፤

 1. በመካከለኛው ምስራቅ፤ በተለይ በአረቡ ዓለም የአሜሪካን ዘላቂ ወታደራዊ፤ እኮኖሚያዊ፤ ዲፕፕሎማቲካዊ ጥቅሞች፤ በተለይ ከራሺያ፤ ከቻይናና ከኢራን ጋር ባላት ፉክክር ዙሪያ አጋር እንዲኖራት በሚልና፤

 

 1. የኢስራኤል ደህንነት ለአሜሪካ ደህንነት ወሳኝ በመሆኑ፤ የኢስራኤል ደጋፊዎች ለፕሬዝደንት ትራምፕና ለቤተሰባቸው የኢኮኖሚ ዘርፍ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማመቻቸት። የውስጥ ተመልካቾች እንደሚሉት ከሆነ የትራምፕ አማች በሕዳሴው ግድብ ድርድር ከፍተኛ የድብቅ ሚና ተጫውቷል፤ ወደፊትም ይጫወታል።

የአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ (ገቢ) ሃላፊ መስሪያ ቤት ድርድሩን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ፤ ከታች በበለጠ የማብራራው የሚለውን ፍሬ ነገር ላቅርበው፤6,000-megawatt የሚገመተው ግድብ ከመሞላቱ በፊት “should not take place without an agreement” ስምምነት ላይ መደረስ አለበት ይላል። ኃብቱ የኢትዮጵያ መሆኑ እየታወቀ፤ እንዴት ኢትዮጵያ ልታዝበት አትችልም ሊባል ይችላል፤ በማን ትእዛዝ፤ ማንን ለመጥቀም፤ ማንን ለመጉዳት? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች አቀርባለሁ።

ከላይ እንዳሳየሁት፤ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ ሁኔታውን ሲረዱት እንዴት ይኼ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይታያሉ። በተለይ ጥቁር አሜሪካኖች።

በዚህ ሳምንት የኔቫዳው የኮንግሬስ አባል ስቲቭን ሆርስፎርድ፤ የአሜሪካ የገንዘብ ሃላፊ የሆነውን ስቲቨን ሙኑችን በኮንግሬስ ስብሰባ በተገኘበት አጋልጠውታል። ይህአይኋዳዊ ነውተብሎ የሚነገርለት ግለሰብ፤ አሜሪካን ወክሎ ከ February 27-28, 2020 ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት የግብጽ፤ ሱዳንና የዓለም ባንክ ብቻ በተገኙበት ስብሰባ ላይ ስብሰባውን መርቷል። ከስብሰባው በኋላ መስሪያ ቤቱ በሰጠው ማስታወቂያ የሚከተለውን አስምሮበት ነበር። “የአሜሪካ መንግሥት የሕዳሴን ግድብ አሞላልና አስተዳደር በሚለከት በአቀነባባሪነት ተሳትፏል። ዓለም ባንክ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጥቷል” ይልና በተጨማሪም፤ “የአሜሪካ መንግሥት ባለፉት አራት ወራት የተካሄዱት ውይይቶችና ድርድሮች ሁሉንም ችግሮችና ተግዳሮቶች ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ ደረጃ ለመፍታት ችለዋል” ይላል።

ኢትዮጵያን ልክ እንደ ቅኝ አገርና እንደ ጥገኛ ያደረገው ድርድርና ውል “ፍትሃዊና ሚዛናዊ” አይደለም። ፍጹም የተዛባና አድሏዊ ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ንቆታል ለማለት እደፍራለሁ። የባሰውን ብሎ፤ ሙንችን የድርድሩና የውሉ መሰረት ግብፅ የተጠቀመችው የቅኝ ገዢዋ የታላቋን ብሪታንያንና በተለይ የ2015 ቱን ስምምነት ነው ይላል። “The foundation of the agreement is the principles agreed between the three countries in the 2015 Agreement on Declaration of Principles (DOP), in particular the principles of equitable and reasonable utilization, of not causing significant harm, and of cooperation.” ፍትሃዊ የሆነ፤ እትዮጵያ የራሷን ወንዝ ድህነትን ለመቅረፍ በሚያስችል ደረጃ ለመጠቀም እንዳትችል የሚያደርግ፤ ኢትዮጵያና ሌሎች የጥቁር አፍሪካ ተፋሰስ አገሮች ያልተሳተፉበት ውል እንዴት ፍትሃዊና ሚዛናዊ እንደሚሆን ሃላፊው ሊገልጽልን አልቻለም።

ግብፅ ይህን ፈለግ ተከትላ ዛሬ አጋሯ ለሆነው ለአረብ ሊግ ያቀረበችው “ድጋፍ” ስጡኝ የሚል ረቂቅ መሰረቱ ተመሳሳይ ቋንቋ የያዘ ነው። ጥሩ ዜና፤ ሱዳን ለውሳኔ የቀረበውን ረቂቅ ስሜ እንዳይገባበት ብላለች። የኢትዮጵያ መንግሥት የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባቱ አግባብ የሌለው ተጨማሪ ጫና መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታትና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ባስቸኳይ ማቅረብ አለበት።

ክብሩ ጠ/ሚንስትር ዶር ዓብይ አህመድ፤ በግብፅና በሌሎች ቁልፍ አገሮች ያሉትን ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጋቸው ጠንካራ ዲፕሎማቲክ እርምጃ ነው፤ በተለይ ከግብፅ።

ግብፅ ውሉን ለመፈረም መዘጋጀቷ ምንም አያስደንቅም፤ የፈለገችውን በአሜሪካ መንግሥትና በዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ድጋፍ ለማግኘት ያስቻላት ውል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ አግባብ አለው። ምክንያቱም፤ ውሉን እንዳለ መቀበል የውጫሌን አደጋ መድገም ይሆናል፤ ኢትዮጵያን የግብፅ እስረኛና ተማራኪ አገር ያደርጋታል። የትሬዠሪን መግለጫ ድምዳሜ ላቅርበው። “ Consistent with the principles set out in the DOP, and in particular the principles of not causing significant harm to downstream countries, final testing and filling should not take place without an agreement.  We also note the concern of downstream populations in Sudan and Egypt due to unfinished work on the safe operation of the GERD, and the need to implement all necessary dam safety measures in accordance with international standards before filling begins. በ 2015 በተደረገው ስምምነት መሰረት፤ የግድቡ አሞላል እና ግምገማ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት መካሄድ የለበትም፤ የግብፅንና የሱዳንን ጥቅም መጉዳት የለበትም፤ የግድቡ ጤናማነት ግድቡ ስራ ከመጀመሩ በፊት መፈተሽ አለበት” ይላል።

ለማጠናከር፤ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ኃብት ነው። የግብፅ አይደለም። ሊፈትሸውና ሊቆጣጠረው የሚገባውና የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው፤ ሶስተኛ አካል ሊሆን አይችልም፤ የሉዐላዊነት ጥያቄ ነው።

የተጠቀሰው ወገንተኛነት፤ አድሏዊነትና ፍጹም ዘረኛነት መርህ ነው። ጀሲ ጃክሰንን፤ ኮንግሬስማን ስቲበን ሆርስፎርድን፤ በአሜሪካና በሌሎች አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ተደጋግፍው የኢትዮጵያን ብሄራዊ መብትና ጥቅም እንዲደግፉ የቀሰቀሳቸው አዲሱ ውል ነው። ስቲበን ሆርስፎርድ ስቲቭን ሙንችንን በቀጥታ የጠየቁት፤ አሜሪካ ለምን አድልዎ አድርጋ ግብፅን ትደግፋለች፤ ከጀርባው ምን መሰረታዊ የአሜሪካ ጥቅም አለ፤ የኢትዮጵያ መብት ለምን ተጣሰ? ወዘተ የሚሉ ናቸው።

የግብፅ መሪዎችና ተባባሪዎች ምስጦች፤ ሴረኞች፤ አጭበርባሪዎች፤ ተንኮለኛች፤ በስለላ የታወቁ፤ ዓላማቸውን ስኬታማ ለማድረግ ጉርሻ (በቅሺሺ) የሚሰጡ መሆናቸው የታወቀ ነው።  የካራ ማራ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት የተደረገው ሴራ ትዝ ይለኛል፤ ግብፅ ነበረችበት። ግብጾች ማስማል ይወዳሉ፤ ቃል ግቡልን ማለት ይወዳሉ። ለማጠናከር የምፈልገው መልእክት፤ ግብጾች ለዓላማቸው ስኬት የማያደርጉት አንድም ነገር የለም የሚለውን ነው። ልክ አሁን እንደሚያደርጉት፤ ሃያላን መንግሥታትን ሙጥኝ ማለት ልምዳቸው ነው። ለነሱ እስከ ጠቀመ ድረስ ጥገኝነት አያስፈራቸውም፤ ለፕሪንሲፕል፤ ለሃቅ፤ ለፍትህ መቆምን እንደ ድክመት ያዩታል።

የአሜሪካው ትሬዠሪ ሃላፊ ሙንችን መግለጫ ከሰጠ በኋላ፤ ፈለጉን ተከትሎ የግብፅ መንግሥት በ March 1, 2020 “ግብፅ ኢትዮጵያ ግድቡን እሞላለሁ ብላ ያወጣችው መግለጫ ተቀባይነት የለውም…ምክንያቱም፤ ኢትዮጵያ በአንቀጽ አምስት የገባችውን ውል የማክበር ግዴታ አለባት” ወይንም ጥሳለች ይላል። “Ethiopia violates the article No. 5 of the 2015 Declaration of Principles, which stipulates that all three countries shall reach an agreement on the rules of filling and operating the dam before starting the process of filling the reservoir with water.” የኢትዮጵያ መንግሥት በድርድሩ ተሳተፈ እንጅ አልፈረመም፤ ቀን ይሰጠኝ ብሎ አማራጭ በማዘጋጀት ላይ ነው። ይህ አቋም ትክክል ነው። እደግፈዋለሁ።

እኔ ብቻ ሳልሆን፤ ስለጉዳዩ ልዩ ዝግጅት አድርገን የሰማኋቸው ባለሞያዎች፤ ሁሉም የአካደሚ ግለሰቦች ደግፈውታል። በዚህ ዙሪያ ጠናካራ የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ጠቃሚ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ላሰምርበት የምፈልገው ግን፤ የአሜሪካና የግብፅ መንግሥታት የዓላማ አንድነታቸውን እየተመካከሩ የሚያደርጉ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ መሆኑን ነው። ያወጧቸው መግለጫዎች የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው። የግብፅ ባለሥልጣናት የአሜሪካን መንግሥት የድጋፍ መግለጫ ተጠቅመው፤ ኢትዮጵያን በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ። ግብፅ ቀን ከሌሊት የሚለፍፈው ስለ ግድቡ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻዎች በሙሉ፤ የአድዋንና የካራ ማራን ድሎች በማስታወስ፤ በሕዳሴ ግድብ የዓላማ አንድነት ድምጽ የማሰማት ግዴታ አለባቸው፤ አለብን።

በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ የምመኘው፤ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አቋም የሚደግፉ  ወይንም የግብፅን የሃላፊነት ደካማነት፤ ወይንም የውሃን አጠቃቀም አውዳሚነት የሚያሳይ ትችት የሚያቀርቡ ሃቀኛ ባለሞያዎች እንኳን በግብፅ መንግሥት፤ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ባለሥልጣናት ሲጠቀሱ አይሰማም የሚለውን ነው። ለምሳሌ፤ ጥቂቶቹን አቀርባለሁ። በ February 25, 2020, የሱዳን የመስኖ ሚንስትር ያሱር አባስ እንዲህ ብሎ ነበር። “ሶስቱ አገሮች፤ ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ 90 በመቶ በሚገመቱ በሕዳሴ ግድብ አሞላል ጉዳዮች ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ብሏል። በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደርም በጉዳዩ ተጠይቆ ሱዳን “ኢትዮጵያን እንደምትደግፍና” ግድቡ ሲሞላ በግብፅም ሆነ በሱዳን ላይ “ጉዳት” እንደማያስከትል ተናግሯል። ስለዚህ አሜሪካና ግብፅ በአንድ ድምፅ “ከፍተኛ ጉዳት” ያስክከትላል የሚሉት ከሳይንሳዊና ቴክኒክ አንጻር ሲታይ  ከእውነቱ የራቀ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ማይክ ፖምፒኦ አዲስ አበባን ሲጎበኙ፤ “የኛ ተልእኮ የራሳችንን መፍትሄ በማንም ላይ ለመጣል አይደለም። ሁኔታዎችን ለመከታተልና ሶስቱን አገሮች እንዲነጋገሩ፤ እንዲወያዩና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ነው” ብለው ነበር። ሆኖም፤ ይህ የውጭ ጉዳዩ ሃላፊ አቋም ከገንዘብ ድርጅቱ ሃላፊ አቋም ይለያል።

ዓለም ባንክ በሞያቸው የተካኑ ግለሰቦች የሚሰሩበት ድርጅት ነው። ግን፤ እኔ የዓለም ባንክ አቋም እጅግ በጣም አሳስቦኛል፤ ለድርጅቱ የወደፊት ሚና እሰጋለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ መላው የዓለም ጥቁር ሕዝብ ስለ ዓለም ባንክ ፕሬዝደንት የግብፅ ደጋፊነት ሲሰማና ወሬው እየተስፋፋ ሲሄድ የድርጅቱ የሞራል ብቃት ጥያቄ ውስጥ ይገባል።  ውሉ አድሏዊ እና ፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን፤ ዘረኝነትን የሚያሳይ መሆኑ ሁኔታውን ያባብሰዋል። የአውሮፓ አባል አገራት “የዓለም ባንክን አቋም በመጠየቅ ላይ ናቸው” ይባላል። ምክንያቱም፤ የተፋሰስ አገሮች በወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ሲጣሉ፤ የድርጅቱ ሚና በሞያና በቴክኒክ የተደገፈ ምክር መለገስ ነው። ገለልተኛ ተመልካች እንጂ አድልዎ የሚያደርግ ድርጅት ሆኖ አያውቅም፤ እስከማውቀው ድረስ።

ዓለም ባንክ ምን ለማድረግ ይችል ነበር?

አግባብ ስለማይኖረው ከሕዳሴው ግድብ ጋር የተያያዙት ጥቂት ምሳሌውችን ብቻ ላቅርብ።

ዓለም ባንክ የግብፅ ችግር የሕዳሴው ግድብ አለመሆኑን በሚገባ ያውቃል፤ ጥናት አድርጓል። ለግብጽስ ምክር ለግሷል። ኢትዮጵያ እስካሁን ያልተጠቀመችበትን የራሷን አንጡራ የተፈጥሮ ኃብት፤ አባይን ገድባ ልማቷን ማፋጠኗ ድህነትን ለማጥፋት ለተመሰረተው ለዓለም ባንክ ተስፋ እንደሚሰጥ ድርጅቱ ያውቃል፤ ጽፏል። ግብፅ እንደምትለው ሳይሆን፤ ግድቡ አደጋ አያመጣም የሚለውን የዓለም ባንክ ባለሞያዎች ያውቃሉ። ዓለም ባንክ ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡ የዘገበውን የግብፅን መሰረታዊና መዋቅራዊ ተግዳሮት ሙሉ በሙሉ ያውቃል። ለምሳሌ፤ የግብፅ የሕዝብ ቁጥር በየስድስት ወሩ በአንድ ሚሊየን ወይንም በዓመት በሁለት ሚሊየን ይጨምራል። በ February 2020, የግብፅ ሕዝብ ቁጥር ከመቶ ሚሊየን በላይ ሆነ። ጋዜጣው ችግሩን እንዲህ በሚል ዘገበው፤ “With little habitable land, deepening poverty and dwindling supplies of water, the future looks bleak. And there is no sign of a slowdown. Egypt’s cabinet said last week that it was on “high alert” to fight population growth, which President Abdel Fattah el-Sisi has described as a threat to national security on par with terrorism. If unchecked, the population could reach 128 million by 2030.” ግብፅ የሕዝቧን ቁጥር ለመቆጣጠር ካልቻለች፤ ፕሬዝደንት አል ሲሲ እንዳሉት፤ ሁኔታው “ለግብፅ ደህንነት ያሰጋል፤ ልክ እንደ አመጸኝነት” ከሚሆንበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። ድህነት እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው።

የግብፅ የውሃ ጭንቀትና በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላት ፍርሃት ከሕዝቧ ጭማሬ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይታያል። ግብፅ ከናየል፤ አብዛኛው ከአባይ ወይንዝ የምታገኘው የውሃ ድርሻ አንድ ጠብታም ከ 55.5 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር በታች እንዳይወርድብኝ ብላ ወደ ጦርነት እሄዳለሁ ብላ ኢትዮጵያን የምታስፈራራው ለዚህ ነው። ዓለም ባንክ ምክር ሲሰጣት የቆየው ግን፤ ልክ የህክምና ባለሞያው ግብጻዊው ዶር አሚር ናዲም ያለውን ነው። “Overpopulation is eating everything…But I don’t feel the government is working all that hard on it.” የግብፅ መንግሥት ትኩረት መሆን ያለበትን ስራ አልሰራም፤ አይሰራም፤ ትኩረቱ ኢትዮጵያ መብቷን አታስከብረም ከሚለው ላይ ነው።

የዓለም ባንክን ምክር ግብፅ ብትሰማና ክሌሎች አገሮች፤ ለምስሌ፤ ከጎረቤቷ ከእስራኤል ለመማር ብትችል ኖሮ፤ ግብፅ ግዙፍ ውሃ ማባከኗን ታቆም ነበር። ብዙ ውሃ የሚያወድመውን የእርሻ ምርት–ሩዝ፤ ስንዴ፤ ፍራ ፍሬ፤ ጥጥ ወዘተ– ታቆም ነበር። ከሜድትራኒየንና ከቀይ ባህር ውሃ እየቀዳች ለማጽዳት ትችል ነበር (Desalination)። አንድ የግብፅ ባለሞያ፤ ፕሮፌሰር ሂያደህ ኤል ኩሲ እንዲህ ብሏል፡፡ “ግብፅ 20 በመቶ የሚገመተውን ውሃዋን ታባክናለች።”

በተመሳሳይ፤ የግብፅ የመስኖ ሚንስትር፤ አብዱላቲፍ ካሊድ በ 2018 ባቀረበው የራሱን ህብረተሰብ ትችት ግብፅ የውሃ ድሃ አገር ናት።  እህል እያመርተች ለውጭ ገበያ ማቅረቧ ልክ ውሃውን (ከኢትዮጵጵያና ከሌሎቹ የጥቁር አፍሪካ የተፋሰስ አገሮች የምትለገሰውን) ኤክስፖርት ከማድረግ አይለይም ወይንም እንደማድረግ ይቆጠራልብሏል።

የፕሬዝደንት ትራምፕ መንግሥትና የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ይህን ሃቅ ተጠቅመው የግብፅን መንግሥት የውሃ አጠቃቀም መርሆዋችሁን የመቀየር ግዴታም አለባችሁ ብለው ለመናገር ለምን አይችሉም?

ይህ  ሁኔታ ምን ያሳያል?

ከላይ እንዳቀርብኩት፤ ኢትዮጵያ ብዙ ወዳጆችና ልትከራከርባቸው የሚያስችሏት ጉዳዮች አሏት።

ግብፅ ሃላፊነቷን ለመወጣት ባለመቻሏ ኢትዮጵያ መቀጣት የለባትም። የሕዳሴው ጉዳይ የተከታታይ ትውልድ ጉዳይ ነው። የሉዐላዊነት ጉዳይ ብቻም አይደለም። የህይወት ጉዳይ ነው። የህልውና ጉዳይ ነው። የብሄራዊ ክብር ጓዳይ ነው። የመለያችን ጉዳይ ነው። የአድዋንና የካራ ማራን ድልና መንፈስ መርህ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውሉን በእምቢተኛነት ማየት አገራዊ ግዴታው ነው። በዚህ አጋጣሚ፤ የትግራዩ ርእሰ መስተዳደር ዶር ደብረጽዮን የአድዋን ድል ትርጉም አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠውን መልእክት እኔም ሙሉ በሙሉ ኣጋራለሁ። ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ የጀመረው የተሃድሶ ግድብ የመላው ኢትዮጵያዊያን ግድብና ጉዳይ ነው።

እኔን በተለይ ያስጨነቀኝ፤ ዶር ደብረጽዮን እንዳሳሰበው ሁሉ፤ የውጫሌው ውል እንዳይደገም ነው። ከተደገመ ግን፤ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግብፅ ትተዳደራለች፤ ቢያንስ ግብፅ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ኃብት የውስጥ አስተዳደር፤ በተለይ በወንዞቿ አጠቃቀም ዙሪያ ጣልቃ ገብታ፤ አሜሪካንና ዓለም ባንክን አጋር አድርጋ የበላይነቱን ይዛ ትኖራለች ማለት ነው።

ኢትዮጵያ የምትፈርመው ውል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፤ ሉዐላዊነት፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ደህንነትና ነጻነት በሚያንጸባርቅ ውል መተካት አለበት። ስለሆነም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያቀርበው አማራጭ ይህን መንፈስ ያንጸባርቃል የሚል ተስፋ አለኝ። በሌላ በኩል፤ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ፤ የአባይን ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ ለማድረግ የሚቻለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘውግ፤ ከኃይማኖት፤ ከጾታ፤ ከኃብት ወዘተ በላይ በማሰብ፤ ለዓላማ አንድነት ተባብሮ የኢትዮጵያን ብሄራዊ መብት፤ ዘላቂ ጥቅምና ብሄራዊ ክብር በመታደግ ነው። እስራኤል ትንሽ አገር ናት፤ የተፈጥሮ ኃብት የላትም። በጠላት የተከበበችና የተበከለች አገር ናት። ግን፤ ራሷን ለማስከበር የቻለችው በመላው ሕዝቧ አገር ወዳድነት፤ ህብረትና ቆራጥነት ነው።

ኢትዮጵያም ቆራጥ፤ ደፋርና ጀግና ሕዝብ የሚኖርባት አገር ናት።

ግብፆች ከፈርዖኖች ዘመን ጀምረው የናየልን ወንዝ፤ በተለይ አባይን ለመቆጣጠር ያላደረጉት ተንኮል የለም። በተከታታይ ኢትዮጵያን ወረው ተሸንፈዋል። የውክልና ጦርነት አካሂደዋል፤ አሁንም እያካሄዱ ነው። የትዮጵያ የባህር በር እንዲዘጋ ደግፈዋል፤ አመቻችተዋል። የኢትዮጵያን ጎረቤት አገሮች አስታጠቀዋል፤ ኢትዮጵያን እንዲወሩ ቀስቅሰዋል።

ይህ ሁሉ ተከታታይ ሴራና ተንኮል ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ ቆይቷል። የግብፅን የናየል ወንዝ የበላይነት ዘለዓለማዊ ለማድረግ ነው። ደካማ፤ የተከፋፈለች፤ በግጭት የተበከለች፤ ድሃና ኋላ ቀር ኢትዮጵያ ለዚህ የበላይነት መሳሪያ ትሆናለች የሚለው መርህ ለግብፅ መንግሥትና ህብረተሰብ የዓላማ አንድነት ፈጥሮለታል። የመካከለኛውን ምስራቅ፤ በተለይ፤ የአረቦችና የኢስራኤል ያልተፈታ ንትርክ የአካባቢውን፤ የሰሜን አፍሪካንና የአፍሪካን ቀንድ የኃይል አሰላለፍ በየጊዜው ሲቀያይረው ይታያል። የሕዳሴ ግድብ ጭቅጭቅ የዚህ አሰላለፍ ክስተት መሆኑን መጠራጠር የለብንም።

ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገቢው እየቀነሰ ሊሰራ የጀመረው፤ ከሰባ በመቶ በላይ የተከናወነው የሕዳሴ ግድብ እክል የገጠመው ለምን ነው?

ግብፅ የተከተለችው ተከታታይነት ያለው የድርድር መሳሪያ ታላቋ ብሪታንያ በቅኝ ገዢነቷ አማካይነት በተለይ ለግብፅ የለገሰቻት ስምምነቶችና ውሎች ለግብፅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት መሰረት ሆኗል። ትኩረት የምሰጣቸው ለሚከተሉት ውሎችና ስምምነቶች ነው።

ተፈጥሯዊ መብት የሚለው የግብፅ አቋም፤ የናይል ወንዝ ፈሰስ፤ አባይን ጨምሮ፤ ከግብፅ ውጭ፤ በማንም ኃይል ለግድብ ሆነ ለመስኖ የግብፅን የውሃ ድርሻ መጠን መቀየር የለበትም የሚል ነው።ታሪካዊ መብትአለኝ የሚለው መርህ፤ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የጥቁር አፍሪካ የተፋሰስ አገሮችን ያገለሉት ስምምነቶች ይህንተፈጥሯዊ  መብት” የሚያንጸባርቅ መርህ ነው። ሁለቱም መርሆዎች በኢትዮጵያ ተከታታይ መንግሥታት ተቀባይነት አግኝተው አያውቁም።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጥናት መሰረት የተጣለው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው። መለስ ብለን ሂደቱን በአጭሩ ብንመለከተው ግብጽ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የጥቁር አፍሪካ የተፋሰስ አገሮችን ሳታማክርና ሳታሳትፍ የሚከተሉትን አቋሟን ያጠናከሩላትን ተግባሮች ተቀናጅታለች። ግብጽ የናይል ባለቤየትእኔ ብቻ ነኝየሚል መርህ ተከትላለች። የችግሩ እምብርት ይኼው ነው።

 1. በ 1929 እ.አ. አ. በታላቋ ብሪታንያ አማካይነት፤ ሱዳንን በማሳተፍ ግብጽ በያመቱ 48 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ውሃ እንድታገኝ ውል ተፈጸመ፤ የቅኝ ግዛት የነበረችው ግብጽ ዋና ተጠቃሚ ሆነች፤ ሱዳን አጋር ሆነች፤ እንግሊዞች አመቻችና ደንጋጊ ሆኑ፤
 2. ይህ ውል ለግብጽ መንግሥት “ታሪካዊ መብት” አለኝ ለሚለው መርህ መሰረት ሆነ፤ “ተፈጥሯዊውን መብት” አጠናከረ፤
 3. እ. አ. አ. በ 1959 ግብጽና ሱዳን የበፊቱን ውል አሻሽለው አዲስና ጠናካራ ውል ተፈራረሙ፤ ይህ ውል ግብጽ ከፍተኛውን የአስዋንን ግድብ እንድትሰራ ፈቀደ፤
 4. በ 1929 ለግብጽ ብቻ ባመት 48 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ውሃ ይገባታል የሚለው በ 7.5 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ውሃ ጨመረ፤ የግብጽ የውሓ ድርሻ መጠን በዓመት 55.5 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ሆነ፤
 5. ሱዳን በፊት ከተሰጣት 4 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር 14.5 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ተጨመረላት፤ በጠቅላላ የሱዳን ድርሻ ባመት 18. 5 ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ሆነ፤
 6. ግብጽ የምትከራከረው ከዚህ የውሃ መጠን አንድ ጠብታ ሊቀነስብኝ አይችልም በሚል አቋም ነው:፤
 7. ሞርሲ ፕሬዝደንት በነበረበት ወቅት፤ የግብጽ የውሃ መጠን ቢቀንስ “ወደ ጦርነት እንሄዳለን” አንዳዝለ እናስታውስ፤
 8. ይህ ሁሉ ድርድርና ውሳኔ ሲደረግ ኢትዮጵያና ሌሎቹ የጥቁር አፍሪካ ተፋሰስ አገሮች ተሳታፊ አልነበሩም።

በተጨማሪ፤ የግብፅ ስትራተጂ ኢትዮጵያን ለይቶ ለማጥቃት ስለነበር፤ የሶስትዮሽ (Triparty Agreement) ማለትም፤ የናይልን የተፋሰስ አገሮች ወደ ጎን ትቶ ግብፅን፤ ሱዳንና ኢትዮጵያን ብቻ የሚያካትት የመርህ አዋጅ (Declaration of Principles/DOP) እ.አ.አ በ 2015 እንዲፈረም አደረገች፤

 1. እነዚህን ተደጋጋፊ ውሎች ኢትዮጵያ ከተቀበለች በራሷ ወንዝና ውሃ ለማዘዝ አትችልም ማለት ነው። ምክንያቱም፤ የኢትዮጵያ ድርሻ ዜሮ ነው፤
 2. በአሜሪካና በዓለም ባንክ ፕሬዝደንት አቀነባባሪነትና ጫና የሚካሄደውን ውል ኢትዮጵያ ከተቀበለች የራሷን የወደፊት ደህንነት፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ የብልጽግና መሰረት እንዲታነቅ አደረገች (Strangulation) ማለት ነው።

ሚዛናዊ ያልሆነ ድርድርና ውል

ዛሬ በድርድሩ ዙሪያ የተከሰተው ጫና መንስኤው ጠ/ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በ March 23, 2015 ከግብፅና ከሱዳን ጋር የፈጸመው ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት “Agreement on Declaration of Principles Between the Arab Republic of Egypt, the Federal Democratic Republic of Ethiopia and the Republic of the Sudan on the Grand Ethiopian Renaissance Dam Project (GERDP)” ይባላል። ስምምነቱ ሲታይ የሚከተለውን ወሳኝና የኢትዮጵያን እጅ የሚያስር አንቀፅ አስገብቷል።

አንቀፅ ሶስት የሚከተለውን ለግብፅ መሰረታዊና ህጋዊም ባይሆን ዲፕሎማቲካዊ መሳሪያ ወይንም መከራከሪያ መሰረተ ሃሳብ አበርክቷል።

III. Principle Not to Cause Significant Harm (ከባድ ጉዳት የማያስከትል ስምምነት)

 • The Three Countries shall take all appropriate measures to prevent the causing of significant harm in utilizing the Blue/Main Nile (ሶስቱም አባል ሃገራት የሚወስዱት እርምጃ ከባድ ጉዳት አያስከትልም)፤
 • Where significant harm nevertheless is caused to one of the countries, the state whose use causes such harm shall, in the absence of agreement to such use, take all appropriate measures in consultations with the affected state to eliminate or mitigate such harm and, where appropriate, to discuss the question of compensation.”

ግብፅ የአሜሪካን መንግሥትና ዓለም ባንክን ተባባሪ በማድረግ የምትከራከረው “ኢትዮጵያ በገባችው ስምምነት መሰረት የሕዳሴ ግድብ ሲሰራና ውሃው ሲሞላ የግብፅን የውሃ መጠን በማይጎዳ መሆኑን ያረጋግጣል ( no significant harm shall occur and that the “affected state” shall “eliminate or mitigate such harm, and where appropriate, to discuss the question of compensation.” ግብፅ የግድቡን መጠን፤ የውሃውን አሞላል፤ የግድቡን ጤናማነት፤ የግድቡን አስተዳደር ወዘተ ይጎዳኛል በሚል መልኩ ካቀረበች ወይንም ወደፊት የሚከሰቱ የአየርና ሌሎች ሁኔታዎች ግብፅን ይጎዳሉ በሚል ስሌት ከተከራከረች፤ በስምምነቱ መሰረት፤ ኢትዮጵያን አጠመደቻት ወይንም አሰረቻት ማለት ነው።  “ከፍተኛ ጉዳት (significant harm) የሚለውን ሃረግ ግብፅ እንደ ፈለገች እየለጠጠች ቅድመ ሁኔታዎችን ለማቅረብ የሚያስችል እድል ሰጥቷታል። ይህ ውል ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷታል።

ኢትዮጵያ ይህን ሚዛናዊ ያልሆነና የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት፤ ግዛታዊ አንድነት፤ ደህንነት፤ ዘላቂ ጥቅምና ክብር የሚፈታተን የሶስትዮሽ ስምምነት በከፊልም ሆነ በሙሉ አልቀበልም ልትል ትችላለች። በዚህ አጋጣሚ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ሆነው፤ ሆነን፤ ልንጠቀምባቸው የሚያስችሉንን መከራከሪያዎች በአጭሩ ላቅርብ።

 1. ኢትዮጵያ ተቀብላቸው የማታወቃቸውን፤ በቅኝ ገዢዎች አማካይነት የተደነገጉትን የ 2029 እና የ 1959 የናይል የበላይነት ውሎች ሙሉ በሙሉ አልቀበልም በሚል መርህ ወጣቱን ትውልድ ማስተማር አለባት፤ እያንዳችን የማስተጋባት ግዴታ አለብን።

 

 1. እትዮጵያ በ 2015 የተስማማችውን ውል (Declaration of Principles or DOP) የራሷ ምክር ቤት ተወያይቶ ስላላጸደቀው አልቀበለውም ወይንም አፍርሸዋለሁ የማለት መብት አላት።

 

 1. ክቡር ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ የወሰዱትን ጠንካራና ብሄራዊ አቋም ሙሉ በሙሉ እየደገፍኩ፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማቲክ አቋም በከፍተኛ ደረጃ የመሩት መሆኑን የዓለም ሕዝብ ስለተገነዘበው፤ የሕዳሴን ግድብብ በሚመለከት፤ የዲፕልማሲው ዘመቻ በጠነከረና ዓለም አቀፍ በሆነ ደረጃ እንዲቀነባበር አሳስባለሁ፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና አምባሳደሮች ትኩረት በጉዳዩ ላይ ቢሆንና ተመሳሳይ መልእክት በየአካባቢው ቢደረግ ተሰሚነት እንደሚኖረው አምናለሁ፤ እያንዳንዳንችን በሞያችን፤ በችሎታችን አስተዋፆ እንድናደርግ ጥሬየን በትህትና አቀርባለሁ።

 

 1. የግብፅ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ለምሳሌ፤ የአረብ ሊግን ድጋፍ መጠየቋ። የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ ተመጣጣኝ፤ ጠንካራ፤ በጥናት፤ በምርምርና በመረጃ የተደገፈ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ ማካሄድ ይጠበቅበታል። ትኩረት የሚሰጣቸው መንግሥታትና ድርጅቶች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል የአውሮፓ የጋራ ማህበር፤ የጥቁር አፍሪካ የናይል ተፋሰስ አገሮች፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ተቋማት፤ የአሜሪካ ምክር ቤት፤ ራሽያ፤ ቻይና፤ እስራኤል።

 

 1. በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ ግብፅ የጠየቀችውን የድጋፍ አቋም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ እንዳያጸድቅና የሱዳንን አቋም እንዲከተል የዲፕሎማቲክ ጫና ማድረግ ያስፈልጋታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአረብ ሊግ የወሰደውን አረባዊ አቋም ማውገዙን አደንቃለሁ።

 

 1. ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ባለሞያዎች ጥናትና ምርምር እያደረጉ የኢትዮጵያን አቋም እንዲደግፉ ብሄራዊ ጥሪ ቢደረግ መልካም ነው።

 

 1. ግብፅ ከፍተኛውን የአስዋንን ግድብና ሌሎችን ግድቦች ስትሰራ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የጥቁር አፍሪካ የናየል ተፋሰስ አገሮችን አለማማከሯን ለመጥቀስ ይቻላል፤ ጉዳዩ የመላው የጥቁር አፍሪካ አገሮች፤ በተለይ የናየል ተፋሰስ አገሮቾ እንዲሆን የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል (Ethiopia must Africanize the issue now)። በዚህም መሰረት፤ ድርድሩ ከአሜሪካ መንግሥትና ከዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ጣልቃ ገብነትና ቁጥጥር ወጥቶ፤ ገለልተኛ የሆነ ግለሰብ ወይንም የመንግሥት መሪ እንዲያስታርቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የቀደሞውን የደቡብ አፍሪካን ፕሬዝደንት ምቤኪን ወይንም የአሁኑን የአገሪቱን ፕሬዝደንት ችግሩን በገለልተኛነት እንዲመሩት ቢያደርግ የተሻለ አማራጭ ይሆናል።

 

 

 1. የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ልኡካን፤ ግብፅ ከአባይና ከሌሎቹ የጥቁር አፍሪካ አገሮች እስካሁን በነጻ ለምታገኘው ውሃ ሁሉ ባለውለታ መሆኗን ጠቅሶ ከአሁን በኋላ ግን፤ ለምታገኘው ውሃ በዓለም ልምድ መሥፈርቶች ተተምኖ ኪራይ መክፈል አለባት የሚል ክርክር ለማቀረብ ይቻላሉ፤ ደቡብ አፍሪካ ለሌሶቶ በያመቱ የምትከፍለው $50 ሚሊየን ኪራይ እንደ ሞዴል ሊጠቀስ ይችላል። ይህ፤ ሌላ አማራጭ የለም የሚለውን ሊመልስ ይችላል።

 

 1. የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን፤ የተለየ ትኩረት በመስጠት፤ ለዓለም ባንክ ቦርድ፤ በተለይ ለአውሮፓና ለኤዚያ አባላት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕዳሴን ግድብ የሚሰራበት ዋና ምክንያት ድህነትን ለመቅረፍ፤ የኢንዱስትሪ ምርት አቅም፤ የስራ እድልን ለማጠናከር፤ እንጨት እየተጠቀመ የሚኖረው ሕዝብ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት እንዲያገኝ ወዘተ መሆኑን፤ ይህም የተቀደሰ ዓላማ ዓለም ባንክ ከቆመለት አላማ ጋር የሚጣጣም መሆኑን፤ በመሆኑም ይህ ድርጅት የኢትዮጵያን የተቀደሰ ፕሮጀክት የመደገፍ ግዴታ እንዳለበት አጠናክሮ ለማቅረብ የሚቻልበት እድል አለ። ውጭ የምንገኝ ባለሞያዎች ለዚህ ግብዓት ለማቅረብ እንችላለን፤ ግዴታችንም ነው።

 

 1. የአሜሪካን ሕዝብ፤ ምክር ቤትና ባለሥልጣናት በሚመለከት፤ የኢትዮጵያ ልኡካንና ዲፕሎማቶች፤ ኢትዮጵያ ግብፅ ከደረሰችበት የልማት ደረጃ፤ ለምሳሌ በነፍስ ወከፍ ገቢ፤ በውሃ አቅርቦት፤ በመብራት አገልግሎት ወዘተ፤ ብትደርስ ለመላው አካባቢ ሰላምና እርጋታ ከፍተኛ አስተዋጾ ሊያደርግ እንደሚችል ማስተጋባት ይችላሉ፤ የጸረ-ሽብርተኛ ትግል አካል የሆነችው ኢትዮጵያ ልማትና ደህንነት ከመላው ዓለም፤ በተለይ ከምእራቡ ዓለም ደህንነት፤ ንግድና ኢንቬስትመንት ጋር የተያያዘ መሆኑን ማሳየት ይጠቅማል።

 

 1. የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ በተገመተው በሰባት ዓመት ብትሞላ ግብፅን ይጎዳል የሚለው የግብፅ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን በተደጋጋሚ በመረጃ ተደግፎ ለዓለም ሕዝብ ይፋ ቢያደርግ ይጠቅማል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መነገር ያለበትና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሆኑ የዓለም ባንክ የማይናገሩት ሃቅ፤ የሕዳሴው ግድብ ኃይል በአንድ ጊዜ ሙሉ አገልግሎት የማይሰጥና በግብፅ ላይ ያለው ጉዳት ዝቅተኛ ወይንም ዜሮ መሆኑ ነው፤ ይህን ሃቅ የአሜሪካ መንግሥትና ዓለም ባንክ የመናገር ግዴታ አለባቸው ማለቱ በቂ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥትና ለኢትዮጵያ መብት የቆምነው ሁሉ፤ ሃቁን የማቅረብ ግዴታ አለብን።

 

 1. ሌላው መከራከሪያ ጉዳይ፤ ግድቡን ለመሙላት እስከ ሃያ ዓመታት (ተጨማሪ) ያስፈልጋል የሚለው የግብፅ ግትር አቋም ኢትዮጵያን በጣም የሚጎዳ አማራጭ ይስተናገድ ከተባለ ግን፤ ኢትዮጵያ በግድቡ የኤሌክትሪክ ሽያጭ በያመቱ የምታገኘውን ገቢ ማን ይከፍላል? የሚል ጥያቄ ቢቀርብ አግባብ አለው። የአሜሪካ መንግሥት፤ ዓለም ባንክና ግብፅ ለኢትዮጵያ በያመቱ ብዙ ቢሊየን ዶላር የሚገመት ካሳ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው? በኔ እምነት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋጋ ከፋይ፤ እዳ ተሸካሚ መሆን የለብበትም።

 

 1. የኢትዮጵያ ልኡካን ከላይ በተራ ሰምንት ለቀረበው ጥያቄ መልስ እንዲሆን፤ ኢትዮጵያ የሚቀርባትን ገቢና ተዛማጅ ወጭ ተምና የአሜሪካ መንግሥት፤ ዓለም ባንክና ግብፅ በጋራ በያመቱ ሊከፍሉ የሚገባቸውን ይኼን ያህል ቢሊየን ዶላር ለመክፈል ተዘጋጅታችኋል ወይ? ብላ በጽሁፍ ለመላው ዓለም ሕዝብ፤ በተለይ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል መንግሥታት፤ ለአውሮፓዊያንና ለሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች የማቅረብ መብት አላትና ይታሰብበት።

 

የሚቀጥል

March 6, 2020

 

 

3 Comments

 1. EXCELLENT ANALYSIS , I HOPE DR. AKLOG BIRARA ADDRESSES HIS VIEWS REGARDING THIS ISSUE TO THE UNITED NATIONS SECURITY COUNCIL WHICH HAS CALLED A BILATERAL INTERVENTION RESPONSE MISSION TO MONITOR THE TRENDS OF THE NEGOTIATION.

  In the meantime let’s not get too carried away, to the point where we minimize the consequences of the Ethio-Eritrean war by reminding ourselves that during the Ethio-Eritrean war 99% of the Eritrean diasporas that were residing in Ethiopia were accused of supporting the Eritrean government at the expense of Ethiopia where those Eritreans were residing in at the time their neighbor country Ethiopia.

  Millions of diaspora Eritreans were put on a bus deported to the Ethio-Eritrean border , with their bank accounts in Ethiopia and other properties confiscated by the Ethiopian government, the deportees crime being supporting the Eritrean government instead of their host country the Ethiopian government.

  Now a little over two decades forward Ethiopian diasporas residing in Israel , Egypt , Arab nations , USA …. are supporting the Ethiopian governments position regarding the GERD at the expense of their host nations.Would this diasporas be subjected to mistreatemennt and end up getting deported with their assets confiscated ? That’s a BIG YES depending on which country.

  WHAT GOES AROUND DOES NOT STAY GONE, IT COMES AROUND, IT IS CALLED CHARMA AND IT CAN BE A PAIN , SO ETHIOPIAN DIASPORAS WAKE UP AND SMELL THE CAPPUCINO DEPENDING ON WHERE WE RESIDE.

  Better to be safe than to be sorry.

  • The honorable Dr. Birara,

   More than the dam, our priority should be to have a country where citizens can move freely, work and live irrespective of their ethnic origin. More than the dam, I care for the 20 or more girls who were kidnapped by OLF and whose whereabout is unknown. Remember, the families of these girls have been crying for the last two months or more. More than the dam, I am concerned about the lawless ness in the country, I care about the lack of justice, I want Joo war who was responsible for the barbaric death of 86 or more innocent Ethiopians to be brought to justice.

   I want the dam to be built but that is not a number one priority. The dam does not give me assurance regarding the continuity of Ethiopia. That is what I want first.

 2. እናት ኢትዮጵያን ከግብጽ ቅኝ ግዛትነት በአንድነት ተባብረን ነጻ እናውጣ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.