ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. / August 26, 2026
ኢትዮጵያ ከውይይት ወደ ሀገራዊ መግባባት መሸጋገር አለባት። ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለአራት ዓመታት ያካሄደው ውይይትና ባለፉት ሳምንታት አራት ሽ ተሳታፊዎችን ያስተናገደው መድረክ ከሽፏል።
የከሸፈበት ምክንያት ከጅምሩም ውይይቱና ምክክሩ የኦህዴድ ብልጽግናን መንግሥት የሚቃወሙ ኃይሎችን ባለማሳተፉ፤ መንግሥት ያቋቋመው ኮሚሽን ከኦህዴድ ብልጽግና ቁጥጥር ውጭ ባለመሆኑና የኦህዴድ ብልጽግናን የማጠቃለል ዓላማ ለመተግበር የተቀነባበረ በመሆኑ ነው። ብልጽግናዎች ያሳተፉትና የተወያዩት ከብልጽግናዎች ጋር ነው።
ነጻና ገለልተኛ አካል ያላስተናገደው ውይይት ዘላቂ እርቅና ሰላም ሊመሰርት አይችልም።
ኢትዮጵያ ግዙፍ የተማረ፤ በልዩ ልዩ ሞያ የተሰማራ የሰው ኃይል አላት። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ልሂቃን ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ አስር አንኳር ጉዳዮችን ላቅርብ።
አንደኛ፤ በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን የጋራ ተነሳሽነት እንዲያሳዩ ወቅቱ ይጠይቃል።
ሁለተኛ፤ ወቅቱ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተን በዓላማ ላይ እንድንመካከር ያስገድዳል።
ለእርቅ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለሕገ-መንግሥታዊ መግባባት የተግባር አቅጣጫ እናቅርብ።
ዋና መልዕክት
ኢትዮጵያ በሰላም የምትቆየው አንዱ ወገን ሌላውን ሲያሸንፍ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ልዩነቶች በኃይል ሳይሆን በሕግ፣ በውይይትና በሕዝብ ፈቃድ የሚፈቱበት ተቋማዊ ሥርዓት ሲገነባ ነው። የዲያስፖራ ምሁራንና ልሂቃን ሚና የወገን ፕሮፓጋንዳን ማጠናከር ሳይሆን፣ እውነትን ማጣራት፣ የሚጋጩ ወገኖችን ማቀራረብ፣ አማራጮችን በማስረጃ ማቅረብ እና ተፈጻሚነትን መከታተል መሆን አለበት።
ሶስተኛ፤ ኢትዮጵያ ከጦርነት አዙሪት መጥቃ እንድትወጣ ስለምንመኝ ወቅታዊ አውዱን መለየት አለብን።
ይህን ለማድረግ የሚቻለው በችግሩ ስፋትና ጥልቀት ላይ የጋራ ግንዛቤ ሲኖረን ነው። የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ፍጹም ወገንተኛ፤ ዘረኛና ቀመኛ፤ አምባገነን፤ ለኢትዮጵያ ብሄራውዊ ጥቅም ጽናት አቋም የሌለው፤ የጋራ እሴቶችን በማምከን ላይ የሚጓዝ፤ ሁሉን ችግር በወታደራዊ ኃይል እፈታለሁ የሚል መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ኦህዴድ ብልጽግና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ኦሮሞውን ጨምሮ የተናቀና የተጠላ መሆኑን አይቀበልም።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2021 ተቋቁሞ ሀገራዊ መግባባት፣ ዘላቂ ሰላምና እርቅ ለማጎልበት ተልዕኮ ተሰጥቶታል። በሐምሌ 2026 በአዲስ አበባ የተጀመረው ሀገራዊ ጉባኤ ከ4,000 በላይ ተወካዮችን አሳትፏል። ኮሚሽኑ ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁን ቢገልጽም፣ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ስለአካታችነት፣ ገለልተኝነትና የአጀንዳ አያያዝ ስጋቶችን አንስተዋል። ስለዚህ የጉባኤውን ውጤት እንደ መጨረሻ መፍትሔ ወይም እንደ ፍጹም ውድቀት ሳይቆጥሩ፣ ለቀጣይ አካታች ሂደት ግብዓት አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያዊያን በተከታታይ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ካውንስል፤ ለአውሮፓ የጋራ ማህበር፤ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ ለአሜሪካ መንግሥት ወዘተ አቤቱታ ማቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ችግር ግን ከድጡ ወደ ማጡ በመሸጋገር ላይ ነው። እኛ ራሳችን ተመካክረን ለመፍታት የማንችለውን አንኳር ጉዳይ የውጭ ተቋማትና መንግሥታት ሊፈቱልን አይችሉም።
አምስተኛ፤ እውነት፣ ትውስታና ተጠያቂነት አስፈላጊ ነው።
ዘላቂ እርቅ የሚጀምረው የተፈጸሙ ጥሰቶችን በመካድ ሳይሆን በጋራ የእውነት ፍለጋ ነው። ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ ከቡድን ወገንተኝነት የጸዳ የእውነት፣ የፍትሕ፣ የካሳና የመታሰቢያ ሂደት ያስፈልጋል። ለዚህ የሚጠቅሙ ሂደቶች የሚከተሉት ናቸው።
ገለልተኛ የማስረጃ ማዕከልና የጥሰት መዝገብ ማቋቋም።
የሽግግር ፍትሕ አማራጮችን በሕዝብ ቋንቋዎች ማቅረብ።
የጥላቻ ንግግርንና የተዛባ መረጃን በማስረጃ መመከት።
ፈቃደኛነት ካለ እነዚህን ለማድረግ የውጭ ተቋማት ወይንም ልሂቃን አያስፈልጉንም።
የምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ ነው አይደለም ወደሚለው ጥያቄ አልገባም፡፤ ንትርክ ይሆናል። ክፍተት እንዳለው ግን ሊካድ አይችልም።
ስድስተኛ፤ ሙሉ አካታችነትና የውይይት ሕጋዊነት ያስፈልጋል።
በጦር ግጭት ውስጥ ያሉ፣ የተቃዋሚ ኃይሎች፣ ተፈናቃዮች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አናሳ ማኅበረሰቦችና ዲያስፖራ በትርጉም ያለው ሁኔታ ካልተሳተፉ የሚወጣ ስምምነት ዘላቂ አይሆንም።
የሚከተሉት ስራ ላይ ቢውሉ ይጠቅማል።
ተሳታፊዎች የሚመረጡበትን መስፈርትና ውሳኔ አሰጣጥ ግልጽ ማድረግ።
የማይሳተፉ ኃይሎችን ለማካተት ገለልተኛ የሽምግልና ቡድን መፍጠር።
በሀገር ውስጥና በዲያስፖራ የሚካሄዱ መድረኮችን በአንድ የምክክር ማዕቀፍ ማገናኘት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርቅና ሰላም ናፋቂ መሆኑን በየመድረኩ ማስተጋባት።
ሰባተኛ፤ የሲቪል ጥበቃ፣ ተኩስ አቁምና የሰላም መሠረት ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።
ውይይት በመድረክ ላይ ብቻ ሊሆን አይችልም። የሲቪል ሕይወት ጥበቃ፣ ሰብአዊ እርዳታ መዳረሻ፣ ተፈናቃዮች በፈቃዳቸውና በደህንነት መመለስ እና የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አስቸኳይ ናቸው።
በሁሉም ግጭት ቀጠናዎች የሲቪል ጥበቃ መለኪያ እና የሕዝብ ሪፖርት ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
ለአካባቢያዊ ተኩስ አቁምና ለሰብአዊ መዳረሻ ቴክኒካዊ ምክር መስጠት ያስፈልጋል።
የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ ማቋቋምና ወደ ማኅበረሰብ ማቀላቀል ላይ ተግባራዊ ንድፍ ማቅረብ ያስፈልጋል።
መንግሥት ዜጎችን በከባድ መሳሪያ እየወጋና እየገደለ የታጠቁ ኃይሎችን በተናጥል መሳሪያችሁን ፍቱ አያዋጣም። መንግሥት በሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን እልቂት ሲያቆም ለድርድር ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል። ሕዝብን እየጨፈጨፉ፤ እያፈናቀሉ፤ እያሰሩና እያሳደዱ እርቅና ሰላም አይቻልም።
የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መንስኤ ሕገ መንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሩ የብሄርና የእምነት ጥላቻን፤ ግጭትን የሚቀስቅስ መሆኑን የውጭ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ውጭ የምንኖረው ልሂቃንና ምሁራን ሃቁን ለመናገር መድፈርና መቻል አለብን።
ስምንተኛ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ስምምነትና የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ አስፈላጊ ሆኗል።
በአብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች የሚነታረኩባቸውና የሚጋጩበት አበይት ጉዳዮች የማንነት፣ የክልል ወሰን፣ የራስ ገዝነት፣ የመገንጠል መብት፣ የአዲስ አበባ ደረጃ፣ የመሬት ባለቤትነትና የሥልጣን ክፍፍል ናቸው።
እነዚህ ጉዳዮች በአንድ ወገን ውሳኔና በመሳሪያ ኃይል ሊዘጉ አይችሉም። በሕዝብ ተሳትፎ፣ በባለሙያ ጥናትና በግልጽ ሕገ-መንግሥታዊ ሂደት መወሰን አለባቸው።
ለዚህ ገንቢ የሆኑ እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዳደረጉት ሁሉ የፌዴራል፣ የክልልና የአካባቢ ሥልጣን አማራጮችን በንጽጽር ማቅረብ ያስፈልጋል። ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት መሆን አለበት።
በመብት፣ በፍትሐዊ ውክልናና በውጤታማ አስተዳደር የሚመዘን ረቂቅ የማሻሻያ አማራጭ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
ሕዝባዊ ምክክርና ሕጋዊ ማጽደቅን ያጣመረ የሕገ-መንግሥት ጉባኤ ሂደት መደገፍ ያስፈልጋል። ይህ አሳታፊ እንጅ ከላይ ወደ ታች ሊሆን አይችልም። በትእዛዝም ሊሆን አይችልም። የሚቻለው ነጻነት ባለበት የሕዝባዊ ተሳትፎ ነው።
የፈረሱት የኢትዮጵያ ብሄራዊ/አገራዊ ተቋማት መታደስ አለባቸው። ከፖለቲካ ቁጥጥር ነጻ መሆን አለባቸው። መላውን ሕዝብና ኢትዮጵያን የሚወክሉ መሆን አለባቸው።
ዘጠንኛ፤ ተቋማት፣ ኢኮኖሚያዊ ፍትሕና የስምምነት አፈጻጸም ወሳኝ ሚና አላቸው።
ሰላም የሚጸናው ነጻ ፍርድ ቤት፣ ታማኝ ምርጫ፣ ሙያዊ የፀጥታ ተቋማት፣ ነጻ ሚዲያ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የወጣቶች የሥራ ዕድል ሲኖሩ ነው። ስምምነት ያለ ጊዜ ሰሌዳ፣ በጀትና ክትትል ባዶ ቃል ይሆናል።
ለማመቻቸት ሊውሉ የሚችሉ መሳሪያዎች የሚከተሉት ናቸው።
የስምምነት አፈጻጸም ሰሌዳ፣ ተጠያቂ ተቋማትና መለኪያዎች ማዘጋጀት።
የክልሎች የገቢ ክፍፍልና የዳግም ግንባታ ድጋፍን በግልጽ መስፈርት ማዋቀር።
የዲያስፖራ ገንዘብና ሙያዊ ድጋፍን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ የቁጥጥር ሥርዓት ማስተዳደር።
አስረኛ፤ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት ያስፈልጋታል? በሚለው ጥያቄ ላይ ውይይትና ስምምነት ያስፈልጋል።
ይህ ማስታወሻ አንድ ተቋማዊ አቅጣጫ ይመክራል። በሕገ-መንግሥት የተገደበ፣ የሰብአዊና የግለሰብ መብቶችን ከቡድን መብቶች ጋር በሚዛን የሚያስጠብቅ፣ ሥልጣንን በፌዴራል፣ በክልልና በአካባቢ ደረጃ በግልጽ የሚከፋፍል፣ ብዙኃን ፓርቲዎችን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ የፓርላማ ሥርዓት ወሳኝ ናቸው።
ነገር ግን “ብሔር ተኮር” ወይም “መልክዓ ምድር ተኮር” ብሎ በቀላሉ መወሰን አይበቃም።
የክልል አወቃቀር፣ የላይኛው ምክር ቤት ውክልና፣ የሕገ-መንግሥት ግምገማ፣ የምርጫ ሥርዓትና የአናሳዎች ጥበቃ በሕዝባዊ ሂደት መደራደር እና ህጋዊ እንዲሆኑ መደረግ አለባቸው።
ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ ጉዳይ መጠበቅ አለበት።
መሻሻል ያለባቸው የሚከተሉትን ሊጨምር ይችላል።
- ፌዴራላዊነትና አካባቢያዊ ራስ-አስተዳደር
- የአናሳ ዜጎች ጥበቃና የውስጥ ተፈናቃዮች መብት
- መሠረታዊ መብቶችና የብዙኃን ፓርቲ ውድድር
- የሥልጣን ሚዛን፣ ግልጽነትና የሕገ-መንግሥት ግምገማ
እነዚህ ግዙፍ አገራዊ/ብሄራዊ ጉዳዮች በፕሮጀክት መልክ እንዲቀርቡና ስራውን ባለሞያዎች ተከፋፍለው እንዲሰሩ ይመከራል።
የ12 ወር የፕሮጀክት እርምጃዎች።
1–3 ወር የምሁራን ገለልተኛ ምክር ቤት፣ የሥነ-ምግባር ደንብና የማስረጃ ማዕከል ማቋቋም።
4–6 ወር ከላይ ከቀረቡት በቅደም ተከተል በያንስ በአምስቱ ጉዳዮች ላይ አጭር የፖሊሲ ጥናቶችና የሚዲያ ውይይቶች ማካሄድ። ውጤቶቹን ለሕዝብ እና ለዓለም ህብረተሰብ ይፋ ማድረግ።
ለዚህ መድረክ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ይህንን እንደ ግሎባል አላያንስ ያሉ ብሄራዊ ተቋማት ሊያመቻቹት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ።
7–9 ወር ከሀገር ውስጥ ተዋናዮች (stakeholders) ጋር ዝግ የመቀራረቢያ መድረኮችና የሕዝብ ምክክር ማካሄድ::
10–12 ወር የሰላምና የሕገ-መንግሥት አማራጭ ሰነድ፣ የአፈጻጸም ሰሌዳና የሕዝብ ሪፖርት ማቅረብ:: ይህን በሜድያ ማሰራጨት። እንዲተገበር ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ።
ማጠቃለያ
“ኢትዮጵያ የምትፈልገው የአንድ ወገን ድል ሳይሆን ሁሉን የሚጠብቅ ሕጋዊ ስምምነት ነው። በውጭ የምንኖር ምሁራንና ልሂቃን እውነትን፣ አካታችነትን፣ የሲቪል ጥበቃን፣ ሕገ-መንግሥታዊ ስምምነትንና ተቋማዊ አፈጻጸምን በጋራ ማጠናከር አለብን።”
የኢትዮጵያ የእርቅ፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ መግባባት ጉዳይ እኛንም ያገባናል። ካገባን መድረኩን የማመቻቸት ግዴታ አለብን።
የሰላምና ሕገ-መንግሥታዊ ውይይት መድረክ እንመስርት።
ማጣቀሻዎች
- የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ. 1265/2021: https://justice.gov.et/en/law/the-ethiopian-national-dialogue-commission-establishment-proclamation/
- Ethiopian National Dialogue Commission, “National Dialogue Conference Concludes Successfully,” Aug. 22, 2026: https://ethiondc.org.et/en/
- Ethiopian News Agency, “Ethiopian National Dialogue Conference Kicks Off in Addis Ababa,” July 15, 2026: https://www.ena.et/web/eng/w/eng_9218541
- Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia (1995), Arts. 1, 45 and 50: https://www.constituteproject.org/constitution/Ethiopia_1994
- የፖለቲካ ኃይሎች ትችትና የአካታችነት ስጋቶች በተለያዩ የሚዲያ ሪፖርቶች ተገልጸዋል፤ በዚህ ሰነድ የቀረበው ግምገማ የኮሚሽኑንና የተቺዎችን አቋም በጥንቃቄ ያስቀምጣል።
የኤዲቶሪያል ማስታወሻ
ይህ ሰነድ የፖሊሲ ሀሳብ እንጂ የማንኛውም መንግሥት፣ ፓርቲ ወይም ታጣቂ ቡድን መግለጫ አይደለም። የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ የሚካሄደው በሕግ፣ በሕዝብ ተሳትፎና በሰላማዊ ሂደት ብቻ መሆን አለበት።
August 26, 2026