ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓም(24-05-2026)
የትግል እርሳሶች
በዛሬው የትዝብት እርሳስ የምፈትሸውና የማቀርበው የሌሎቹን ሁለት እርሳሶች የለውጥ ወይም የፖለቲካ ትግል አይነቶች ዙሪያ የሚመለከት ይሆናል።
የመጀመሪያው የእርሳስ ትግል አንድን አገዛዝ በመሣሪያ ማለትም በጠመንጃ በጥይት እርሳስ ወይም ባሩድ በጦር ሜዳ ተፋልመው ለማሶገድ የሚያካሂዱት ትግል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአይምሮ ውጤት በሆነው በፍልስፍና ፣በአመለካከት ተመርቶ ፕሮግራም ነድፎ በፖለቲካ ድርጅት የሚመራና የሚካሄድ ሰላማዊ ትግል የሚመለከተውን ይሆናል።የዛሬው ትኩረቴና ትዝብቴም በዋናነት በዚሁ የትግል ዙሪያ ላይ ይሆናል።
በአገራችን የረጅም የትግል ታሪክ ውስጥ በጠመንጃም በሰላማዊ ትግልም በኩል ብዙ መስዋእትነት እንደተከፈለ አይካድም።ሆኖም ግን ለምንፈልገው የስርዓት ለውጥ አላበቃንም።ላለመሳካቱ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋናው በተጀመረ ትግል ቁርጠኝነትና ጽናት ባለመኖሩ እንደሆነ መካድ አያስፈልግም።በወረትና በሆይሆይታ ብሎም በጠባብ እይታና ፍላጎት ስለሚዋጥ ትግሉ ሳይራመድና ከግቡ ሳይደርስ ከውስጥም ከውጭም በሚነሱ ድክመቶች ተሰናክሎ ወይም ተሽመድምዶ ቀርቶ ለአምባገነኖች አገዛዝ ዕድሜ ቀጥል ሆኗል።
አሁንም የሚታዬው ድክመት ከዚያ የተለዬና የራቀ አልሆነም።አሁን ላይ በጫካ መሣሪያ አንስቶ ከሚታገለው ለውጥ ፈላጊ ወገን ጎን ለጎን በጎሰኝነት ተሰልፎ አገር ለመበታተን የተነሳም ታጣቂ የሚንቀሳቀስበት እንዲሁም ሕዝብ አስገድዶ የሚዘርፍና ንብረት የሚቀማ የሚያወድም ወንበዴም የሚተራመስበት ጊዜ ላይ እንዳለን ማንም የማይክደው ሃቅ ነው። ከዚያም ውጭ በከተማ የሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶች ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። አገዛዙ ሳይወድ በግድ ለማጭበርበሪያም ቢሆን በከፈተው ሕጋዊ የትግል መስክ ተጠቅሞ አገዛዙን ወጥሮ በመያዝና ሕብረተሰቡን በመቀስቀስ በሰላማው መንገድ ፣ሳይ ገሉና ሳይሞቱ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉበትን መንገድ የመረጡ መኖራቸውን እያዬን ነው። እነዚህ ቡድኖች የምርጫ ሂደት ከተፈጠረና ዕድሉ ከተገኘ በድምጽ በሁለተኛው እርሳስ መዋጋትና አገዛዙን አሸንፎ ማሶገድ ይቻላል፣ያም በብዙ አገሮች የታዬና የተፈተነ የትግል አይነት ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።
እርግጥ ነው አምባገነን አገዛዞች ፈልገው ከሥልጣን አይወርዱም፤ሁሉንም መንገ ይጠቀማሉ፤ ይገላሉ፣ያስራሉ፣ ያቆስላሉ፣ ያሳድዳሉ፣ ያስርባሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ የውጩን ትኩረት ለመቀዬርም ከልባቸውም ባይሆን የማስመሰል የምርጫ ስልት ይጠቀማሉ።ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ የሚፈልጉትን ለውጥ ለማምጣት መሞከር ብልህነት እንጂ ከጅልነት አይቆጠርም። በአገዛዙ ዛቻና ተንኮል እንዲሁም ከውጭና ከውስጥ በሚጎነጎን ሴራና ማስፈራራት ሳይበገሩና ሳይንበረከኩ በሁሉም የትግል ሜዳ ከመቀጠል በቀር ሌላ አማራጭ የለም።።ለዚያ ደግሞ ተበደልኩ፣መብቴ ተገፈፈ፣ ቤተ ፈረሰ፣ ተፈናቀልኩ፣በድህነትና በርሃብ አለንጋ ተገረፍኩ፣ልጄ ተራበ ፣አገሬ በጎሰኞች ልትፈራርስብኝ ነው፣…ወዘተ የሚለው ሕዝብ ጉልህ ሚና ሊጫወትና ሃላፊነቱን ሊወጣ የሚችልበት ሰፊው መንገድ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል።እቤቱ በመቀመጥ ወይም በጥቂቶች መስዋእትነት የምፈልገውን አገኛለሁ ብሎ ከዳር ሊቆም አይገባውም።ከዳር ከቆመና ተመልካች ከሆነ ለአገዛዙ ደጋፊና ተባባሪ መሆን ማለት ነው።
በልዩ ልዩ መንገድ አገዛዙን ወጥሮ በመያዝና መፍለክለኪያ በማሳጣት ፣የሕዝብም ተቀባይነት እንዳይኖረው አሽመድምዶ ለማሶገድ የሚደረገው የምርጫ እርሳስ ትግል ትልቁን ወሳኝ ሚና የሚጫወት ይሆናል።በዚህኛው የእርሳስ ትግል ውስጥ የሚጠቃለሉት ትግሎች አመጽ አልባ በመባል ይታወቃሉ።ከነዚያም መካከል የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው።
በኪነት መልክ በሙዚቃ፣በመዝሙር፣ በዘፈንና ሽለላ በድራማና በትያትር ፣በስነጽሁፍ፣በፕሮፓጋንዳና የማጋለጥ ዘመቻ የሚደረገው ትግል የእርሳስ ትግሉ መገለጫዎች ናቸው።
በሕዝባዊ እምቢተኝነት መልክ ደግሞ በተቃውሞ ሰልፍ፣በሥራማቆምና መለገም አድማ መምታት፣ግብር ባለመክፈል የአገዛዙን ግብአት በመገደብ፣ የኤኮኖሚው ምንጩን በማድረቅ፣ለጸጥታ ሃይሎችና ለአገዛዙ ክብርዘበኞች የሚውለውን የገንዘብ መዋጮ በማሳጣት…ወዘተ የሰላማዊ ትግሉ ማለትም የእርሳስ ትግሉ አካል የሆኑትን ማፋፋም ሌሎቹ ናቸው።
ስለአመጽ አልባ የለውጥ ትግል በዓለምአቀፉ ግንዛቤ የሚከተለውን ይመስላል። በእንግሊዘኛ የቀረበ ሲሆን የትርጉም ስህተት እንዳያስከትል በማለት በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱትን የትግል አይነቶች ያጠናከረና ተመሳሳይ ስለሆነ እንዳለ ማስቀመጡን ወርጫለሁ።
“A nonviolent Revolution is a revolution conducted by unarmed civilians using tactics of civil resistance ,including various forms of nonviolence protest,to bring about the departure of governments seen as entrenched and authoritarian without the use of threat of violence. While many campaigns of civil resistance are intended for much more limited goals than revolution, generally a nonviolent revolution is characterized by simultaneous advocacy of human rights ,and national independence in the country concerned.
An effective campaign of civil resistance ,and even the achievement of a nonviolent revolution may be possible in a particular case despite the government in power taking brutal measures against protesters ……”ይልና በመቀጠል የትግሉን ሂደት ቀጣይ ምእራፍ ወይም ደረጃ በአንዱ ተራቁጥር ላይ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል።
“ Confrontation : organized and sustained campaigns of picketing,strikes ,sit-ins,marches,boycotts,die-ins,blockades to disrupt business as usual in institutions and government.By putting one’s body on the line nonviolently the rising movement stops the normal gears of government and business.”
ከላይ ያሰፈርኩትን እንደመንደርደሪያ አድርጌ አሁን በአገራችን ወዳለው የተለያዩ ትግሎች ስገባ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር የሚታገሉትን አራት ድርጅቶችና ሌሎቹንም በተመለከተ የሚሰነዘሩ ትችቶችን በተለይም የኢሕአፓን የትግል አካሄድ በሚቃወሙና በሚደግፉት በኩል የተነሱትን አስተያዬቶች ትኩረት በመስጠት ሃሳቤን ለመማካፈል እወዳለሁ።ምክንያቱም በሚያካሂደው ትግል በተለይም ምርጫውን አስመልክቶ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ከውስጥና ከውጭ የገጠሙት ችግሮችና ተቃውሞዎች ምንና ምንስ ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ጥቅምና ጉዳታቸው ምን እንደሚመስል ለማሳዬት እሞክራለሁ። አንድን ነገር በጭፍን ከመደገፍ ወይም ከመንቀፍ ይልቁንስ በምክንያት የተደገፈ ነቀፋና ድጋፍ ቢሆን ውጤቱ ያማረና ትክክለኛ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ከስህተትና ከጸጸትም ያድናልም እላለሁ።
ወደ ኢሕአፓ ዝርዝር ታሪክ ከመግባት ተቆጥቤ አሁን ከአገዛዙ ጋር የሚያደርገውን ግብግብ ስመለከተው አንድ በሰላማዊ ትግል እሳተፋለሁ ብሎ የተነሳ የፖለቲካ ድርጅት የሚከተለው የትግል አቅጣጫ መሆኑን እረዳለሁ። የሰላማዊ ትግል ደግሞ ከላይ እንደተብራራው ሁሉንም መንገድ ማለትም በምርጫም ቢሆን አገዛዙን ለማስወገድ በሚረዳው ሁሉ መሳተፍን ያጠቃልላል፤ከዚያም አንዱ በምርጫ በእርሳስ አሸንፎ መውጣት ይሆናል።ይህንን በመቀበል ነው ደጋፊዎቹ ሁሉ አብረውት እስከአሁን ድረስ የዘለቁት ባይ ነኝ።
ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን የሰላማዊ ትግሉን አካል የሆነውን የምርጫ መሳተፍ ከያቅጣጫው ደጋፊና አማካሪ ከተባሉት በኩል ሳይቀር ተቃውሞ ገጥሞታል።በጫካ በመሣሪያ ከሚፋለመው አንስቶ በአገዛዙ በኩል ለመከፋፈልና በጥቅም በመደለል ብሎም የጥቃት እርምጃ እንደማስፈራሪያ ተደርጎ ከምርጫው እራሱን እንዲያገል ብዙ ሙከራዎችና ተጽእኖዎች እዬተወሰዱበት መሆኑን ታዝቤያለሁ።
እንደ እኔ ግንዛቤ የጫካው የትጥቅ ትግልም ሆነ የከተማው ሕጋዊ ወይም ሰላማዊ ትግል የዓላማ ልዩነት እስከሌላቸው ድረስ እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ እንጂ የሚፏከቱ መሆን አለባቸው አልልም፤መሆንም የለበትም።የገጠሩ ከከተማው ነዋሪ ሕዝብ ትግል ጋር ካልተያያዘና ሁለግብ ትግል ካልተካሄደ ውጤቱ መሸነፍ ወይም ለሌላ ዙር አምባገነናዊ አገዛዝ መደላድል መፍጠር ይሆናል።
በምርጫ መሳተፍና አለመሳተፍ የሚሰጠውን ጥቅምና የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ የሚከተሉት ሃሳቦች ተጋርጠውብኛል።
በምርጫው መሳተፍ የሚሰጠው ጥቅም
1 በተከፈተው ዕድል ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ይረዳል(በቅስቀሳ ወቅት የተደረጉት በሚድያ የክርክር መድረኮች ዋቢ ናቸው።
2 በክርክር ወቅት እንደታዬው የአገዛዙን ገመናና ድክመት ለሕዝብ ለማሳወቅ ተጠቅሞበታል
3 ለአገራችን የሚበጀው የፖለቲካ መንገድና ስርዓት ምን መሆን እንዳለበት አማራጭ ለማቅረብ ፤የዴሞክራሲን አሠራር ሰጥቶ መቀበልን በማስተማር ከተደጋጋሚ በጠመንጃ የመገዳደልን ፖለቲካዊ ባሕል ለመለወጥ ና በሰለጠነና በቆራጥ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አስተምሮበታል።
4 የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለሰላማዊ ትግሉ ድጋፍና እርዳታ እንዲያደርግለት በር ይከፍታል።
4 ሕዝቡ ደፍሮ ለመብቱ እንዲቆምና እንዲታገል በመሪነትና በምሳሌነት ሚና ተጫውቷል።
5የሰላማዊ ትግል ደጋፊ የሆነው የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለትግሉ ድጋፍና እርዳታ እንዲያደርግለት በር ይከፍታል።የአገዛዙንም መሰሪ አካሄድ እንዲረዳው ያደርጋል።
6 የሕዝቡን እውነተኛ አቋምና ለለውጥ ያለውን ፍላጎት ለማወቅ ይጠቀምበታል።
በሰላማው እርሳሱ አገዛዙን ለማሶገድ ያልደፈረ ሕዝብ ወይም ለውጥ ፈላጊ ጫካ ገብቶ በመሣሪያ እርሳሱ ለመታገል ይደፍራል ተብሎ አይጠበቅም።
በምርጫው አለመሳተፍ ደግሞ የሚያመጣው ጉዳት የሚከተለው ይሆናል
1 አገዛዙ ካለምንም ተቃዋሚና ተወዳዳሪ ሜዳውን ብቻውን እንዲጋልብበት ይረዳዋል
2 ሕዝቡን የሚያደራጅና በትግል የሚመራ ድርጅት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል።
3 በምርጫ አንሳተፍም የሚሉት ድርጅቶች ሕጋዊ እውቅናቸውን በምርጫ ቦርድ ተብዬው ውሳኔ እንዲያጡና እንዲሰረዙ ያደርጋቸዋል ።ዳግም ለማንሰራራትም ይከብዳቸዋል፤ካለፈው የቅንጅት ተመክሮና ከሰሞኑ የደቡብ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሰነጣጠቅ ማዬት ይቻላል።
4 የድርጅቱ አባላት ሰላማዊ ትግሉን በመተው በጸረ ዴሞክራሲነትና በሽብርተኝነት ተወንጅለው እንዲታሰሩ ምክንያት ይሆናል።
እነዚህ ከሞላ በጥቂቱ የሚከሰቱ ችግሮች ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።
ስለሆነም ያለው አማራጭ ኢሕአፓም ሆነ ሌሎቹ የትብብር አባል ድርጅቶች በያዙት ዓላማ ጸንተው ቢሸነፉም ቢያሸንፉም የሰላማዊ ትግሉን እስከጫፍ ማድረስና በምርጫው መሳተፋቸው የተሻለ ነው፣ሌላው ቢቀር በቃል የመጽናትን ትርጉም ማሳዬቱ ቀላል አይሆንም።ይህ ማለት አገዛዙን አጅባችሁ ተጓዙ ከሚለው የተለዬ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።አገዛዙን በአዬር ላይ ሳይሆን በመሬት ላይ ለዚያውም የእኔ ነው በሚለው የትግል ወረዳ በመጣበት መንገድ መግጠም የደፋሮች ሙያ ነው።በምርጫው መሳተፍ ኢትዮጵያውያን ለሰላማዊ ትግሉም ባዳና እንግዳ ወይም ጸር አለመሆናችንን ማሳዬቱ በራሱ አንድ ትርፍ ነው።
አሁን ከውስጥና ከውጭ ከምርጫው እንዲወጡ የሚቀሰቅሱት ስብስቦችም ሆኑ ግለሰቦች በእሳት ላይ ተቀምጠው ትግሉን ከሚመሩት ሰዎች በላይ ሊወስኑ አይችሉም።የድርጅቱ አመራርና አብዛኛው አባል የተቀበለውንና የተስማማበትን ማክበር የቀና ደጋፊ ድርሻ ነው።አባላቱን ለመከፋፈልና ከምርጫው ጨዋታ ለማሶጣት በሆነ ባልሆነው መንገድ አገዛዙ እንደሚሞክረው መታወቅ አለበት። ለውጥ ፈላጊው ምርጫ መካፈል ማለት መሸነፍንም መቀበል ማለት እንደሆነና የትግል መጨረሻም እንዳልሆነ ሊገነዘበው ይገባል።በተለይም በውጭ አገር ተቀምጦ በአገር ውስጥ ህይወታቸውን አሲዘው የሚታገሉትን በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ ለማለት ማንም የሞራል ብቃት የለውም።ሲሆን በርቱ ብሎ መደገፍና በጎደለ መሙላት አለያም አማራጭ የተሻለ የትግል መንገድ መጠቆም የወዳጅ ተግባር ይሆናል፤ ነውም። የሚድህን ወፌ ቆመች ብሎ እጁን ይዞ መርዳት እንጂ ዓይንህ ይፍሰስ ብሎ ወይም ገፍቶ መጣል አይገባም።ሕዝቡን የሚመራ ድርጅት የለም በማለት የተፈጠሩትን ደግሞ እንዳይንቀሳቀሱ ጋሬጣ መሆን እርስ በርሱ ይቃረናል።
የጠመንጃ እርሳስ፣ የመምህራን እርሳስና የምርጫ እርሳስ የጨበጠው የኢትዮጵያ ለውጥ ፈላጊ ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለጋራ ድል እንዲበቁ እመኛለሁ!
ወደው ሳይሆን ተገደው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ህይወታቸውን በጦር ሜዳ በመገበር ላይ ላሉት ወገኖቼም ትግላቸው ከከተማው ትግል ጋር ተቆራኝቶ በድል አድራጊነት የአገራቸውን ሰላምና አንድነት ለማዬትና ሰላማዊ ኑሯቸውን ለመምራት እንዲበቁ ያለኝን ታላቅ ምኞት ልገልጽላቸው እወዳለሁ።
ድል ለባለእርሳሶች ይሁን!!
አገሬ አዲስ