December 8, 2024
40 mins read

ግልፅ ማስታወሻ ለፕሮፌሰር ዓለም አንተ ገ/ሥላሤ – ከአንዳርጋቸው አሰግድ

ጁባ፣ ኅዳር 2017
ደቡብ ሱዳን

አንዳርጋቸው አሰግድ
አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ

ትውስታዎቼ፡ ስለ መሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ የኃይሌ ፊዳን እና የኔን ስሞች ያወሱባቸውን ገፆች ጓደኞቼ ልከውልኝ ደረሱኝ። ከዚያም፤ ናሁ ለሚባለው መድረክ ኅዳር 29 ዕለት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ፣ ተከታተልኩ። ትውስታዎችዎ ብዙ ብዙ እንደሚያስታውሱ ስለምገምት፣ መፅሐፍዎን አግኝቼ በጥሞና አነባለሁ። እስከዚያው ድረስ፣ ይህቺን ግልፅ ማስታወሻ ልኬሎዎታለሁ። ከትውስታዎችዎ መካከል ሦስቱ ስህተት ስለሆኑ፤ እንዲታረሙ ለመጠየቅ ነው።

 

መ/ቤቱን ስለተቀላቀልኩበት ሁኔታ እና ጊዜ

በትክክል እንዳስታወሱት፣ በመ/ቤቱ ለመቀጠር እርስዎ ዘንድ ቀርቤ አመልክቼ ነበር። ዕለቱ ቢዘነጋኝም፣ በጥቅምት 1967 አጋማሽ ወይንም መጨረሻ ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። ቅጥር የታገደ መሆኑን ገልፀውልኝ ተመለስኩ። ሆኖም አስከትለው እና “ስለዚህ” ብለው የሚከተለውን አከሉ።

“ስለዚህ፣ አዋጁ በሚረቀቅበት ጊዜ አንዳርጋቸው የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ አልነበረም። መሬት ይዞታ ውስጥ መቀጠር የቻለው፣ አዋጁ ከወጣ በኋላ ሕጉን ለማስፈፀም በየክፍለ ሀገሮችና በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉ ሰዎች በብዛት በሚያስፈልግበት ጊዜና ደርግ የልጅ እንዳልካቸውን የአዲስ ሰው ቅጥርን ካነሳልን በኋላ ነው። አንዳርጋቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች አንዳርጋቸው የጠቀሳቸውን ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይን፣ ዮሴፍ አዳነን እና ዮሐንስ (ዲማ) ነገዎን የቀጠርናቸው አዋጁ ከወጣ ከወራት በኋላ ነው” (ገፅ 89)።

የልጅ እንዳልካቸው የቅጥር እገዳ የተነሳው እርስዎ እንዳሉት “አዋጁ ከወጣ ከወራት በኋላ” አልነበረም። አቶ ዘገዬ አስፋው በኅዳር 1967 የመ/ቤቱ ሚኒስትር ሆነው እንደተሾሙ እና መ/ቤቱ አዋጁን ለመተግበር የሚይስችሉትን ዝግጅቶች እንዲፈፅም በደርግ በተፈቀደላቸው ጊዜ ነበር። አቶ ዘገዬ የተሾሙበትን ጊዜ በሚመለከተው፣ “መርማሪ ኮሚሽን” ይባል የነበረው ተቋም በወሎ ለደረሰው የረሀብ ዕልቂት በኃላፊነት የሚጠየቁ ሰዎችን ዝርዝር ኅህዳር 4፣ 1967 ዕለት አሳወቀ። እርሳቸው ኅዳር 5 ዕለት ሲያዙ፤ አቶ ዘገየ አስፋው ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

ዝግጅቱ በአንድ በኩል፣ በአቶ በለጠ ገ/ፃድቅ ዘመን የተሠራውን ረቂቅ ማጠናቀቅ እና በደርግ ማስወሰን ነበር። በሌላ በኩል፣ የመ/ቤቱን የሰው ኃይል ማጠናከር፤ የክ/ሀገራት ቢሮዎቹን ማዋቀር፣ ማደራጀት እና ማቴሪያላዊ ግዢዎችን መፈፀም ነበር። አቶ ዘገዬ ይህንኑ፣ “Land to the Tiller – An interview with Zegeye Asfaw” በሚል ርዕስ በታተመው መፅሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው አስታውሰዋል።

“(I) was given authority to hire up to a Master’s level without the Central Personnel Agency. So, I could hand-pick to the level of a Master’s degree without any problem. I was also given authority to purchase vehicles without going through the cumbersome process of applying to the Ministry of Finance. This was especially for the Land Reform. In this case we were going to avoid all red tape, and the Derg government had decided that all the restrictive rules were not applicable.

“We hired battalions of very enthusiastic young people. At this time, there were some highly innovative young women and men in the Ministry of Land Reform” (Ann Oosthuizen, Morfa Books, June 2020, ገፅ 41).

አርስዎም ይህንኑ፣ እኔን እና የዘረዘሯቸውን ሌሎቹን “የቀጠርናቸው ደርግ የልጅ እንዳልካቸውን የአዲስ ሰው ቅጥርን ካነሳልን በኋላ ነው” በማለት አስታውሰዋል። ያንን የሚያክል አዋጅ ያለቅድመ ዝግጀት ሊታውጅ የሚችል አዋጅ እንዳልነበር፣ ግለፅ ነው። የመ/ቤቱን የክ/ሀገራት ቢሮዎች ኃላፊዎችን እና ሠራተኞችን ለመመልመል የነበረው ጥድፊያ እና ርብርብም፤ የሚታወስ ነው።

አያይዘን ካጤንነው ደግሞ፤ በታኅሣስ 1967 የታወጀው የዕድገት በኅብረት ዘመቻም፣ የዝግጅቱ አንድ አካል ነበር።

የኔን በሚመለከተው፣ በኅዳር መጨረሻ ወይንም በታኅሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ከመ/ቤቱ ተደውሎልኝ ተጠራሁ። ከመ/ቤቱ ስደርስ ሌሎች ሁለት ተጠርተው ስለነበር፤ እዛው ተገናኘን። በተለይም የገበሬ ማኅበራትን አደረጃጀት በሚመለከተው እንድንተባበር ተጠየቅን። እኔ ጥያቄውን ተቀብዬ ለመተባበር ተስማማሁ። ዕውነታው ይኼው ነው።

 

ስለድርጀቶች አባላት እና ተሳትፏቸው

በመፅሐፌ ውስጥ፣ አውጁን በማርቀቅ ብቻ ሳይሆን በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉትን ሰዎች ስም ጭምር ዘርዝሬአለሁ። አንዳንዶቹ ተሳታፊዎች በጊዜው የነበሩት የአንዳንድ ሕቡዕ ድርጅቶች አባል እንደነበሩም አመልክቼአለሁ። አስከትዬም፣ “አብረው የሠሩት እንደግለሰብ የመንግሥት ተቀጣሪ እንጂ፤ የፖለቲካ ቤተሰቦቻቸው ተወካይ በመሆን እንዳልሆነ” ገልጫለሁ። በሌላም ሥፍራ፣ የመሬት ይዞታ እና የአገር አስተዳደር ክፍለ ሀገራት ቢሮዎች ኃላፊዎች ከነበሩት መካከል፣ ግንባር ቀደም አስፈፃሚ የነበሩትን አንዳንድ ሰዎች ከነፖለቲካ ቤተሰባቸው ጭምር ዘርዝሬአለሁ። እርስዎም ይህንኑ፤ በመፅሐፍዎ ገፅ 89 እና

  • ውስጥ፣

“ከመካከላችን የእነዚህ ድርጅቶች አባል ስዎች የነበሩ ቢሆኑም እንኳ፣ እኔን ጨምሮ ሌሎቻችን የየትኛውም ድርጅት አባል አልነበርንም። እኔም ኢሕአፓን የተቀላቀልኩት አዋጁ ክወጣ በኋላ ነው” ብለው አስታውሰዋል። አቶ ዘገዬም ከላይ በተጠቀሰው መፅሐፍ ውስጥ፤ እንደሚከተለው አውስተውታል።

The Ministry of Land Reform was the hub of all these political groups. We had EPRP. We had MEISON, and we had people from small political groups. We agreed on a common goal፡ ‘Let us keep our politics to ourselves; and let us not frustrate the proper implementation of the Land Reform Program” (ገፅ፣ 53).

እርስዎን ያካተትኩት በስህተት እንደሆነ እና የኢሕአፓ አባል የሆኑት ከዚያ በኋላ እንደነበር አስታውቀዋል። የእርስዎን በሚመለከተው፣ ይቅርታዎን እጠይቃለሁ። የሌሎችን ስም በስህተት አክዬ ከሆነ፤ ስህተቴን ለማረም ዝግጁ ነኝ። ሆኖም፣ የሚከተለውንም አከለው ዘገቡ።

“(አንዳርጋቸው) አዋጁ የተዘጋጀው በመኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ ወዝ ሊግ እና ኦነግ ስምምነት እንደተዘጋጀ አድርጎ ያቀረበው ትርክት ፈፅሞ ስህተት ነው”(ገፅ 89)።

ከመፅሐፌ ገፅ 283 ውስጥ የጠቀሱትን አንቀፅ በቁንፅል ጠቅሰውም ጭምር፣ እንደማስረጃ ተጠቀሙበት። አመጣጥዎን ለማሰብ ብችልም፤ በጠቀሱት አንቀፅ ውስጥም ሆነ በመፅሐፌ ውስጥ በመላ፣ አዋጁ በዘረዘሯቸው ድርጅቶች ስምምነት ተዘጋጀ የሚል “ትርክት” ከአንድም ቦታ የለም። የዘረዘርኩትም፣ የአርቃቂ ኮሚቴውን አባላት ለይቼ አልነበረም። የአርቃቂው ኮሚቴ አባላት እና የአዋጁ ግንባር ቀደም አስፈፃሚዎች” ብዬ ነው። ሙሉ ይዘቱ የሚከተለው ነው።

“አዋጁ የተረቀቀው በመንግሥት ወይም በደርግ ትዕዛዝ በመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር ባለሞያዎች ነው። ነገር ግን ኤክስፐርቶቹ የዚህኛው ወይም የዚያኛው የፖለቲካ ድርጅት አባሎች ነበሩ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ካቀረብን፤ የአዎንታ መልስ ሊሰጥበት ይችላል። በተጨማሪም አርቃቂው ቡድን በወቅቱ በአገሪቱ አሉ ይባሉ የነበሩት ተራማጅ ምሁራንና የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎች ይገኙበት የነበረ የባለሞያዎች ቡድን ነበር ብንልም ያስኬዳል። ለዚህም የአርቃቂው ኮሚቴ አባላት የነበሩትንና የአዋጁ ግንባር ቀደም አስፈፃሚ የነበሩትን ምሁራን ከነፖለቲካ ቤተሰባቸው ጭምር ዘርዝሮ ለማቅረብ የሚቻል ነው። አንድ ማስታወሻ መጨመር ቢያስፈልግ በኮሚቴው ውስጥ አብረው የሠሩት እንደግለሰብ የመንግሥት ተቀጣሪ እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶቻቸው ተወካይ በመሆን እንዳልሆነ ነው።

“ወደ ዝርዝሩ ብንሻገር ከመኢሶን መስፍን ካሱና እኔ ነበርን። ከኢሕአፓ የመሥሪያ ቤቱ ቋሚ ተጠሪ ዓለም አንተ ገብረ ሥላሴ እና በኋላም ተስፋየ ታደሰ ገብረ መስቀል፣ ዶ/ር ተስፋየ ደበሳይ እና ዮሴፍ አዳነ ነበሩ። በባሮ ቱምሳ ዙሪያ ከነበሩት መሀከል ሚኒስትሩ ዘገየ አስፋው፣ በፍቃዱ ዋቅጅራ እና ዮሐንስ ነገዎ ነበሩ። በሕግሓኤ መስመር ከነበሩት መሀከል የአርቃቂው ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የነበረው ጣዕመ ሥላሴ በየነ ነበር። በዶ/ር ዓለሙ አበበ ዙሪያ ከነበሩት መሀከል ወንድወሰን ኃይሉ ነበር። በመጨረሻም በአጠቃላይ በመስመርና በወዳጅነት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ከየትኛውም ድርጅት ወይም ቡድን ጋር ያልተሳሰሩ ሌሎች ተራማጅ እና ዲሞክራት ምሁራን ነበሩ። ለምሳሌም ያህል ታምራት ከበደን፣ ታዬ ጉርሙን፣ ዶ/ር ክፍሌ ገብሩን፣ ኃይሉ ወልደ አማኑኤልንና የመሳሰሉትን ለማስታወስ ይቻላል። ከነዚህ ከኋለኞቹ መሀከል ታምራት ከበደ ከመጀመሪያዎቹ የመኢሶን አባላት መሀከል ሲሆን በየካቲት 1965 ከድርጅቱ የተለየ ነበር።”

በኅዳር 29 በናሁ ቲቪ ላይ ባደረጉት ቃለ መጠይቅዎ ፣ ዝርዝሩን በተጠቀሰው ዘዬ ያቀረብኩት “ክሬዲት ለመውሰድ ነው” እያሉ ያሳውቁትን አደመጥኩ። ጋዜጠኛው እያሟሙቀ ሲመላለስበትም ተመለከትኩ። ይሁንና፣ ከላይ በተጠቀሱት አንቀፆች ውስጥ፣ ለመኢሶንም ሆነ ለራሴ ለይቼ የሰጠሁት የተለየ “ክሬዲት” የለም።

 

ይህንን በዚሁ ልለፈው እና፣ በንጉሠ ነግሥቱ ዘመን በመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ይደረጉ የነበሩት ጥናቶች እና ይዘጋጁ የነበሩት ረቂቆች ምስጢር አልነበሩም። አንዳንዶቹንም፣ በተማሪ ማኅበራት መፅሔቶች ውስጥ እየወጡ እንወያይባቸው ነበር። በመ/ቤቱ እየተዘጋጁ ለደርግ ይቀርቡ የነበሩት የመሬት ለአራሹ አዋጅ ረቂቆች እና በተለያዩ ጊዜያት ከደርግ ጋራ ይደረጉ የነበሩት ውይይቶች እና ምልልሶችም እንደዚሁ ምስጢር አልነበሩም። እንዲያወም፣ አንዳንድ በሕቡዕ የነበሩ ድርጅቶች ከአንዳንድ የመ/ቤቱ ባልደረቦች እና በተለያዩ ጊዜያት ከደርግ ጋራ ይደረጉ የነበሩት ውይይቶች እና ምልልሶችም እንደዚሁ ምስጢር አልነበሩም። እንዲያውም፣ አንዳንድ በሕቡዕ የነበሩ ድርጅቶች ከአንዳንድ የመ/ቤቱ ባልደረቦች እና ከአንዳንድ የደርግ አባላት ጋር በነበሯቸው ግኑኝነቶች አማካኝነት ይሰሟቸው እና ያውቁ ነበር። ድርጅቶቹም ሃሳቦቻቸውን ያካፍሉ ነበር። ይህንን ድርጅታዊ አሠራር አሁን ሳወሳ፤ አሁንም “ክሬዲት ለመውሰድ ነው” በማለት እንዳማይተረጎሙት ተስፋ አደርጋለሁ። ከተረጉሙትም፣ የመንግሥትን ነገረ ሥራ እና አካሄድ ለማወቅ በዙሪያው “ማነፍነፍ” እና መረጃዎችን መሰብሰብ፤ የፖለቲካ ድርጅት አሠራር ሀሁ እንድሆነ አስታውሼዎት አልፋለሁ። በጥቅምት 1967 ይመስለኛል፣ “ደርጎች በአንዳንድ ጉዳይ እየደርቁ ናቸው። የምታውቋቸው ሰዎች ካሉ አነጋግሯቸው” የሚል መልዕክት ተቀብዬ፤ ለመኢሶን አመራር አድርሻለሁ። በተረፈው፣መፅሀፌን ያዘጋጀሁት አብዮቱ በተለያዩ ወቅቶች የተከናወነበትን አውዶች እና በየወቅቱ የተጓዘባቸውን ሂደቶች ማቅረብ በሚል እሳቤ ተመርቼ ነው።

 

ሰለሞን ዋዳ ኃይሌ ፊዳ ቤት ተደበቀ

የሶዶ አውራጃ የመሬት ይዞታ ቢሮ ኃላፊ ስለነበረው ሰለሞን ዋዳ ባተቱበት አንቀፅ ውስጥ፣ የሚከተለውን ፅፈዋል።

“ሰለሞን ከወላይታ ከተሰወረ ብኋላ ከኃይሌ ፊዳ ቤት ተደብቆ እንደቆየ ዘገዬ ነግሮኛል።…. ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ‘ሰለሞን እንዲጠፋ

አደርኩ’ ብሎ ለዘገዬ አስፋው እንደነገረው፤ ዘገዬ እራሱ በጊዜው ነግሮኛል” (ገፅ፣ 109)።

ይህንን ጉዳይ፣ አቶ ዘገዬ ከላይ በጠቀስኩት መፅሐፍ ውስጥ ሰለሰለሞን ዋዳ ያሉት የሚከተለው እንደነበር አስታውሼ አልፈዋልሁ።

“The settlers there (in Wolayta) really concocted a story that he (Solomon) was organising people to march against a certain Amhara, who were residing in Walaita town. He had to run away from his place of assignment. While on route to Addis Abeba, he called me several times on the phone. I was also stupid. I was answering (his calls) and telling him to ‘please come to me. We can do something.’ But instead, he was trying to escape through Begemder (Gondar) Province to Sudan, and he got caught by the military; he was unfortunately executed. I went and asked Mengistu, ‘how on earth could such a thing be done under your leadership?’ “And he said, ‘I was outvoted’.” (ገፅ 55-56)።

አቶ ዘገዬ በተጨማሪም፤ በወለጋ ክ/ሃገር የነበረው ገመቹ መገርሳ ከወለጋ ሸሽቶ ከርሳቸው ቤት ተደብቆ እንደተረፈ አስታወሰዋል።

ሰለሞን ዋዳ በወላይታ በተነሳው ግጭት ምክንያት ወደጎንደር እንደሸሸ እና መተማ ላይ ተይዞ እንደተገደለ የወቅቱ ትኩስ ዜና ነበር። “ኮለኔል መንግሥቱ ሰለሞን ወደ ጎንደር እንዲያመልጥ አደረኩ” ማለታቸውን ግን፤ ከመፅሐፍዎ ከማንበቤ በፊት ሰምቼው አላውቅም። “ከተሰወረ በኋላ ሃይሌ ፊዳ ቤት ውስጥ

ተደብቆ ነበር” ተብሎ የተወራውንም፤ ካሁን ቀደም እልሰማሁም። በተለይ ከኃይሌ ቤት ስለመደበቁ የተነገረዎት ፍፁም ሃሰት መሆኑን ለመመስከር ግን፣ እሩቅ መሄድ አያስፈልገኝም።

አንደኛ፣ ኃይሌ ፊዳ “የዘር ቅስቀሳ” ፖለቲካ አራማጅ እና ተባባሪ አለነበረም። ሆኖም አያውቅ። ሁለተኛ፣ ኃይሌ እና እኔ በዚያን ወቅት የምንኖረው አፍንጮ በር አካባቢ ይገኝ በነበረው ቤታችን ውስጥ አብረን ነበር። ሰለሞን ዋዳ ከቤታችን ሊደበቅ ቀርቶ፤ ከቤታችን ደርሶም አያውቅም።

 

ስለመሬት ለአራሹ አዋጅ መረቀቅ እና የአተገባበር ሂደቱ ባጭሩ

የመሬት ይዞታን እና የባለርስት/ጭስኛ ግኑኝነት እንዲሻሻሉ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የተላያዩ አዋጆች እየተረቀቁ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል። ከነሱ መካከል፣ በተለይም በእናንተ፣ በወቅቱ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ሚኒስቴር በነበራችሁት ባለሙያዎች፣ የተረቀቁት የተለያዩ አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው። ደርግ ገና በ4ኛ ክፍለ ጦር እያለም፣ የጭላሎ እርሻ ልማት ድርጅት ሠራተኞች አንድ ረቂቅ ለደርጉ ሰጥተው ነበር። በእያንዳንዱ የመሬት አዋጅ ማርቀቅ ሥራ ውስጥ ተሳትፈው የነበሩ ሰዎች ስም ዝርዝር በትክክል መመዝገብ እና መታወቅ አለበት። ለእያንዳንዱ አስተዋፅዖም፣ ተገቢው ዕውቅና መሰጠት አለበት። ይህም፣ ከታሪክ ዝክር አንፃር ብቻ ሳይሆን፤ ከተጠያቂነትም አንፅር አስፈላጊ ነው። ሆኖም ግን ዋናው ጥያቄ፣ የአንዱ ወይንም የሌላው አዋጅ መረቀቅ አይደለም። የአዋጁ አተገባብር ሂደት ነው።

የየካቲት አዋጅ በሚተገበርበት ወቅት፣ አንዳንድ የቀደሞ ባለመሬቶች አዋጁን ተፃርረው የትጥቅ ትግል ጭምር አካሄዱ። በአንዳንድ አካባቢ ይነሱ የነበሩ ሁከቶች፤ የብሔር ግጭት ባሕሪይ አላቸው እየተባለ ተወራ። አንዳንድ የታጠቁ ባለመሬቶች በደቦ በወስዷቸው ማጥቃቶች፣ የበርካታ ዘማቾች ሕይወት በጅምላ ተቀጨ። ዘማቾችም በአንዳንድ ሥፍራ፣ ከአዋጁ መመሪያ እና መንፈስ ውጭ የነበሩ እርምጃዎችን ወስዱ። ይህም ሆኖ፣ ያ እጅግ ሥር ነቀል አዋጅ በአገሪቱ በመላ የተተገበረው፣ በንፅፅር በአጭር ጊዜ ውስጥ እና በተገናዛቢ ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ይህንን ሂደት ያስቻሉት ሁኔታዎች፣ ቀደም ሲል እና አዋጁ ከወጣ በኋላ የተከናወኑት አምስት የተያያዙ ጉዳዮች ነበሩ።

በመጀመሪያ እና እንደሚታወቀው፣ የመሬት ለአራሹ ጥሪ የሠፊውን አርሶ አደር ሕዝብ ጭብጥ ጥቅም የሚመለከት እና አርሶ አደሮች በተለያዩ ጊዜዎች እና መንገዶች ሲታገሉለት የነበረ ጥያቄ ነበር። የኢትዮጵያ ሊበራሎች፣ ተማሪዎች፣ የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ በሕቡዕ የነበሩ ተራማጅ ድርጅቶች፣ ስብስቦች እና አርሶ አደሮች ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ ሲጠይቁት እና ሲታገሉለት የነበረ ጥያቄ ነበር። ይህም በራሱ፣ ቀድም ሲል ጀምሮ ለሥርዓት ለውጥ ይደረግ ለነበረው ትግል የፖለቲካ መደላድሉን አስፍኖ ነበር። ነገሮች በዚህ እንዳሉ፣

 

  • የየካቲት1966 ሕዝባዊ አብዮት እንቅስቃሴ ተነሳ። ሕዝባዊው አብዮት በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ከቡድን ጥቅም እና ከፖለቲካዊ ለውጥ ጥያቄዎች አልፎ፣ ወደ ማኅበራዊ አብዮት ለውጥ ዓይነት ተሻገረ። ዋነኞቹ የለውጥ ጥያቄዎች፣ መሬት ለአራሹ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ይለቀቁ የሚሉ ነበሩ።

 

  • የንጉሠ ንገሥቱ ዘመን የገዢ መደብ እና የባለመሬት ማኅበራዊ ክፍሎች፣ ከየካቲት1966 ጀመሮ በተካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እና፤ ደርግ በተለይም በኅዳር 14፣ 1967 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ባለሥልጣኖች ላይ በፈፀመው የግፍ ግድያ ምክንያት፤ እንደመደብ በእጅግ ተዳከሙ። እነዚህ ከሥልጣን ማማዎች እና ከማኅበራዊ አቀማመጥ ከፍታቸው እየወረዱ የተዳከሙትንም ያህል፣ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ባለመሬቶች መደብ፤ የመደብ አጋር ሊሆኑት ይችሉ የነበሩትን ከፍሎች ድጋፍ አጣ።

 

  • በዚህ ላይ፣ ከ60 000የማያንሱ አዝማቾች እና ዘማቾች በመግሥታዊ ጡንቻ (በመለዮ ለባሾቸ እና በፓሊስ አባሎች) እየታጀቡ በከተሞች እና በገጠሪቱ አትዮጵያ ፈሰሱ። ይህም፣ በኢትዮጵያ ከተሞች እና ገጠር የነበረውን የኃይሎች አሰላለፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሥረ መሠረቱ ለውጦ፣ የአስላልፍ ሚዛኑን ወደ አብዮቱ ወገኖች ደፋ።

 

  • አስፈፃሚዎቹ የመሬት ይዞታ እና የአገር አስተዳደር ሚኒስቴሮች ሠራተኞች፣ አዝማቾች፣ ዘማቾች፣ ምሁራን፣ መለዮ ለባሾች እና የፖሊስ ሠራዊት አባሎች ከአርሶ አደሩ መደብ ጋር አምርረው እየወገኑ ተዋደቁ።
  • በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተጨባጭ ተፈጥሮ የነበረው ኅብረት እና ትብብር በራሱ ብቻ ለማለት ይቻላል፤ የአዋጁ ተቃዋሚ በነበሩት የቀድሞ ባለመሬቶች ላይ ከባድ ሥነ ለቦናዊ ጫናን አሳረፎ በባሰ አዳከማቸው።

 

ብዙዎች በወቅቱ ይሉት እንደነበረው በውነትም፣ ያንን ኅብረት እና ትብብር ያስቻሉት ያ የጋራ አቋም እና ትብብሩ የተደገፈባቸው እነዚያ ዝግጅት እና ማቴሪያላዊ አቅም ነበሩ። እነዚህ ባይኖሩ ኖሮ፣ አዋጁ እንደዚያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እና በተገናዛቢ ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ አይተገበርም ነበር። ደርግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይፈፅማቸው የነበሩት የወደኋላ/ወደፊት መዋለሎች የተገቱትም፣ በዝያ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በተፈጠረው ኅብረት እና ትብብር ጥንካሬ ነበር።

የየየካቲት 1967 ዓ.ም. የመሬት ለአራሹ አዋጅ በመሠረቱ እና በዋናነት የተተገበረው በዝያ ኅብረት እና ትብብር ጡንቻ ነበር። ድሉም፣ ያ ኅብረት እና ትብብር በኢትዮጵያ ፊውዳላዊ ሥርዓት ላይ የተቀዳጀው የጋራ ድል ነበር። ትግሉም የመደብ ትግል እንጂ፤ የብሔር ገጭት አልነበረም። በፍፁም ፍፁምም ደግሞ፤ ዛሬ ዛሬ ከፅንሰ ሃሳባዊ ምንነቱ ጭምር ተፋቶ እንደሚሰማው፣“በዘር ቅስቀሳ” እና ግጭት የተበከለ አልነበረም። ወቅቱ በጥቅሉ ቢገለፅ፣ የአብዮቱ አራማጅ ኃይሎች የበላይነትን ሥፍራ ይዘው በጋራ የታገሉበት ወቅት ነበር።

በተከተሉት አጭር ወራት ውስጥ ግን፣ አሰላለፎች የተለዋወጡባቸው ሁኔታዎች እያንሠራሩ አብዮቱ ከአጥቂነት ወደተከላካይነት የወረደባቸው እና የመከላከል እርምጃዎች የተወስዱባቸው ወራቶች ሆኑ። አሰላልፉ የተወሳሰበ እና ትንቅንቁም በውዥንብር የተሞላበት ሁኔታ ደነደነ። አብዮቱም የዚያኑ ያህል፣ ከመጨንገፍ ሂደት ውስጥ እንደገባ ተደርጎ የታየበት ወቅት ሰፈነ።

የመጀመሪያው ጉዳይ፤ በተራማጁ ሠፈር ውስጥ ዘመቻው ይበተን/አይበተን በሚል የተነሳው የአመለካከት እና የትግል ሥልት ልዩነት ያስከተለው የኃይል ሚዛን ለውጥ ነበር። ልዩነቱ ያስከተለውን በአጭሩ ለማስታወስ፣ ዘመቻው የተበተነውን ያህል እና በመሬት ይዞታ እና በአገር አስተዳደር ሚኒስቴሮች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ተራማጆች ሕቡዕ እየገቡ ወደ አሲምባ ያቀኑትን ያህል፤ በአርሶ አደሩ እና በተራማጁ ሠፈር መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ኅብረት እና ትብብር የሚይዳክም ሁኔታ ተፈጥረ። የዚያኑም ያህል፣ የገጠሩ እና ወደ ከተሞች ሸሽተው የነበሩት ባለመሬቶች በወሬ እና በታጠቀ ትግል ጭምር ተሰልፈው አብዮቱን ወደ ማጥቃት ተሻገሩ። እንደወሬው ከነበረም፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኅብረት (ኢድኅ) ይባል የነበረው የመሣፍንት ድርጅት ለምሳሌ፤ ከቤገምድር ተነስቶ አዲስ አበባ ላይ ሥልጣንን ለመጭበጥ የቀረው አንድ ሃሙስ ነበር።

ሁኔታዎች በዚህ እንዳሉም ነበር፤ ደርግ በአንድ በኩል እና ተደናግጦም ጭምር ለማለት ይቻላል፤ የሐምሌ 19፣ 1967 ዓ.ምን. የከተማ መሬት እና ትርፍ ቤቶች ያወጀው። ይሁንና፣ አዋጁ በራሱ ብዙዎችን ወደተቃዋሚነት የገፋና አሰላለፎችን በባሰ ያተራመሰ እና የትግሉን አውድ የባሰውን ያወሳሰበ ሆነ። ደርግ በሌላ በኩል ግን፣ አንድ አደርጅ ኮሚቴ የተባለን አሃድ አቋቁሞ እየሠራም ነበር። የኮሚተው ሥራ ውጤት፣ ለአብዮቱ አራማጅ ሠፈር ይበጁ የነበሩ ሁኔታዎች መወሰድ ነበር።

የመስከረም 19ኝ 1968 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ኅዳር 25፣ 1968 ተነሳ። በዘመቻው ላልተካፈሉ ዘማቾች “ምሕረት” ተደርጎ የዘመቻው ጊዜ ተራዘመ። ከ100 በላይ የሚሆኑ ተራማጅ ምሑራን፣ 26 የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች እና 18 የመምሕራን ማኅበር መሪዎች ከእሥር ተለቀቁ። ታወጀ። የኢሠአማ ቢሮ ተከፈተ። የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ፅ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ እና የብሔራዊ ዲሞክራትቲክ አብዮት ፕሮግራም ወጡ። የከተማ እና የገጠር ቀበሌ ማኅበራት ማጠናከሪያ አዋጆች እና የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ታወጁ። የየካቲት ’66 የፖለቲካ ት/ቤት፣ የውይይት ክበቦች እና የአብዮት መድረክ ተከፈቱ። በኤርትራ ላይ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሳ። ግንቦት 8፣ 1968 ዓ.ም. የኤርትራን ጉዳይ በፖለቲካ መንገድ ለመፍታት “የዘጠኝ ነጥቦች የፓሊሲ ሠነድ” ወጣ። በአጭሩ፣ ለአብዮቱ አራማጅ ኃይሎች ሠፈር እንቅስቃሴ እና መጠናከር ያመቹ ሁኔታዎች እየተገለጡ የመጡበት አና የአብዮቱ አራማጅ ወገኖች የተጠናከረ መከላከል እርምጃዎችን ለመውሰድ የቻሉበት ወቅት ከፈተ።

ይህም ግን፣ ከአንድ ዓመት ዕድሜ በላይ የነበረው ወቅት አልነበረም። ምክንያቱም፣ የተከተሉት ወራት በአንድ በኩል፣ በአብዮቱ አራማጅ ኃይሎች መካከል እየሰፋ በሄደው የትግል ሥልት ልዩነት ብቻ ሳይሆን፤ ከመስከረም 1969 አንስቶ በጀመረው የፖለቲካ ግድያ ዓይነተኛ ሆኑ። በሌላውም በኩል፣ ከሶማሊያ ወረራ ጋር ተያይዞ አዲስ ብሔራዊ እና ውጫዊ አሰላላፍ ተፈጠረ። ኮለኔል መንግሥቱ ወረራውን ተጠቅመውም ጭምር፣ የአብዮቱን አራማጅ ኃይሎች በአብዮታዊ ሰደድ ጡንቻ እየደቆሱ አጠፉ። እስከ የኢሠፓው አንድ ፓርቲ አገዛዝ ድረስ ለመጓዝ እና የአንድ የራሳቸውን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማቆም በቁ። የአብዮቱ አራማጅ ኃይሎች የተዳከሙትን እና ከጨዋታው ውጭ እየሆኑ የሄዱትንም ያህል፣ ትግሉ በኢሠፓ አገዛዝ እና በታጠቁ የብሔር ድርጅቶች መካከል እየሆነ ሄደ። ይዘቱ እና ሂደቱ በእኔ እና በበርካታ መፅሐፍት ውስጥ ታትተው ይገኛሉ።

 

ለማጠቃለል

ከላይ እንዳልኩት፣ መፅሐፍዎን አግኝቼ በጥሞና አነባለሁ። ወቅቱ አጣዳፊ ነበር። ሁኔታዎች እና ኹነቶች የሚደርሱት በየዕለቱ እና እየተደራረቡ ነበር። በዚህ ላይ፣ የሆነው ያልሆነው ይወራ እና ይነገር ነበር። ሃምሳ ክረምቶችም ተቆጥረዋል። ስለዚህ፣ አንዳንድ ጉዳዮች የተከናወኑበት ሁኔታ እና አንዳንድ ኹነቶች የተከሰቱበት ጊዜ ተሟልቶ ባይታወሰን ይገባኛል። ከዓመታት በኋላ የሚደረሱ መፅሐፍት እና ፅሑፎች አንዱ ጥቅም፣ አንዱ የዘነጋውን ሌላው እንዲያስታውስ ማገዛቸው ነው። የተመለስኩባቸው ጉዳዮች እንዲታረሙ የምጠይቅዎት፣ በዚህ መንፈስ ነው።

ይህንን ግልፅ ማስታወሻዬን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎች፣ “አሁን በዚህ ጌዜ” እያሉ ቢተቹ ይገባኛል። ይሁንና፣ ከራሴው ጋር ብዙ ከተሟገትኩ በኋለ፣ የበኩሌን ለማሳወቅ ወሰንኩ። ምክንያቶቼ ሁለት ናቸው። አንደኛ፣ መፅሐፉ የወጣው አሁን በዚህ በኅዳር ወር ስለሆነ፤ በብዛት የሚነበበው አሁን ነው። መፅሐፍዎ ዛሬ እንደ የግል ማስታወሻ የሚነበብ ቢሆንም ቅሉ፤ ውሎ አድሮ የምርምር ግብዓት ይሆናል። ስለዚህም፤ አንባቢያን እና ተመራማሪዎች የሌላውንም ማስረጃ እና አመለካከት ከአሁኑ እና በትኩሱ ቢያውቁት ይሻላል ብዬ አመንኩ።

ሁለተኛ፣ በኅዳር 29 በሠፊው የተሰደደውን ቃለ መጠይቅዎን ሳዳምጥ፤ በአንድ በኩል፣ የጠያቂዎ ጋዜጠኛ ግብ እና አካሄድ ከእጅግም በእጅግ በወገንተኝነት የተሟላ መሆኑን አስተዋልኩ። በሌላው በኩል፣ በዚህች ፅሁፍ ስህተት መሆናቸውን ባመለከትኳቸው ጉዳዮች ላይ እየተመላለሱ፣ በቃል እና በእንቅስቃሴ ጭምር ሲያጠናከሯቸው ተመለከትኩ፣

የእርስዎ እና የእኔ ትውስታዎች የዛሬ ሥፍራ፣ ለየቅል እና አንዳንዴም እግረ መንገዶች እያገናኙን በጋራ የኖርውን ከመዘከር ያለፈ አይደለም። ትውስታዎቻችን ሆኖም ግን፤ የተለያዩ መዛግብትን፣ ሰነዶችን፣ መፅሐፍትን እና ፅሑፎችን አመሳክረው ለሚያጠኑ እና ለሚመረምሩ ባለሙያዎች ይጠቅማሉ። የየካቲት ሕዝባዊ አብዮት የተካሄደባቸውን የተለያዩ አውዶች እና በየወቅቱ የተጓዝባቸውን የተለያዩ ሂደቶች ከማንኛውም ዓይነት ወገንተኝነት በፀዱ አካዳሜሺያን እና ጋዜጠኞች የሚዘከሩበት ጊዙ እንዲቀድ እመኛለሁ።

 

 

 

1 Comment

  1. አለም አንተ ገ/ስላሴ ትግሬ ነው ኤርትራዊ? ይህንን መጠየቅ ያስፈለገበት አስተሳሰባቸው ሁልጌዜ ጤነኛ ካለመሆኑም በላይ ይዞት የሚመጣው ተንኮል ስላለ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop