November 26, 2024
14 mins read

ስህተትን በስህተት የማስተናገዱን አስቀያሚ የፖለቲካ ባህል ካልታገልነው ታጥቦ ጭቃ እየሆን ነው የምንቀጥለው!

maxresdefault 12November 25, 2024

ጠገናው ጎሹ

ከአስቸጋሪው የፖለቲካ ባሀላችን እየመነጩ በእጅጉ ከሚፈታተኑን አስቀያሚ እውነታዎች አንዱ ልክ የሌለው የግል   ዝና ( excessive self-aggrandizement ) ፈላጊነታችን ነው። ፋኖም በዚህ አስቀያሚ የፖለቲካ ሰብዕና አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ለጊጊዜውም ቢሆን ከተሸነፉ ግለሰቦች ነፃ ባይሆን አይገርምም። ከልክ እያለፈ ጊዜን፣ ገንዘብንና ሰብአዊ ሃብትን አላግባብ ሲያባክንና በተለይም ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለበትንና እየተከፈለበት ያለውን የህልውና እና የነፃነት ተጋድሎ አደጋ ላይ ሲጥል መታገስ ግን ፈፅሞ ትክክል አይሆንም። ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች የመኖራቸው እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ  እጅግ አስከፊ ፣ አሳፋሪ  የሆነው እና መከረኛውን ህዝብ የእኩያን ገዥ ቡድኖች መጫወቻና መሳለቂያ  የሚያደርገው ውድቀት የሚመነጨውም ከዚሁ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህሪያችንና ባህላችን ነው።

አዎ! እንደ እስክንድር ነጋ አይነት ወገኖች ለከፈሉትና በመክፈል ላይ ላሉት  ዋጋ እውቅና እና አድናቆት አይገባም የሚል ጤነኛና ነፃነት ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። አሁን ከምንሰማውና ከምንታዘበው   ህሊናን የሚያንገጫግጭ ባህሪና ድርጊት አንፃር ግን  የሆኑትና ያደረጉት ሁሉ በዜሮ ቢባዛ ሊገርመን አይገባም። በተለይ  ተገቢና አስቸኳይ  እርምት  ለማድረግ  ፈቃደኞችና  ዝግጁዎች  ካልሆኑ።   አዎ!  ያለፈውን ግዙፍና የሚደነቅ ክሬዲት በአግባቡ  ይዘን አግባብነት ላለው ሥራ ካላዋልነው ከስህተት ለማይማረው ለዛሬውና ለነገው  ምንነታችንና ማንነታችን ፈፅሞ ዋስትና አይሆንም ፤ ሊሆንም አይገባም።

ሌላውና አስቸጋሪው አስቸጋሪው ፖለቲካዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እኛነታችን  የአድናቆታችንና የትችታችን መንሸዋረር (በማስተዋልና አግባብነት ባለው ሂሳዊ አቀራረብ ያልታጀበ አለመሆኑ)  ነው። ለዚህ ነው አሁን እንደምንታዘበው እንደ እስክንድር አይነቶቹ  ወገኖቻችን ከህዝብ ያገኙትንና  ከሰው ልጅ ባህሪ ውጭ ወደ ፍፁምነት የተጠጋ ምስጋና እና አድናቆት በተሳሳተ አኳኋን በመተርጎም ራሳቸውን  ክንፍ  አልባ  መላእክት ፖለቲከኞች አድርገው እያዩብን  የተቸገርነው።

ለህዝብ ሲባል እንዲህ አይነት ወገኖችን በአግባቡ መንገር፣ ማነጋገርና  በራሳቸው ፈቃድ የተሸከሙትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እና አይ ከእኛ ወዲያ ላሳር ነውና አትናገሩን  ወይም  የሚተች  የፖለቲካ   ማንነትና ምንነት የለንም”  የሚሉ ከሆነም  እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሰብእና ለዘመናት ተፈትኖ አይወድቁ ውድቀት አስከትሏልና  ሃላፊነቱን በክብር አስረክቡና በክብር ተሰናብቱ  ማለት የግድ ነው። ለምን?  ቢባል እስከመቼ   ነው መከረኛው ህዝብ በግለሰቦች አስቸጋሪና ከመጠን ያለፈ እወቁልኝና እወቁኝ ባይነት ምክንያት የመከራና የውርደት  ህይወትን እየተጋተ የሚቀጥለው?  የሚለው ግዙፍና መሪር ጥያቄ ሳይመለስ ሌላ አያሌ ዘመንን ማባከንና የአስከፊ ባርነት ሰለባ እየሆኑ መቀጠል እንኳንስ የምንታገሰው የምናስበው ጉዳይ ሊሆን አይገባውምና ነው ።

እስክንድር ለትራምፕ የውጭ ጉዳይ አለቃነት የመለመለውን ሮቢዮን ያውቀዋልና ፣ ወዘተ የሚለው በአሁኑ ወቅት እስክንድር መሬት ላይ ከሚሆነውና ከሚያደርገው  የልጆች ጨዋታ ፖለቲካ አይነት  ጋር ሲታይ እውን ስሜት  ይሰጣል እንዴ?  ደግሞስ የዘመናችን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ  የዓለም ፖለቲካ ፣ የዓለም አቀፍ ግኑኝነትና  የዲፕሎማሲ  ተልእኮና ተግባር በዚህ ልክ  አቃለን ነው  የምናየው እንዴ? እውን አንደን ባለሥልጣን በሆነ አጋጣሚ ማወቃችንና መተዋወቃችን ምናልባት ደግመን ስንገናኘው አዲስ ያለመሆንና የሃሳብ ልውውጣችን በአንፃራዊነት ያቀልልን እንደሆነ እንጅ እንደምናስበው ድጋፍ  በድጋፍ ያንበሸብሸናል እንዴ? እንዲህ እጅግ ግልብ እይታ እኮ የተም አያደርሰንም።

እዚያው በመሬት ላይ ካሉና መስዋእትነት ከሚከፍሉ ሁሉም የህልውና እና የነፃነት ተጋዳይ ጓዶች ጋር ሲሆን የመሪነቱን ሃላፊነት አንተ ትመጥናለህ ወይም አንች ትመጥኛለሽ እና እኔ በሚፈጠረው የዘርፈ ብዙ አመራር  ውስጥ ሆኘ እጅግ ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮችን እየተከታተልኩና እያደራጀው ለአመራራችን ግብአትነት አቀርባለሁ በሚል ገንቢና ትክክለኛ ትህትና ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ የመሪነቱ ቦታና ሃላፊነት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሚካሄድ ውይይትና ውሳኔ ሳይሆን ሰፊና ጥልቅ የሃሳብ ልውውጥና ከምር የሆነ የጋራ መግባባት ላይ እንዲፈፀም ማድረግ ሲገባ ከዚህ መንፈስና አሠራር ውጭ  አሸንፌ  ተመርጫለሁና  ከፈለጋችሁ  በእኔ ሥር ካልሆነ ግን አትረብሹኝ የሚልንና እጅግ ግልብ የሆነ ዝና ፈላጊነትን ፈፅሞ በዝምታ ወይም ከምንም በማያድን/በማይታደግ  ፍርሃት  ማለፍ ፈፅሞ አይጠቅምም። ይልቁን ሳይቃጠል  በቅጠል ይሻላል ።

አዎ! እዚያው መሬት ላይ  ያሉትን የፋኖ መሪዎችንና ሌሎችንም ጊዜ ወስዶና ታግሶ በማወያየትና  በማማከር አንድ አይነት የጋራ ስምምነት ያለበትን  አደረጃጀትና ስያሜ መፍጠር  እየተቻለ  ህዝባዊ  ድርጅት  እና እዝ   በሚባሉ ስያሚዎች  ራሱንና ከእርሱ ጋር የተስማሙትን ይዞ “የተመርጫለሁና የአሸንፌያለሁ”  አዋጅ በማወጅ በህዝብ የተሰጠን አድናቆት ማበላሸት ፈፅሞ ትክክል አይደለም።

አዎ!  ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በትእግሥት፣ በጥበብና በእልህ አስጨራሽ የጋራ ጥረት መታየትና  መወሰን የነበረበትን የፋኖ መሪነት እጅግ ግልፅ ባልሆነና የልጆች ጨዋታ በሚመስል ሁኔታ  ከዛሬ  ጀምሮ  በድምፅ  ብልጫ  አሸናፊነት  የመሪነትን ቦታ ይዣለሁና እወቁልኝ” በሚል  በራሱ አንደበት ያነበበልን አዋጅ ግራ ያላጋባውና ያላስደነገጠው እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር  አይመስለኝም።

ታዲያ እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ሰብእና  ለአንተም ሆነ ለትግሉ እና በተለይም ለአማራ ህዝብና  በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይጠቅምምና አሁንም አደብ ገዝተህ  ወደ ትክክለኛው  መስመር በመግባት   ያበረከትከው የረጅም ጊዜ  መስዋእትነት በወርቅ ቀለም እንዲፃፍ አድርግ” ለማለት የምንፈራ/የምንሽኮረመም ከሆነ  ስለ የትኛው  የፋኖ  ትግል ድል አድራጊነት ነው የምናወራው

ይህንን አስተያየት ስሰነዝር የጋግርታሙ ፖለቲካ ባህላችን ልክፍት  የእስክንድር ብቻ ሳይሆን  የሌሎችም  የፋኖ መሪዎች እንደሚሆን   ዘንግቸው አይደለም። እስካሁን ባለው  ግልፅና ግልፅ መረጃ

  በፋኖ  መካከል  ሌላ የፋኖ ቡድን (ህዝባዊ ድርጅትና ወታደራዊ እዝ)  ፈጥሮ በትግሉ ላይ አላስፈላጊ ጫና እና ፈተና እንዲከሰት በማድረጉ

ከትግሉ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር  ሁሉንም አሳታፊ የማያደርግ ቅድመ ዝግጅትና ግልፅነት  በሌለው አካሄድ (ጥድፊያው  ለምን እንደ ነበር  ለመረዳት በሚከብድ ሁኔታ)  በዴሞክራሲያዊ  አሠራር  ተመርጫለሁና   ይህንን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት መሞከር ፀረ ዴሞክራሲነት”  በሚል አይነት የፖለቲካ ሰብእና የሄደበት መንገድ በራሱ በዴሞክራሲ መቀለድ ስለሆነ ነው የእስክንድርን ጉዳይ   እንደ ከስህተት   የመማሪያ ጉዳይ አድርጌ የወሰድኩትና ከአፅንኦት ጋር ሂሳዊ አስተያየቴን የሰነዘርኩት።

ለዘመናት ለመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ለምንገኝበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት እንድናደርግ ካደረጉን ፈተናዎች መካከል የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን (political culture of civility) ከአገራችን በጎ ባህሎች ጋር ባጣጣመ መልኩ ለመቀበልና ለማዳበር ያለመቻላችን ደካማነት ውድቀት ነው። ከሥልጡን ፖለቲካ መገለጫዎች መካከል አንዱ ደግሞ የምንሰራውን  ስህተት ሲሆን ራሳችን ተገንዝበንና ተቀብለን በራሳችን የማረም ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በግል ጥላቻና በስሜታዊነት ሳይሆን ግልፅ/ተጨባጭ በሆነ ይዘትና አቀራረብ  ሌሎች የሚሰጡንን ሂሳዊና ገንቢ ትችት ለመቀበልና ለማስተካከል የመቻላችን አስፈላጊነት ነው።

እስክንድርና ሌሎች የህልውና እና  የዴሞክራሲ ፋኖዎች /አርበኞች ይህንን ሂሳዊ  አስተያየቴን ከዚህ  ግዙፍና መሪር እውነታ አ ንፃር እንደሚገነዘቡት ተስፋ  እያደርጉ አበቃሁ!

Go toTop

Don't Miss

Eskinder

ኳሷ ያላችው እስክንድር ነጋ ጋር ነው – ግርማ ካሳ

እስክንድር ነጋ በኢትዮ360 ቀርበ ነበር፡፡ ማስታወቂያውን አስቀድሞ ስለሰማሁ ቃለ ምልልሱን
193287

እስክንድር ነጋ ተካደ | ከፍተኛው የደህንነት ሀላፊ ተሸኘ | ሰራዊቱ ለቆ ሊወጣ ነው? “በቃን ህዝቡ ጠልቶናል”ባለስልጣናቱ ከነገ ጀምሮ እግዱ ተነስቷል

እስክንድር ነጋ ተካደ | ከፍተኛው የደህንነት ሀላፊ ተሸኘ ሰራዊቱ