የቀን ጅብ አለቅጥ ከፍቶ ቆሞ እየሄደ ሰውን ሲበላው ሲታመስ አገር፣
እርግቦች ተምድር ሲጠፉ ጆፌው ግን ልፋጩን ይዞ በሰማይ ሲበር፣
ዓለምን ንቆ ገዳም የገባ የእውነት መነኩሴ አንገቱን ደፊ መናኝ ለመምሰል፣
ኧረ ተው ሰጎን ኩምቢህን ተጉድጓድ ከተህ አንገትን ቀብረህ አትኑር፡፡
የአእዋፍ ስደት ዘር ፍጅት ለማስቆም ንሥር እንደ ጀት በሰማይ ሲበር፣
አንተ ተውሽንፍሩ ያመለጥክ መስሎህ ተድቡሽት ራስ ስትቀብር፣
ዶፍ ዝናብ ሲወርድ ተጉድጓድ የምትወጣውን ያይጧንም ያህል አታፍር?
ሰውም ከብቱንም አርዶ እሚበላ ሰይጣን የላከው ፋሽሽት ሲመጣ፣
ባምስቱ ዘመን አላየህም ወይ መናኝ መነኩሴ እንኳን እየፎከረ ሲወጣ፣
ምንይሽር ጓንዴ በልጅግ አንግቶ ጀበርና ዝናሩን ታጥቆ ሲቆጣ!
እረጅም አንገት እያለህ ዞር ብሎ ማያ አይምሮ እዝነ ልቡና ያጠረህ፣
በኩምቢህ ገጦች ገላልጠህ ብራና አንብበህ የዓለምን ታሪክ ማወቅ ያቃተህ፣
አንዳንድ እርግቦች የጠፉት በየዋህነት ስላልታገሉ መሆኑ ዛሬም ያልገባህ፣
ካጂው ጥንብ አንሳ መጥቶ በቁምህ ሆድህን እስቲዘረግፍ ትጠብቃለህ?
ኧረ ተው ሰጎን መስሎ ማደሩ አድርባይነት ይቅርብህ ታርዶ ሲጠፋ ወገንህ፣
ጆቢራው ጫጩቶችህን እየጨለፈ ተምድር ሲያጠፋ ተጅብ ጋር ሲቆምርብህ!
የሰጎን ዘሮች በጥንብ አንሳዎች ሲበሉ በባንዳ ጭልፊት መሪነት፣
ድምጥህን አጥፍተህ መኖሩ ይኸንን የማታውቅ መስለህ እንደ ሙት፣
ምን ያህል ህሊናን ብትፍቅ ብታደርግ ተአንገት ማተብን ቡጭቅጭቅ?
ምድሪቱ ቁና ስትሆን በድሮን ባሩድ እሩምታ በሰማይ ሲበር ወቢ የተፋው ጥንብ አንሳ፣
ይኸንን ያህል ዝምታ ኩምቢ ቀስረህ ተክልህ ተአሸዋ ምግብና መጠጥ ፍለጋ፣
እግዚኦ መሀርነ ክርስቶስ ያንተስ ሆድ እንደ ውቂያኖስ የሰፋ የሚስያቀረጥፍ ይሉኝታ፡፡
የንሥር አርበኛ ተፋልሞ የአእዋፍ ዘር ፍጅት ሲቆም የተሻለ ቀን ሲጠባ፣
አታፍር ይሆናል እኮ ራስክን ተደበክበት አውጥተህ አንገት ነቅንቀህ ስትመጣ፡፡
የአእዋፍን ቆሽት የሚያነድ ልብ የሚያደማ የሚያስተዛዝብ ቀን መሽቶ ሳይነጋ፣
ኧረ ተው ሰጎን እንደ አይጥ መደበቅ አቁመህ ሞረሽ ሲጠሩህ ከች በል ተጀግኖች ሥፍራ፣
በሰማይ በረህ መፋለም ባትችል በምድር እየሄድክ የሚዋደቅን ንሥር እርዳ!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ህዳር ሁለት ሺ አስራ ሰባት ዓ.ም.